CURRENT

የመለስ ፋውንዴሽንና የአርብቶ አደሮች ፎረም የአርብቶ አደሮችን አቅም ለመገንባት ተስማሙ

By Admin

March 10, 2017

በአርብቶ አደር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችን እና ህፃናትን ለማስተማር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማስተዋወቅ እና በጥናት እና ምርምር ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ለማድረግ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን እና የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ፎረም ተስማሙ፡፡ተቋማቱ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን በጋራ ሊሰሯቸው የሚችሏቸው ነጥቦች ላይም ተስማምተዋል፡፡የአርብቶ አደሩን  ማህበረሰብ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የአየር ንብረትን ለመቋቋም የሚያስችሉ የምርምር እና የጥናት ስራዎችን በጋራ ለመሥራት ነው የተስማሙት፡፡

የመለስ ፋውንዴሽን ምክትል ሊመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ፋውንዴሽኑ ለሴት አርብቶ አደሮች ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ለአርብቶ አደሩ ዘላቂነት ያላቸው እቅዶችን እና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ማስፋት እንደሚገባም ነው የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ፎረም ሊቀመንበር አቶ አብዲ ሁሴን የገለፁት፡፡

በመድረኩ ከሴት አርብቶ አደሮች ጋር በተያያዘ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡