Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመልካም አስተዳደር እጦት ነዋሪውን አማሯል

0 393

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀደም ሲል በነበረው የመንግስት አሰራር አልጋወራሹ ለሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት የጉልበት ዋጋ መኖሪያ ቤት በመስጠት ነበር፡፡ በዚህ አሰራር በ1942 .56 አባወራና እማወራዎች በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የቤት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ይሄ መንደር «ጎመን» ሰፈር የሚለውን መጠሪያ ይዞ የበርካታ ሰዎች መኖሪያ ሆኖ ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ነዋሪዎቹ እንደነዋሪ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ ፣ሁሌም ቅሬታና አቤቱታቸውን ላለው አስተዳደር እያቀረቡ ጆሮ ዳባ ተብለው 67 ዓመታትን አስቆጥረዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት በሚገኘው ጎመን ሰፈር ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ካሰች ገብረጊዮርጊስ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት 96 አባወራና እማወራ በመንደሩ ይኖራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ እየኖሩ የጄሪካን ውሃ ከጀርባቸው አልወረደም፡፡ በኩራዝ መብራትም ዕድሜያቸውን እየቆጠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህ ሊሆን የቻለው «ሰነድ አልባ ናችሁ። መስተናገድ አትችሉም» በሚል ሰበብ እንደሆነ ወይዘሮ ካሰች ይገልፃሉ፡፡

«መንግስት ከ1998 .ም በፊት የተሰሩትን ህገወጥ ይዞታዎች በሰነድ አልባ እያስተናገደ ባለበት ወቅት ይህን ሁሉ ዓመት በአካባቢው ኖረን ለዚህ ሁሉ ቤተሰብ ምላሽ መስጠት እንዴት አቃተው? ›› በማለት ጥያቄ አዘል ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ «የመብራትና ውሃ ችግሩ በቅድሚያ ይፈታ» የሚል ጥያቄ ለወረዳቸው ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ወረዳውም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ አንድ ለአምስት ውሃ እንዲያገኙ ወስኗል፡፡ ሆኖም ባልታወቀ ምክንያት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ውሃ እና መብራት ገብቷል ሲሉ ፍትሀዊነት የጎደለው አሰራር መኖሩን ይጠቁማሉ፡፡

የአካባቢ ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ተክለማርያም ከወረዳ ዘጠኝ ልዩ ስሙ «አለምፀሀይ ድልድይ» የመጡ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት በአካባቢው ከ390 ሺ ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተሰራ የኮብልስቶን ንጣፍ መንገድ አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ መንገዱ ሲሰራ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ መግባት በሌለበት ቦታ ላይ ገብቶ ለዚህ ችግር ዳርጎታል፡፡ በዚህም 70 የሚደርሱ ቱቦዎችም (10 ሺ አምስት መቶ ብር) ግምት ያላቸው የህዝብና የመንግስት ሀብት ያለ አግባብ ለብክነት ተዳርጓል፡፡ ችግሩን የልማት ኮሚቴው በተደጋጋሚ ለወረዳው ቢያሳውቅም ‹‹እናንተን ምንም አይመለከታችሁም›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ፡፡ አያይዘውም በወረዳው ውስጥ መንገድ ላይ የጋራዥ ስራ የሚሰሩትን ባለጋራዦችን ጉዳይ አስመልክቶ ለወረዳው በተደጋጋሚ ጥቆማ ቢደርሰውም ሊፈታ እንዳልቻለ ይገልፃሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ቅሬታዎች የቀረቡት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነበር፡፡ በመድረኩም ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው የሸቀጦች የዋጋ መጨመር፣ የውሃና የመብራት እጦት፣ ለስራ ፈላጊዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ከመመዝገብ ያለፈ ተጠቃሚነት ያለመኖር፣ ሽግግር ያደረጉ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን ቦታቸውን ያለማስለቀቅና ለሌሎች ያለማስተላለፍ ፣ የደሃ ደሃ ቤት አሰጣጥ ፣ በክፍለ ከተማው ባሉ ወረዳዎች ያሉ የመመሪያ አፈፃፀም ልዩነቶች ፣ በተቋማት ምክንያት ባለመናበብ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ብክነቶች፣ ያለአግባብ የህዝብና የመንግስት ንብረት የሆነውን መሬት ማስተላለፍ እና ተያያዥ ችግሮች ከነዋሪው ቀርበዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙላት ቡሉላ እንደገለፁት፤ ከወረዳው የተነሳው የ 96 አባወራዎች ጥያቄ ተገቢነት አለው፡፡ አባወራዎቹ ከሶስት መቶ በላይ ቤተሰቦችን የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡ ከነዋሪዎቹ የተነሳውን ጥያቄ ወረዳው ተመልክቶ መረጃቸውን ሲያጣራ ሰነድ አልባ እንደሆኑ ታውቋል። ሆኖም ግን ውሃና መብራት ሊያገኙ እንደሚገባ በማመን ወረዳው ለሚመለከተው አካል ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ እንደቀረ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መሀል ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወረዳው ጋር ምንም መረጃ ሳይኖር ለተወሰኑት ውሃና መብራት እንደገባም ይገልፃሉ፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ቀጣይ የማጥራት ስራ ወረዳው እንደሚሰራ አቶ ሙላት ቃል ገብተዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ ወረዳ ዘጠኝ ላይ የተሰራው ኮብልስቶን የጥራት ጉድለት እንዳለበት አምነዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሳው ጥያቄም ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ በቀጣይ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከመንገድ ላይ ጋራዥ ጋር ተያይዞም የተወሰደው እርምጃ በቂ ነው ባይባልም ግለሰቦቹን የማወያየትና በደንብ ማስከበር እርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ ይህን መሰል የመፍትሄ እርምጃዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

እንዲሁም ከነዋሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ጥያቄዎች ትክክለኛና መሰረታዊነት ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይም ችግሮቹን በፍጥነት እርምት መውሰድ ላይ ክፍተት መኖሩን አምነዋል፡፡ በቀጣይም ከነዋሪዎች የተነሱትን ጥያቄዎች እንደ ችግሩ መጠን ቅድሚያ በመስጠት በየደረጃው ባለው በወረዳ ፣ በክፍለ ከተማ እንዲሁም በራሱ በህብረተሰቡ መፈታት ያለባቸውን በመለየት እንደሚፈቱ ገልፀዋል፡፡ ethpress

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy