Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ“…መንግሥት አሰራቸው” ነገረ- ዲስኩር

0 416

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ“…መንግሥት አሰራቸው” ነገረ- ዲስኩር (ዘአማን በላይ)

ይህ የማወጋችሁ ጉዳይ መነሻው የአንድ ወዳጄ ነው። ቦታው በአንድ የኦሮሚያ አካባቢ ነው—ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነ። ነገሩም ወዲህ ነው።…አንድ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ አባል ሚስታቸውን ክፉኛ ይደበድቧቸዋል። ከባድ ጉዳትም ያደርጉባቸዋል— የግራ አይናቸውን ከጥቅም ውጪ በማድረግ። ተበዳይ ሚስትም ሁኔታውን በአካባቢው ለሚገኘው የሴቶች ጉዳይ ፅህፈት ቤት ያስረዱና “የፍትህ ያለህ…ህግ ይፍረደኝ!” በማለት ‘አቤት’ ይላሉ። ታዲያ ፅህፈት ቤቱ ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ ያስተላልፈዋል። ዐቃቤ ህግም ጉዳዩን ባለቤት ለሆነው ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ያቀርባል— ድርጊቱ ሲፈፀም የነበሩ የዓይን እማኞችን በመቁጠር።    

ተከሳሽ ባልም ህግ ፊት ቀረቡ። ዳኞች የእምነት ክህደት ቃል ተቀበሉ። የክሱን ጭብጥ መረመሩ፡፡ የግራና ቀኙን ክርክርም በጥሞና አደመጡ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ተከሳሹ ላይ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ብይን ሰጡ፡፡….ታዲያ የወጉ ባለቤት የሆነው ወዳጄ በዳኞቹ የተሰጠው የጥፋተኝነት ብይን አላስደመመውም። ይልቁንም አግራሞት ያጫረበት ጉዳይ በባለቤታቸው ላይ አካል የማጉደል ወንጀል የፈፀሙትን ታሳሪ ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት ሲሄድ ግለሰቡ የሰጡት ምላሽ ነው። ፍርደኛው ባልም ለወዳጄ እንዲህ አሉት—“ለመታሰሬ ምክንያቱ መንግሥት ነው።”….

እርግጥም ይህን ምላሽ ያዳመጠው ወዳጄ ጆሮውን ማመን አልቻለም። ደግሞም ጠየቃቸው። ሰለሰም። ግለሰቡ ግን ‘ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ’ በማለትየሰጡት ምላሽ አንድ ብቻ ነው። እናም ደጋግመው የታሰሩበትን “ጥብቅ ምስጢር” ወደ ጠያቂያቸው ወዳጄ ጆሮ ቀረብ በማለት ተናገሩ—ለመታሰራቸው ምክንያት መንግስት መሆኑን አፅንኦት በመስጠት። ምንም እንኳን ይህን ፅሑፍ የሚያነብ ሰው ወጉን ለምን እንዳነሳሁት ሊገምት ቢችልም፤ ወጉን አስታውሼ ለፅሑፌ መንደርደርያ ያደረግኩት ግን ጭፍን ጥላቻ ምን ያህል ርቀት ሊጓዝ እንደሚችል ለማሳየት መሆኑን መገንዘቡ አይቀርም።

አዎ! መንግስት በባልና ሚስት የግል ጠብ ውስጥ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊገባ አይችልም። የጭፍን ጥላቻ መንገድ ግን ሚዛናዊነትን አያውቅም። ይሉኝታም የለውም። ጥላቻውን መግለፅ እስከቻለ ድረስ ሁሉንም ነገር በተጠይው ላይ ለማላከክ ወደ ኋላ አይልም። እንዲህ ዓይነቱ ሁሉንም ነገር በመንግስት ላይ የመደምደም አባዜ ያለባቸው ሰዎች በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ በአጋጣሚ መንገድ ላይ እንቅፋት ቢመታቸው፤ መንግስት እንቅፋቱ እንዲመታቸው ሆን ብሎ መንገድ ላይ ያስቀመጠው የሚመስላቸው ናቸው። እርግጥም “…የመንግሥት አሳሰረኝ ወይም አሳሰረው” ትረካ ከዚህም አልፎ ባህር በመሻገር ለፅንፈኞች የአሉባልታ ማድመቂያና በመሆን ሲነገር መስማትና ማንበብ አዲስ ነገር አይደለም። በየቀኑ የምንሰማው ዕውነታ ነውና።

ይህ የ“…መንግሥት አሰራቸው” ልቦለዳዊ ትርክት ነገር ወደ ፕሬሱ ዓለም ጋዜጠኞች ሲመነዘር፤ ጋዜጠኞቹ የትኛውንም ህግ ተላልፈው ቢገኙ ጥፋታቸውን ለመሸሸግ “…መንግሥት አሳሰረኝ” ይላሉ።… ራሳቸውን ‘አምኒስቲ አነትርናሽናል’፣ ‘ሂዩማን ራይትስ ዎች’፣ “ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ’…ወዘተ እያሉ ለሚጠሩ ተቋማት። በህግ ጥላ ስር ያሉት ጋዜጠኞችም ለጠያቂዎቻቸውና ምናልባትም በሚዲያ ሙያቸው የሀገሪቱን ህጎች እንዲተላለፉ ለሚገፋፏቸው ለእነዚህ ፅንፈኛ ተቋማትም ወደ ጆሯቸው ቀረብ በማለት “የመንገስትን አሳሪነት” ይነግሯቸዋል።

ታዲያ እነዚህ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው፣ በተለያዩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ስም የሚንቀሳቀሱና ለሰዎች በአጠቃላይ፣ ለጋዜጠኞች ደግሞ በተለይ ቆመናል በማለት በክቡሩ የሰው ልጅ ስም ለመቆመር በሚሹ “የርዕዩተ-ዓለም ሲራራ ነጋዴዎች” ይህን “ጥብቅ ምስጢር” በመያዝ በመንግስት ላይ በዙር የቅብብሎሽ ሪፖርት ጋጋታን ያዥጎደጉዳሉ—“…መንግሥት አሰራቸው” እያሉ። ጉዳዩን ይበልጥ ለማሳመርም ‘መንግሥት ሆን ብሎ የሀገሪቱን የፕሬስ ነፃነቱን እያፈነው ነው’ የሚል እውነት መሳይ ቅጥፈትንም ያክላሉ።

ግና ይህ በየሁለት ወሩ፣ ከበዛም በየሶስት ወሩ እንደ ቤተክርስቲያን ስዕለት በእነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች የሚቀርበው ‘የፕሬስ ነፃነት ታፈነ’ ነገር ምላሽ የሚያስፈልገው ይመስለኛል። የ“መንግስት አሰራቸው” ነገር ማጠንጠኛው ይኽው ሀገሪቱ ያላፈነችው የፕሬስ ነፃነት ነውና። እናም ወደ እውነታው ጓዳ በሚከተለው ሁኔታ መዝለቅ፤ የባለቤታቸውን አካል በድብደባ እንዳጎደሉት ሰውዬ ‘ለእስር ሁሉ ምክንያቱ መንግሥት ነው’ የሚለውን ርዕዩተ-ዓለማዊ ጭፍን ጥላቻ ያስተካክለዋል ብዬ አስባለሁ።  

የታሪክ ድርሳኖች እንደሚያስረዱት ሀገራችን ካሳለፈቻቸው መንግሥታት ውስጥ፤ እንደ ዛሬው የኢፌዴሪ መንግሥት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ህገ-መንግሥታዊ ዋስትና እንዲኖረው የታገለና እውን እንዲሆንም ያደረገ ማንም የለም። ያለፉት መንግስታት በባህሪያቸው ፊውዳላዊና አምባገኖች በመሆናቸው ‘የፕሬስ ነፃነት’ የሚለው ቃል የሚያስደነግጣቸው ናቸው። እናም እንደ ኢፌዴሪ መንግስት ለፕሬሱ የነፃነት አውድ የታገለ፣ በተግባርም ነፃነቱ በዴክራሲያዊ መንገድ በሀገራችን ውስጥ እውን እንዲሆን በህ መንግስቱ ውስጥ ተካትቶ ዋስትና እንዲያገኝ ያደረገ የመንግሥት አወቃቀር አልታየም። እናም ይህን የፕሬስ ነፃነት ምህዳር እውን ያደረገ መንግሥት እንደምን ፕሬሱን ሊያፍን እንደሚችል ግልፅ አይደለም።   

በእኔ እምነት መንግሥት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግባራዊ ከሚሆንባቸው ወሳኝ መድረኮች አንዱ ፕሬስ መሆኑን የሚያምን ይመስለኛል። ለተፈፃሚነቱም በቁርጠኝነት እንደሚተጋም እንዲሁ። ከሁሉም በላይ የዜግነት መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግና በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሐራዊ መግባባት ለመፍጠር ፕሬስ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑንም መረዳቱ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ ያከናወናቸው ተግባራት እነዚህን ሃቆች የሚያረጋግጡ ናቸውና። ይህ ማለት ግን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም—እንደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጀማሪነታችን ተግዳሮቶች መኖራቸው የሚቀር አይደለም። ሆኖም እስካሁን የተሄደው ርቀት መንግስትን የሚያስመሰግነው እንጂ፤ በጭፍን ጥላቻ መንፈስ “ፕሬስን አፈነ’ የሚያስብለው አይመስለኝም።

ታዲያ እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ዕውነታን ማንሳት የሚገባ ይመስለኛል። ይኽውም ፕሬስ በባህሪው የዴሞክራሲ ስርዓትን በመገንባት ረገድ ሊጫወት የሚችለው ከፍተኛና በጎ ሚና የመኖሩን ያህል፤ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ዓላማዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ነው። የኃላፊነት መንፈስ የማይሰማቸው አንዳንድ የፕሬስ ውጤቶች የህዝቦችን ኋላቀር ስሜቶች በመኮርኮት፣ ነገሮችን በማጋነን ወይም ፈጥሮ በማውራት መተላለቅን ለመፍጠር እንደሚችሉ ሩዋንዳ ውስጥ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈተ-ህይወት ከዳረገው “ሬዲዮ ፍራንሲስ ኮሊንስ” ብዙ መማር የሚቻል ይመስኛል። ይህ የሬድዮ ጣቢያ የዚያች ሀገር ዜጎችን በመከፋፈልና እርስ በርስ በማጋጨት ለዘግናኝ እልቂት እንደዳረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነውና።

ያም ሆኖ ፕሬስ በባህሪው ይህን መሰሉ ችግር ያለበት መሆኑ ቢታወቅም፤ መንግስት ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ በዘርፉ ሊፈጠር የሚችል ጉዳትን ለማስቀረት ሲል ጥቅሙን የሚገድብ አቅጣጫን አልተከተለም። ላድርግ ቢልም አይችልም—ህገ መንግስቱ ያግደዋልና። ከዚህ ይልቅ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ነፃና ጤናማ ፕሬስ እውን እንዲሆንና በዚህም የበሰለ ዴክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ብዙ ርቀት ተጉዟል። የዳበሩና ኃላፊነት የሚሰማቸው የግልና የመንግሥት ፕሬሶች እንዲኖሩ ለማድረግ የተካሄደው ሁለንተናዊ ጥረት የዚህ አባባሌ አስረጅ ነው። በፕሬስ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በቂና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ፣ ስራቸውንም ነፃና ጤናማ በሆነ አኳኋን እንዲያከናውኑ ለማስቻል የወጡ አዋጆች የጥረቱ ተጠቃሽ አንድ አካል ነው።

እርግጥ ይህን መሰሉ የሀገራችን ፕሬሶች ነፃና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉና እንዲጎለብቱ በመንግሥት በኩል የሚወስዱት ቁርጠኛ አቋሞች፤ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስር እንዲሰድ ታልሞ የሚከናወን መሆኑን ለአፍታም ቢሆም ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ሆኖም አሁንም የሚቀሩ ስራ መኖራቸው አይታበይም። መንግሥት በተለይም ከግሉ ፕሬስ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ዴሞክራሲውን ለማጥለቅ ይበልጥ መትጋት ይኖርበታል። በእኔ እምነት ይህ የግሉ ፕሬስና የመንግስት ቅርርብ ምናልባትም የ“…መንግሥት አሳሰራቸው”ን ነገረ ትረካ ሊያስቀር ይችላል። እናም በቀጣዩቹ ጊዜያት መንግስት ለሌሎች የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎች ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ መልኩ ለፕሬሱም አትኩሮት ሊሰጥ የሚገባ ይመስለኛል።  

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግሥት ከባህሪው በመነጨ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲያብቡና እንዲፈኩ የሚረባረብ እንጂ፣ እንዲጠወልጉ የሚሰራ አይመስለኝም። ራሱ እውን እንዲሆን የታገለለትን ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብት መልሶ የሚደፈጥጥበት ባህሪያዊ ተፈጥሮም ሆነ እምነት ያለው አይመስለኝም። በመሆኑም ‘መንግስት የፕሬስ ነፃነትን ያፍናል’ የሚለው ርዕዩተ-ዓለማዊ ልቦለድ፤ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸውና የሚስታቸውን አካል አጉድለው በህግ ጥላ ስር ከዋሉት ግለሰብ “ለመታሰሬ ምክንያቱ መንግስት ነው” ከሚለው የአራምባና ቆቦ “ምስጢራቸው” ተለይቶ የሚታይ የሚችል አይደለም።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy