Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማስረጃ ያለህ

0 441

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥር 1 ቀን 2009 .ም በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ዘንድ በሌብነት የሚገለጽ ብልሹነት መኖሩን አንስተው፤ «ባገኘነው ማስረጃ ልክ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ በወሬ እርምጃ አይወሰድም፡፡ ሰው ለማሰር ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎችም ማስረጃ እያለን አላሠራችሁም የምትሉ ከሆነ ፈትኑን» ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ፤ መንግሥት ከፍተኛ አመራሩን ተጠያቂ ለማድረግ የዋናው ኦዲተር፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርቶችን በመጠቀም በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በኩል ለመሥራት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ምሁራን ከፍተኛ አመራሩን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በዚህ ደረጃ መንግሥት መዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን በመግለፅ፤ በቂ ማስረጃ የለም ማለት ግን የቁጥጥር ሥርዓት አልተዘረጋም፤ ተጠያቂነት የለም ማለት ስለሆነ መንግሥት አለኝ የሚላቸውን መረጃዎች ወደ ማስረጃ በመቀየር ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል የሚል መከራከሪያ እያነሱ ናቸው፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋካልቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር መሀሪ ረዳይ፤ ህብረተሰቡ ከየአቅጣጫው የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ተንተርሶ መርምሮና የሚገኙትን ጥቃቅን መረጃዎች ገጣጥሞ ወደ ማስረጃ በመቀየር ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል ይላሉ። ማስረጃ ስለሌለኝ ተጠያቂ አላደርግም ማለትም ለዶክተር መሀሪ ትክክለኛ ድምደሜ አይደለም፡፡ ምክንያታቸውም አሉ የተባሉት መረጃዎች ማስረጃ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነውና የሚል ነው፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ ደግሞ፤ መረጃ እንጂ ማስረጃ የለንም ማለት መንግሥት ሹመኞቹን የሚጠይቅበት ሥርዓት አላበጀም፤ ተጠያቂነት ያለው ሥርዓትም አልፈጠርንም ብሎ መናገር ስለሆነ አሳማኝ መከራከሪያ ነው ብሎ መቀበል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚገልጹት፡፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባርና ሥነዜጋ መምህሩ አቶ ደባ ዱቤም ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው፡፡ እርሳቸው እንደተናገሩትም፤ መረጃ ከተገኘ ማስረጃ ማግኘት ቀላል ነው። ነገር ግን በፖለቲካ አመራሩ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ምንጊዜም ተጽዕኖ ፈጠሪ ስለሆኑ ተቋማት ተጠያቂ እንዳያደርጓቸው ጫና ያሳድራሉ። መንግሥት በሹመኞቹ ላይ ማስረጃ ካላገኘ አገሪቱ አደጋ፤ ተቋማቱም በጥያቄ ውስጥ ናቸው ማለት ነው፡፡ ማስረጃ ስለሌለ መጠየቅ አልተቻለም ማለት ህዝቡን ተስፋ ማስቆረጥ እንዳይሆንም ያሰጋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ መምህርና የቢዝነስና ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞላ ረዳም፤ መረጃ እንጂ ማስረጃ የለም ማለት ዋና ኦዲተር፣ የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሚዲያዎች የሉም ማለት እንደሆነ በመግለጽ፤ እነዚህ ተቋማት ደግሞ እስከነጉድለታቸውም ቢሆን የተቻላቸውን እየሠሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም የእነሱን የሥራ ውጤት እንደ ማስረጃ ተጠቅሞ ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል የሚል አቋም አላቸው።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ መንግሥት እያለ ያለው ማስረጃ አላገኘንም ሳይሆን ያገኘነውን መረጃ ህዝቡና የሚዲያ ባለሙያዎች በድፍረት ሄደውበት ያጋልጡ ነው። ጋዜጠኞች መንግሥት ያልደረሰባቸውን ማጋለጥ፤ መንግሥት ካገኛቸው መረጃዎችም በላይ አልፈው በመሄድ ማጋለጥ እንዳለባቸው ነው መንግሥት እያሳሰበ ያለው።

በዓለም ተሞክሮ መሰረት፤ ዋናው ኦዲተር ማለት የመንግሥት ሀብት ጠባቂ፣ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት መሥራት አለመሥራቱን የሚፈትሽ የህዝብ ዓይንና ጆሮ የሆነ መንግሥትን ማስቀየር የሚችል ተቋም ነው፡፡ «በእኛ አገር ከዓመት ዓመት በጣም ጉልህ የሆነ ችግር ሪፖርት እየተደረገ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና መንግሥት እርምጃ አልወሰዱም። የኦዲት መጓደል የተገኘበትን ኃላፊም ከኃላፊነት ማውረድ አልቻሉም። ለምንሲሉ የሚጠይቁት የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ጋሼ የማነ ናቸው።

ህግ አዋቂው ዶክተር መሃሪ፤ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ላይ ተመስርቶ ሁሉም ሹመኛ ሙስና ፈጽሟል ብሎ መደምደም አይቻልም ባይ ናቸው፡፡ ነገር ግን በኦዲት ጉድለቱ ላይ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ፤ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተመዘገበውን የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሀብት ተመስርቶ በህጋዊ መንገድ ያገኙት መሆን አለመሆኑን አጣርቶ ተጠያቂ ማድረግ የሚቻልበት እድሉ አለ ይላሉ። ድርጅቱ ችግር አለብኝ ብሎ የገመገመው የበላይ አመራሩ ላይ ሆኖ ሳለ ከቦታ ከማንሳት የዘለለ ለተምሳሌት የሚሆን እርምጃ አለመወሰዱም ተገቢ አይደለም፡፡

አቶ ካህሳይ በበኩላቸው፤ ሙስና ገንዘብ መስረቅ ብቻ አይደለም፤ መንግሥት ለህዝብ ለመሥራት የገባውን ቃል ሳያሳካ ሲቀርም ተጠያቂነት መኖር አለበት ይላሉ። ለልማት ተነሽዎች የተባለውን 100 ሚሊዮን ብር አመራሩ ተከፋፍሎ ከበላ መንግሥት የቁጥጥር ሥርዓት የለውም ማለት ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ሹመኛና የተራ አስፈፀሚው ልዩነት በግልጽ ተቀምጦ አሰራርን በትክክል ተግባራዊ ማድረግ፣ የፖሊሲዎችን አፈፃፀም መለኪያ ማበጀት ይገባል ባይ ናቸው። ይሄ ሲሆንም የጠፋውን ማስረጃ ማግኘት የሚቻለው፡፡

አቶ ደባ ደግሞ፤ የፖለቲካ ውሳኔ የሚሰጡ አካላት እጃቸውን ከዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ማንሳትና ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይፈጽሙ እንቅፋት መሆናቸውን ማቆም አለባቸው፡፡ በህገ መንግሥቱ በተቀመጠው አግባብ ልክ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መፍቀድ ከተቻለ አለ የተባለውን መረጃ በቂ ማስረጃ ማድረግ ይቻላል ነው የሚሉት።

አቶ ሞላ ደግሞ፤ በአገር ደህንነት ላይ እንደሚሠራው ሁሉ የኢኮኖሚ ደህንነት ላይ መሥራት ይገባል ባይ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ጠንካራ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና ህብረተሰቡ ውስጥ በአቋራጭ የመበልጸግ አስተሳሰብ በማደጉ በመሆኑ ይህን የሚቀርፍ ሥራ ከተሠራ የጠፋውን ማስረጃ ማግኘት ይቻላል ሲሉ መክረዋል።

ዶክተር ነገሪ በበኩላቸው፤ መረጃ የተገኘ ባቸውና ተጠርጣሪ የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በዋናው ኦዲተርና ሌሎች ተቋማት ማስረጃዎች ላይ በመመስረት ክስ እንዲመሰርት ለዓቃቤ ህግ ኃላፊነት ተሰጥቷል። መንግሥት ያለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅሞ በዘረጋቸው የምርመራ ሥርዓቶች ተጠያቂ ለማድረግ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ዶክተር ነገሪ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሚኒስትሮችንም ለመጠየቅ መንግሥት ዝግጅቱ እንዳለው የገለጹትም ከዚህ ቀደምም መከሰሳቸውን ለአብነት በማንሳት ነው፡፡ አሁንም ለጥንቃቄ ሲባል ስም አልተገለጸም እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ በኢህአዴግ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ይህን በመከታተል ይፋ ማድረግ የጋዜጠኞች ሥራ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ምንም እርምጃ አልተወሰደም የሚለው መከራከሪያ አያስማማም። ሂደቱም ስላላለቀ ዋንጫው እስኪሞላ መጠበቅ ይገባል። ዙሪያቸው የተከበበ ብዙ አመራሮች አሉ ሲሉ ነው ያስታወቁት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy