Artcles

የምስራች ለዓባይ ልጆች!

By Admin

March 31, 2017

የዓባይ ተፋሰስ፤ ለመላው የባለድርሻ ሀገራት ህዝቦች የስጋትና ያለመተማመን ምንጭ ሆኖ ስለመቆየቱ ብዙ ተብሏል፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሁሉም የባለድርሻ ሀገራት ህዝቦች በተለየ መልኩ የቁጭትና የቁዘማ ምንጫችን የዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብታችንን ትርጉም ላለው የልማት ተግባር ማዋል ሳንችል መቆየታችን እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በከዚህም ፤ ስለታላቁ የዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብታችንና ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ የሚገባትን ጥቅም ሳይሰጣት ስለመቆየቱ በሚያወሳ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ፤ የየራሳቸውን ቁጭት ለመግለጽ ያለመ ኪነ-ጥበባዊ ስራ ያቀረቡልን ከያኒያን  ጥቂት እንዳልነበሩ ማስታወስ አይገድም፡፡ በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ እንደሚገነባ ይፋ እስከተደረገበት እለት ድረስ፤ ባለው  የሀገርቱ ህዝቦች የጋራ ታሪክ ውስጥ፤ የተፃፈ ዓባይ ነክ ግጥሞችንም ሆነ የተቀነቀኑ ዜማዎችን ሁሉ እያነሳን ብንመረምራቸው ፤ በእርግጥም ጉዳዩ ስር የሰደደ የብሔራዊ ቁጭት ምንጭ ሆኖብን ስለመቆየቱ የተሻለ ግንዛቤ የሚያስጨብጠንን የኪነ-ጥበብ ሰዎቻችን ምስክርነት እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ለማንኛውም ግን፤ ከዚሁ ለዘመናት በዘለቀው የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ታሪክ ቁጭታችን ምንጭ ሆኖ ከቆየው የዓባይ ተፋሰስ የውሃ ሀብታችን ጋር በተያያዘ መልኩ የተለያዩ የሀገራችን ከያኒያን የፃፏቸውን ግጥሞችና እንዲሁም ደግሞ ድምጻዊያን ያዜሟቸውን የቁዘማ መንፈስ ያጠላባቸው የስነ ጽሁፍ ስራዎች በዝርዝር መጥቀስ ስለሚከብድ፤ እኔ ከማስታውሳቸው መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ለአብነት ያህል አንስተን እንመለከት ዘነድ መርጫለሁ፡፡ በዚህ መሠረትም፤ ከአንጋፋዎቹ ኢትዮጵያዊያን ታዋቂ ከያኒያን፤ በተለይም ስመ ጥሩ የሀገራችን ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ዓባይ” በሚል ርዕስ የፃፈውና “እሳት ወይ አበባ” የተሰኘ ተወዳጅ የስነ ግጥም መድብሉ ውስጥ አሰባስቦ በ1950ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ካሳተማቸው ሥራዎቹ አንዱ የሆነው ዘመን አይሽሬ ግጥም ለጉዳያችን እንደቀዳሚ ማጣቀሻ ሊወሰድ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲሁም ደግሞ የዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብታችን ባክኖ መቅረት የፈጠረባቸውን እጅግ በጣም ጥልቅ ቁጭት የሚገልፅ መሰል ዘመን ተሻጋሪ የግጥም ስራ ካበረከቱልን ወጣት የሀገራችን ከያኒያን መካከል በዕውቀቱ ስዩም “ምስጢረ ህላዌ” ሲል ርዕስ በሰጠውና የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም ካሳተማቸው ስብስብ ግጥሞቹ ጋር አካትቶ ያወጣው ድንቅ ስራ የተሻለ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚሰማኝ፡፡

ሌላው ይህን ርዕሰ ጉዳይ ካነሳን አይቀር ሳናወሳው ማለፍ የማይኖርብን የዓባይ ነክ ቁጭት አዘል ግጥሞችን ደጋግሞ የፃፈ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ ደግሞ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን አንጋፋ ጋዜጠኛ ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱ ነው፡፡ ኮሎኔል ሞገስ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የብአዴን ኢህአዴግ ታጋይ ሆኖ ጎጃም ባህር ሲኖር “”ዓባይ ጠላ ቢሆን” እና “ማንኛችን ነን ሰው?” በሚል ርዕስ የፃፋቸውን ሁለት አጫጭር፤ ግን ደግሞ ሀገሩን የሚነቀንቅ ነጎድጓዳዊ የቁጭት ስሜት የተስተጋባባቸው ግጥሞቹን “ፍልሚያ” የተሰኘ መድብሉ ውስጥ አካቶ እንዳሳተማቸው አይዘነጋም፡፡

ይህ እንግዲህ በመፀሐፍ መልክ ታትመው ከሚገኙት የሁለት ሦስት ኢትዮጵያዊ ትውልድ ዘመን ገጣሚያን ፤ የዓባይ ወንዝ ውሃ ሀብታችን ያለ ምንም ጥቅም ሲፈስ ማየት የፈጠረባቸውን  ቁጭት ለመተንፈስ ሲሉ ስንኝ ከቋጠሩባቸው የስነ ግጥም ስራዎች መካከል በጣት የሚቆጠሩትን ብቻ ያወሳንበት ምሳሌ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ እንጂ ስለ ዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብታችን የምድረ በዳ ሲሳይ ሆኖ መኖር የተሰማውን ቁጭት በስንኝ ቋጠሮ ለመግለፅ ያልሞከረ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ አለ እንዴ? እንዲሁም በርካታ የሀገራችን ድምፃዊያንም፤ በየራሳቸው የዘመን መንፈስ ከተቃኘ የሙዚቃ ቅንብር ጋር እያጣጣሙ ያዜሟቸው መሰል የብሔራዊ ቁጭት መገለጫ ግጥሞች እንዳሉ ፀሐይ የሞቀው ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ እኔ በዚህ ረገድ ለአብነት ያህል ቢቀርብ የመጣጥፌ ማጠንጠኛ ለሆነው ርዕሰ ጉዳይ ጥሩ ማጣቀሻ ይወጣዋል የምለው ዘመናዊ ሙዚቃ ስራም በተለይ እጅጋየሁ ሺባባው (ጂ.ጂ) “ዓባይ” በሚል ርዕስ ያዜመችውን ምርጥ ዘፈን ነው፡፡

ይህን የምልበት መሠረታዊ ምክንያትም፤ ተወዳጇ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሺባባው፤ በተጠቃሹ ዜማዋ “ዓባይ-ዓባይ የበረሀው ሲሳይ…..” የሚል አዝማች ያለውንና እርሷም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ በጉዳዩ እንቆቅልሽ ሆኖ መኖር ቆሽቷ ማረሩን በሚያመለክት ተስረቅራቂ ቃና የምታቀነቅነውን ግጥም ልብ ብሎ ለሚሰማው ሰው የታላቁ ወንዛችን ውሃ ለዚች ሀገር ህዝቦች ብርቱ ስጋት  ጭምር ሆኖብን እንደኖረ ይገለፅለታልና ነው፡፡ እንዴት? የሚል አንባቢ ካለም ደግሞ፤ ጂ.ጂ ለ3ኛ ጊዜ ባሳተመችው የሙዚቃ አልበሟ ላይ ስለታላቁ የዓባይ ተፋሰስ ውሃና ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ጋር በጥብቅ እንዲቆራኝ ስለሚያደርገው መልክአምድራዊ እውነታ፤ ብሎም ታሪካዊ ዳራ ጭምር ጥልቀት ባለው መልኩ የሚያወሱ የግጥም ስንኞቿን የምታቀነቅንበት የድምፅ ቅላፄ ምን ዓይነት ልዩ ስሜት እንደሚያጭር ያልገባው ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡

ዓባይ፤ ዓባይ….

የበረሀው ሲሳይ፤

ዓባይ ወንዛ ወንዙ፤

ብዙነው መዘዙ……

እያለች ድምፃዊቷ ጉዳዩ ለእኛ ለኢትጵያውያን ህዝቦች ብርቱ ስጋት አዘል ቁጭት ምንም እንደሆነ ዘመናትን የማስቆጠሩ ምክንያት፤ ምን ዓይነት አንድምታ እንዳዘለ የሚያጠያይቅ ይዘት ባለው ድግግሞሽ የምታቀነቅናቸውን የግጥም ስንኖች ብቻ እንኳ እስቲ በጥሞና እናድምጣቸው? መቼስ የናንተን ባለውቅም ለእኔ ግን ዓባይን ፈፅሞ የማይነካ አስፈሪ ነገር አድርጎ ከመውሰድ የሚመነጭ “ ጎመን በጤና እቴ!” እንደማለት አይነት ፍርሃት እንዲጋባብን የሚጋብዝ ቁዘማ ነው ከዚህ የጂጂ ሙዚቃ ቅኝት ውስጥ ጎልቶ የሚሰማኝ፡፡

ለነገሩ ማኮ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በነበረው ታሪካችን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍል “ዓባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ” የሚለውን ብርቱ ስጋት ያዘለ ሀሳብ አምኖ እንደሚቀበል የሚያመለክትና በተለይም ግብፆች እንኳንስ ዓባይን ስለመገደብ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ለማሰብም ዕድል ሊሰጡን እንደማይችሉ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር ማስታወስ አያዳግትም፡፡ በእርግጥም ደግሞ ቀደም ባለው ታሪካችን ውስጥ የነበሩት የሀገራችን መንግስታት ጭምር፤ ኢትዮጵያን የዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብቷን ገድባ ለህዝቦቿ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በሚሰጥ የልማት ተግባር ላይ እንዳታውል ያደረጋት ምክንያት እንደነ ግብጽ ዓይነቶቹ የተፋሰስ ባለድርሻ ሀገራት የሚፈጥሩብን ፈርጀ ብዙ አሉታዊ ተጽእኖ ነው ብለን እንድናምን የሚያደርገንን የአይቻልም ፕሮፖጋንዳቸውን ሲግቱን ነው የኖሩት፡፡ እናም እኔን ራሴን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ “ጎመን በጤና” እንደማለት ለሚቆጠር የተሸናፊነት መንፈስ እጅ መስጠትን መርጦ መቆየቱ የማይስተባበል ሀቅ ነው፡፡

ከዚሁ ብርቱ ስጋታችን የተነሳም፤ የፊደል ዘር የመቁጠር ዕድል ያልገጠመው አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህብረተሰባችን ሳይቀር፤ ከዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብታችን ተጠቃሚ ሳንሆን በመቅረታችን የሚሰማውን ጥልቅ ቁጭት ለመግለፅ ሲሞክር የሚደመጥባቸው አፋዊ ግጥሞችና ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሁሉ፤ አንዳች የስጋት ስሜትን ያዘሉ ሆነው እንደቆዩ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ልክ የዛሬ ስድስት ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በዓባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ካስቀመጡ በኋላ ባሰሙት ታሪካዊ ንግግር “ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከዓባይ ተፋሰስ መጠነ ሰፊ የውሃ ሀብቷ ተጠቃሚ ሳትሆን የቆየችው በተለይም የኢኮኖሚ አቅሟ ደካማ ስለነበርና የውጭ እገዛ እንዲደረግላት ለባለፀጋዎቹ ሀገራት የምታቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያጣ በሌሎች ተፅዕኖ ይደረግብን ስለነበር እንደሆነ ባይካድም፤ እኛ ራሳችን ጉዳዩን ፈጽሞ የማይሞከር ነው ወደሚል ድምዳሜ በሚያደርስ ፍርሃት ውስጥ መግባታችንም ግን የማይናቅ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል” ብለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚያው ጉባ ሸለቆ ላይ ተገኝተው ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ካኖሩ በኋላ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸው “ስለዚህ የሀገራችን አንጡራ ሀብት የሆነውን የዓባይ ወንዝ ውሃ አልምተን ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጠን ለማድረግ እንድንችል የመጀመሪያው ከኛ የሚጠበቅ እርምጃ መሆን ያለበት ጉዳይ አላስፈላጊ ፍርሃት ማስወገድ የሚል ፅኑ እምነት አለኝ” ሲሉ መደመጣቸውም አይዘነጋም፡፡ የእርሳቸውን ምክር ያለአንዳች ማቅማማት ተቀብሎ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ በራስ አቅም ስለመገንባት ጉዳይ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር የቻለው ህዝባችንም ታዲያ ፕሮጀክቱ ሲጀመር ለአቶ መለስ የገባውን ክቡር ቃል አላጠፈም፡፡

እነሆ በዓባይ ወንዝ ላይ የዛሬ ስድስት ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ያስቀመጡትን የመሰረት ድንጋይ ተከትሎ ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ፤ አሁን ስራው እየተፋጠነ መሆኑ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችም ጭምር ምስክርነታቸውን ሲሰጡ የሚደመጡት፡፡ ስለዚህ እኔም የመጣጥፌን ርዕስ የምስራች ለዓባይ ወንዝ ልጆች ልለው የመረጥኩት ያለምክንያት እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ይልቁንም በቀደመው የዘመናት ታሪካችን፤ መላውን የቀጠናው ሀገራት ህዝቦች “ዓባይ ወንዛ ወንዙ፤ ብዙ ነው መዘዙ” የሚያሰኝ አላስፈላጊ ስጋትና ፍጥጫ በፈጠረው አለመተማመን የጎሪጥ እየተያየን ከኖርንበት የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ቆፈን ያላቀቀና በአፍሪካዊ የወንድማማችነት መንፈስ አብሮ የማደግ (የመበልፀግ) አዲስ ምዕራፍ ስለመክፈቱ መገንዘብ አያዳግትምና ነው፡፡

ስለሆነም፤ ይህን አስተያየቴን ይበልጥ ለማስረገጥ ይረዳኝ ዘንድ፤  የኢፌዲሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ካሰሙት ንግግር መካከል፤ ጥቂት ጠቃሚ ነጥቦችን እጠቅሳለሁ፡፡

በዚህ መሰረትም አቶ ኃይለማርያም ሰኞ ዕለት የአዲስ አበባ መስተዳድር እንዳዘጋጀው በተነገረለት መድረክ ለተገኘው በርካታ የመዲናችን ነዋሪ ህብረተሰብ የዘንድሮውን በዓል አስመልክተው ገለፃ ሲያደርጉ….“ታላቁ ግድባችን ለመላው ሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሊሰጥ ስለሚችለው ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፤ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ የፈጣን ልማት ጉዟችንን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችል በቂ የሃይል ምንጭ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም ደግሞ በመላው የሀገራችን ክፍል ለሚገኙ የገጠሪቷ ኢትዮጵያ ነዋሪ ወገኖቻችን የመብራት አገልግሎት ከማዳረስ አኳያ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚታመንና የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ከሚፈጥረው በጣም ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ጋር በተያያዘ ለበርካታ ዜጎቻችን ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ስለሚጠበቀው አዳዲስ የስራ መስክ ወዘተ… ለእናንተ መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ስለሚቆጠርብን እተወዋለሁ” ሲሉ መደመጣቸውን በዚህ አጋጣሚ አስታውሼ ለማለፍ ነው እኔ የፈለግኩት ውድ አንባቢያን፡፡ በተረፈ ግን እንኳን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስድስተኛ ዓመት የግንባታ ሂደት መጀመሪያ አደረሳችሁ አደረሰን፡፡ መዓሰላማት!