Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰማያዊው ጎርፍ መንገደኞች

0 618

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመንግስት ሰራተኞች አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የፐብሊክ ሰርቪስ ማጓጓዣዎች ለብዙሀኑ እያበረከቱት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው።ይህ በመሆኑም የስራ ሰአት በአግባቡ እንዲከበር፣እንግልትና ድካም እንዲቀርና በአላስፈላጊ ወጪዎች ኤኮኖሚ እንዳይቃወስ ጭምር አስተዋጽኦ አበርክቷል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዘወትር ትራንስፖርቱን በሚጠቀሙ ሰራተኞች መሀል እየዳበረ ያለው ማህበራዊ ግንኙነትም የመተሳሰብ ባህልን በማዳበር ላይ ይገኛል።የአዲስ ዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም ጠዋትና ማታ በጉዞ አጋጣሚ የሚገናኙና መልካም ግንኙነት የፈጠሩ ሰራተኞችን አነጋግራ ያለውን ገጽታ እንዲህ ታስቃኘናለች።

 ከሥራ መልስ ወደቤት ለመሄድ ተራ ይዘው ሰርቪስ ከሚጠባበቁት መሀል አብዛኞቹ ወደውስጥ ገብተው ወንበር መያዝ ጀምረዋል። ዘግየት ብለው የደረሱ ሠራተኞችም ከፊት ተቀምጦ ማንነታቸውን ለሚጠይቃቸው ተቆጣጣሪ መታወቂያቸውን እያሳዩ ቀሪዎቹን ወንበሮች ለመጋራት ወደ ኋላ እያለፉ ነው። ሾፌሩ የመንቀሳቀሻ ሰዓታቸው መድረሱን እንዳረጋገጡ ሞተሩን አስነሱ።

እንደተለመደው ጎን ለጎን የተቀመጡ መንገደኞች ጨዋታ ይዘዋል። በወንበር ተቀምጠውና ተረጋግተው ከሚጓዙት ሌላም በየፌርማታው የሚወርዱና የሚገቡ እንዲሁም ቆመው የሚሄዱ ጥቂቶች አይደሉም። ይህ ጉዞ አብዛኞቹ ከሥራ ድካም በኋላ አረፍ የሚሉበት ጭምር ነው። ከተሳፋሪዎቹ ብዙዎቹም የዕለት ውሏቸውንና የሥራ ቆይታቸውን እያነሳሱ ይጨዋወታሉ። በዚህ መንገድ የዓለም ውሎ አዳርን ጨምሮ የቤትና የጓዳው ምስጢር ሳይቀር ይዳሰሳል።

ሰዓቱ የሥራ መውጫ በመሆኑ መንገዱ ተዘጋግቷል። ይህ ክስተት ብዙ ጊዜ የተለመደ ቢሆንም የዛን ዕለት ያገጠመው የመኪኖች ግጭት ደግሞ ከወትሮው በባሰ አዝጋሚ ጉዞ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ሲሆን ራቅ ባሉ አካባቢዎች በታሰበው ሰዓት መድረስ ዘበት ይሆናል። አንዳንዴ ችግሩ ከትራፊኮች አቅም በላይ ይሆንና በርካታ መኪኖችም ጊዜያቸውን በመቆም ሊያሳልፉት ይችላሉ። መነሻውን ስድስት ኪሎ መድረሻውን ደግሞ ጀሞ ያደረገው ሰርቪስ ሠራተኞችን አድርሶ ወደማደሪያው ለመመለስ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም አለበት። ብዙ ጊዜ ግን ይህን ፍላጎት በዚህ ሰዓትና ወደ ጀሞ በሚወስደው መንገድ ላይ ማሳካት ዘበት ሊሆን ይችላል።

የጀሞ ሰርቪስ ተጠቃሚዎች አሰልቺውን መንገድ በጨዋታና በዕንቅልፍ ማጋመሳቸው የተለመደ ነው። የበረቱና የዕንቅልፍ ፍላጎት የሌላቸው ደግሞ በዝምታና በሀሳብ ተውጠው መንገዱን መግፋት ለምደውታል። የዛን ዕለት ከታሰበው በላይ የቆዩና በሰዓቱ ቤታቸው መድረስ ያልቻሉ ስለደህንነታቸው ከቤተሰቦቻቸው የሚደወልላቸውን ስልክ እየተቀበሉ ቆይተዋል። ጥቂት መንገድ የቀራቸውና ቀሪውን ጉዞ በመጨናነቅ ማሳለፍ ያልፈለጉ ደግሞ ከመኪናው እየወረዱ በእግራቸው ተጉዘው ቤታቸው ገብተዋል።

የመካኒሳን መንገድ አልፎ የሚካኤልን አደባባይ በጭንቅ የዞረው የሠራተኞች ሰርቪስ እንደምንም ተጉዞ ከጀሞ አንድ ጫፍ ደርሷል። መጨናነቁ የፈጠረው አጋጣሚ ምሽቱ እንዲያይልና ሰዓቱ እንዲገፋ ቢያስገድድም ሁሉም ከጉዞው ፍጻሜ በመድረሱ እፎይታ ተሰምቶታል። ከዚህ በኋላ የሰርቪሱ ሾፌር ተሳፋሪዎችን አውርደው ወደመጡበት ለመመለስ መፍጠን ይኖርባቸዋል። መንገዱ ዳግም እንዳይዘጋና ከዚህም በላይ እንዳይመሽባቸው የሰጉ ይመስላል። የያዙትን መኪና ወደ ማደሪያው አድርሰው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ደግሞ ተጨማሪ ሰዓትና ጉዞ ይጠበቅባቸዋል። እናም ትልቁን መኪና ከቆመበት አስጓርተው ወደፊት ገሰገሱ።

ሾፌሩ መኪናውን ከማደሪያው አድርሰው ከመውረዳቸው በፊት ውስጡን የመፈተሽ ልምድ አላቸው። ሁሌም መስኮቶች በአግባቡ መዘጋታቸውንና መጋረጃዎች ወደውጭ ያለመቅረታቸውን ያረጋግጣሉ። የዛን ዕለት ምሽትም ከወትሮው በተለየ ሰዓቱ እንደገፋ ቢያውቁም ይቅርብኝ ሲሉ አልተዘናጉም። መብራት አብርተው ከመጀመሪያዎቹ መስኮቶች ተርታ ፍተሻውን ጀመሩ። ጥቂት ወንበሮችን አልፈው ወደ ጥግ ሲደርሱ ግን ዓይናቸው ከመጨረሻዎቹ መቀመጫዎች በአንደኛው ላይ አተኮረ። አልተሳሳቱም። የተመለከቱት የተረሳ ዕቃ አልያም ሌላ ነገር አልነበረም ። ጥግ ተቀምጣ በታላቅ ዕንቅልፍ ውስጥ የነበረችን ሴት እንጂ።

በተመለከቱት እውነት የደነገጡት አሽከርካሪ ራሳቸውን አረጋግተው ሊቀሰቅሷት ተጠጉ። በከባድ ዕንቅልፍ መውደቋና ከሌሎች ተነጥላ መቅረቷ እጅግ ቢያስገርማቸውም ይበልጥ የደነቃቸው ግን ወንበሩ ላይ የነበረችው ሴት ዓይነስውር መሆኗ ነበር። ይህን ያረጋገጡት ሾፌር በሆነው ሁሉ ቢያዝኑም እንደመፍትሄ የወሰዱት አማራጭ ይህቺን ሴት የምሽት ዕንግዳቸው አድርገው ወደ ቤተሰቦቻቸው መውሰድን ነበር። ይህ አጋጣሚ ከአንድ ዓመት በፊት በጀሞ የሰርቪስ ተጠቃሚ የመንግሥት ሠራተኞች ዘንድ በስፋት ሲወራ ከርሟል። የሾፌሩ ቅንነትና የቤተሰቦቻቸው መልካምነትም እንዲሁ።

ወይዘሮ አሰገደች እንድሪስ በሥራ በቆየችባቸው ዓመታት በርካታ ውጣ ውረድን አልፋለች። ወደ ሥራዋ ለመሄድ በማለዳ መውጣትና ትራንስፖርት መጠበቅ ግዴታዋ ነበር። ታክሲ ለመያዝና ከሌሎች ጋር እኩል ለመጋፋት ደግሞ እንደሷ ላለ ዓይነስውር መንገደኛ እጅግ ከባድ የሚባል ፈተና ነው። ነጋ አልነጋ ስትል በማለዳ የምትወጣው አሰገደች በሰዓቱ መድረስ ሳይቻላት ቀርቶ አርፍዳ የምትደርስባቸው ቀናት የበረከቱ ነበሩ። ብዙ ጊዜ በምትጠቀምበት የከተማ አውቶቡስ ረጅሙን መንገድ ቆሞ መሄድ ለእሷ ቀላል የሚበል አይደለም። ከሥራ መልስ ወደ ቤት ለመግባትም በተመሳሳይ ችግር ማለፍ ግድ ይላታል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ምሽት በድካም ዝላ ቤቷ ስትደርስም ለምታስተዳድረው ቤተሰብና ጎድሎ ለሚጠብቃት ጓዳዋ ሌላ ኃላፊነትን መወጣት የዕለት ተዕለት ግዴታዋ ነበር።

ዛሬ አሰገደች ያንን አስቸጋሪ ህይወት አልፋዋለች። እንደቀድሞው በጠዋት የመነሳት ልምዷ ቢኖርም በትራንስፖርት እጦት መንገላታቱ ግን ቀርቶላታል። አሁን ታክሲ ለመያዝ መጋፋት፣ አርፍዶ ሥራ መግባትና አምሽቶ ወደቤት መመለስ የለም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት ለሠራተኞች ባመቻቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆኗ ነውና እጅግ ደስተኛ ሆናለች። አሰገደች በምትጠቀምበት ሰርቪስ ያሉ ተገልጋዮች ሁሌም የተለየ ስፍራ አዘጋጅተው ይንከባከቧታል። በተለይ ሾፌሮች የእሷን መድረስ ሳያረጋግጡ መንገድ አይጀምሩም። ለእሷ መሰል አካል ጉዳተኞች የሚደረገው ትኩረትም ያለስጋት እንዲጓዙ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል። አሰገደች የቀድሞውን ሁኔታ አሁን ካለችበት ጋር ስታወዳድር ቃላት ያጥራታልና ዘወትር ምስጋናዋ የላቀ ነው።

ወይዘሮ አረጋሽ ሰውነት ሲሰሩ ከቆዩበት የመንግሥት ሥራ በቅርቡ በጡረታ ተሰናብተዋል። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን መንግሥት ለሠራተኞች ባመቻቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ለተወሰነ ጊዜ የመጠቀም ዕድሉን አግኝተው ነበር። በዚህ ወቅት በሠራተኞች መካከል የነበረው መተሳሰብና መግባባት ማህበር እስከማቋቋምና የተቸገረን እስከመርዳት የዘለቀ ነበርና በነበረው አጭር ጊዜ የዕድሉ ተሳታፊ በመሆናቸው ደስ ይላቸዋል። እርሳቸው በቆዩበት ጥቂት ጊዜ ሰው ሲቀርና ኀዘን ሲደርስበት፣ ሲታመምና ችግር ሲያጋጥመው እንዴት ነው? የማለት ምስጢሩ አብሮ የመጓዙ አጋጣሚ የፈጠረው ግንኙነት እንደሆነ ያምናሉ። ወይዘሮ አረጋሽ ለዓመታት በትራንስፖርት ችግር ሲንገላቱ መቆየታቸውን አይዘነጉም። ለጥቂት ጊዜ የተገለገሉበትን የእፎይታ ጉዞ ሲያስቡት ግን ለዓመታት ከኪስ አውላቂዎች ጋር ታግለው ያለፉበት ፈታኝ ጊዜ በእጅጉ ይቆጫቸዋል።

ከዓመታት በፊት ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ትኩረት መሰጠቱ በርካቶችን አስደስቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ ብዘዎችን ከእንግልትና ከተጨማሪ ወጪ ታድጓልና ሁሌም ከጉዞው አመቺነት ጋር ምስጋና ማቅረብ የተለመደ ነው። አብዛኞቹ መንገደኞች የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ቢሆኑም ይበልጥ ያቀራረባቸው የጠዋት ማታ ጉዞው ነው።

የአራዳ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ተክላይ ወልደጊዮርጊስም ዘወትር በሚመላለሱበት የሠራተኞች ሰርቪስ ይህን ተመልክተዋልና በሆነው ሁሉ ደስተኛ ናቸው። አገልግሎቱ መጀመሩ አድካሚው መንገድ እንዲቃለል ብቻ ሳይሆን የሥራ ሰዓት እንዲከበር፣ መረጋጋት እንዲኖርና እርስ በራስ መተዋወቅ እንዲቻል አድርጓል። እርሳቸው እንደሚሉትም በዚህ መንገድ አብሮ ከሚጓዝ ሰው ብዙ የህይወት ልምድን መቅሰም ይቻላል። መተሳሰብ፣ እርስ በርስ መተዋወቅና ወቅታዊ ሁኔታን እያነሱ ለመነጋገር ጭምር ያለው ጠቀሜታ የላቀ ነው።

እርሳቸው ቀደም ሲል ወደሥራ ለመሄድ በታክሲ ሰልፍ መንገላታትና በአውቶቡስ ቆሞ የመሄድን ድካም አይተውታል። በየጊዜው በሚጨምረው የትራንስፖርት ታሪፍ ሳቢያም በየቀኑ የሚያወጡት ክፍያ ቀላል አልነበረም። ዛሬ ያ ሁሉ ችግር አልፎ ከእንግልት መዳኑ ቢያስደስታቸውም አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎች የሚያሳዩት ያልተገባ ባህርይ ደግሞ ያሳስባቸዋል። እነዚህ ሰዎች በሥነ ሥ ርዓቱ ከመጠቀም ይልቅ ከሾፌሮች ጋር የሚያደርጉት የአላስፈለጊ ንግግር ብዙዎችን ሲያውክ ተመልክተዋልና ይህ ችግር ባይደጋገም ሲሉ ይመክራሉ።

በሰማያዊው አውቶቡስ ጉዞ በርካቶች ማህበራዊ ህይወታቸው መልካም የሚባል ነው። ለወራት ሲያገለግሏቸው የቆዩ ሾፌሮች ሲቀየሩና ከእነሱ ሲለዩም «እናመሰግናለን» ለማለት የተለያዩ ስጦታዎችን ገዝቶ ማበርከት ተለምዷል። ይህ ልማድ ለአንድ ሾፌር ብቻ ሳይሆን ግልጋሎቱን አጠናቆ ቦታ ለሚቀይር ሁሉ የሚደረግ በመሆኑ አብዛኛው ተሳፋሪ በራሱ ተነሳሺነትና መልካም ፈቃድ የሚከውነው ይሆናል።

ብዙ ጊዜ ተሳፋሪ ከሾፌር የማያግባባው አጋጣሚ ቢፈጠር እንኳን መሀል ገብቶ የሚያስማማና ጠብን አስወግዶ ሰላም የሚያወርድ ሽማግሌ አይጠፋም። ይህ ችግር አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ቢሆንም አብሮ ከመቆየት ባህርይን የመላመድ ሁኔታ ያለ በመሆኑ በመኮራረፍ የመዝለቅ ሁኔታው እምብዛም አልተለመደም። ይህ አብሮነትም ከአንዱ ወደአንዱ እያለፈ ጉዞውን ሰላማዊና የመተሳሰብ እንዲሆን በቅብብሎሽ ለመቀጠል አስችሎታል።

ወይዘሮ ዘውድነሽ ኃይሌ ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩት መሀል አንዷ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ዕድል ተገልጋይ የመሆናቸው እውነት በፈቃደኝነት ተሳፋሪውን ለማስተባበርና ቁጥጥሩን ለመምራት አነሳስቷቸዋል። ቀድሞ በትራንስፖርት በተጠቀሙባቸው ዓመታት ለረጅም ጊዜ መቆማቸውና በእንግልት መቆየታቸው ለከፋ የወገብ ህመም ቢያጋልጣቸውም ዛሬ ባገኙት ዕድል በእጅጉ ተክሰዋልና አቅማቸው በፈቀደ መጠን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ።

ዘውድነሽ ጠዋት ማታ በሚደረገው ጉዞና በሥራቸው አጋጣሚ ማን እንደመጣና እንደቀረ የማወቅ ዕድሉ አላቸው። ሰዎች ያለምክንያት ሲጠፉና ከዓይን ሲርቁም እንደመልካም ጎረቤት ያሳስባቸዋል። በተለይ ለረጅም ጊዜ ቋሚና ተጠቃሚ ከሆኑት መሀል ችግር የደረሰባቸውን ተሳፋሪዎች ቢችሉ በአካል፣ አልያም ደግሞ በስልክ ደውለው መጠየቅን ለምደውታል።

ጠዋትና ማታ በመነሻና መድረሻ ስፍራዎች እንደ ሰማያዊ ጎርፍ አካባቢውን የሚያጥለቀልቁት የሠራተኛ ሰርቪሶች ብዘዎችን ከድካም፣ ከሥራ ብክነትና ከተጨማሪ ወጪ በመታደግ «እፎይ» አስብለዋል። እኔ የመኪኖቹን ብዛትና በተመሳሳይ ሰዓትና ቦታ በአንድ የመገኘት እውነታ ያለማቋረጥ እንደሚፈስ ሰማያዊ ጎርፍ መስዬዋለሁ። የእነዚህ ሰርቪሶች መኖር ለሠራተኛው ካበረከተው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባሻገር የፈጠረው ማህበራዊ መስተጋብርም ላቅ ያለ መሆኑን አምናለሁ። በሰማያዊው ጎርፍ የተገናኙ ተጓዦች ሁሌ ህይወታቸውን ይካፈላሉ፣ ልምዳቸውን ያጋራሉ፣ ማንነታቸውን አሳይተውም ያለፉበትን መንገድ እያለፉበት ባለው ጎዳና ላይ ይመነዝራሉ፤ በርካቶቹ የሰማያዊ ጎርፍ መንገደኞች።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy