Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰሞኑ አደጋ ዝርክርክነትን የሚያጋልጥ ነው!

0 779

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በመጀመሪያ በረጲ በተለምዶ ‹‹ቆሼ›› በሚባለው ሥፍራ በደረሰው አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸው ላለፈ ዜጎች የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንገልጻለን፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም መፅናናትን እንመኛለን፡፡ ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ አደጋ በአገር ላይ የደረሰ በመሆኑም፣ አገርንና ሕዝብን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች ከመከላከል አንፃር መሠረታዊ ጉዳዮችን አንስቶ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ የአገሪቱ ዜጎች ጤና፣ መኖሪያ፣ አካባቢና ደኅንነት የመሳሰሉት ከአደጋ ሥጋት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ለዚህም ሲባል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም ተጠናክሮ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የሰሞኑ አደጋ በአገሪቱ የሚታዩ ዝርክርክ አሠራሮችን የሚያጋልጥ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ይህ አደጋ የደረሰበት የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ በአንድ ወቅት ተዘግቶ ነበር፡፡ የከተማው ቆሻሻም ከአዲስ አበባ ውጪ ሰንዳፋ አካባቢ ይወገድ ነበር፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት ምክንያት የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ በመከልከሉ፣ የተዘጋው የረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ እንደገና ሥራውን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በዚህ ሥፍራ አደጋዎች እየደረሱ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ በሰዎች አካልም ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ የቆሻሻው ክምር ከመጠን በላይ በመግዘፉ የተነሳም በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው መንሸራተትተ አጋጥሟል፡፡ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ይህንን ችግር ተገንዝቦ ወቅታዊ ዕርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ የአሁኑ አሳዛኝ አደጋ ተከስቷል፡፡ አደጋን አስቀድሞ መከላከል መቻል የሰው ልጆችን ሕይወት ከመታደግ በተጨማሪ፣ ለሌላ ጊዜም አሥጊ እንዳይሆን የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አገሪቱ ሐዘን ተቀምጣለች፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ አደጋው ከተከሰተ በኋላ ለቀናት ከቆሻሻው ክምር ውስጥ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለመታደግ አልተቻለም፡፡ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ በቂ የቁፋሮ ማሽኖችንና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በማሰማራት በቅልጥፍና መሥራት ባለመቻሉ፣ የአካባቢው ሰዎች በዶማና በአካፋ ቁፋሮ ላይ ተሰማርተው ታይተዋል፡፡ የጠፉባቸውን የቤተሰብ አባላት (እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት፣ ልጆች…) የሚፈልጉ ብዙዎች በእጃቸው ጭምር ክምር ቆሻሻ ሲያገላብጡ ነበር፡፡ አደጋው የደረሰው በምሽት በመሆኑ በአካባቢው በእርግጠኝነት ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ አይታወቅም፡፡ በግምት 150 ሰዎች ያህል ነበሩ ቢባልም ከ70 በላይ መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡ በሕይወት የተገኙም አሉ፡፡ ሌሎቹ ግን የት ደረሱ? አሁንም ፍለጋው ቀጥሏል፡፡ ከቅድመ መከላከል እስከ አደጋው ማግሥት ያለው ሒደት የአቅም አለመገንባትን ያሳያል፡፡ ይህም ያሳዝናል፡፡

በአደጋው ሥፍራ ላይ የሚታየው የአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች መባዘን የሚናገረው የወገኖቻቸውን ዕጣ ፈንታ አለማወቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ልብ የሚነካ የቤተሰቦች ሐዘንና ግራ መጋባት ችግሮችን በጥልቀት ለመፈተሽ ይጠቅማል፡፡ ይህ ሥፍራ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ እንደ ሥጋት ይታይ እንደበር በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ለከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች በተደጋጋሚ መናገራቸውንና ሰሚ አለማግኘታቸውንም በሐዘን ይገልጻሉ፡፡ ቆሻሻ ከመጠን በላይ ተከምሮበት ተራራ የሚያክለው አካባቢ በተደጋጋሚ መንሸራተቱም ይነገራል፡፡ ታዲያ ግዴለሽነትን ምን አመጣው? በቀን ከ500 በላይ ሰዎች የሚውሉበት የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ በግምት በከተማው በዓመት ከሚሰበሰበው 300 ሺሕ ቶን ቆሻሻ አብዛኛው እንደሚከማችበት ይታወቃል፡፡ ይህ ሥፍራ ለራሱ ብቻ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አያስፈልገውም? ይህንን ተግባር መፈጸም ያለበት ባለቤት የለውም? ይህም ሌላው የዝርክርክነት ማጋለጫ ነው፡፡

በዚህ ሥፍራ እየተከማቸ ያለው ቆሻሻ ከመጠን በላይ ከመከመሩ የተነሳ አንድ ቀን ከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋጥም አለመጠርጠር አንድም የዋህነት፣ ካልሆነ ደግሞ ግዴለሽነት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተለያዩ አደጋዎች ሲደርሱ ክሬኖችና የመቆፈሪያ ማሽኖች ስለማይገኙ በውሰት ከሌላ ቦታ እስኪመጡ ድረስ በሰው ሕይወት ላይ ተፈርዷል፡፡ ከባድ የሚባሉ አደጋዎችም ደርሰዋል፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅምን በመገንባት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን መቀልበስ ይቅርና የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መገንባት እንኳን አልተቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ አደጋ ሲከሰት ግርግርና ጥድፊያ ይበዛል፡፡ በዚህ መሀል ግን የሰው ልጆች ሕይወት ለአደጋ ይዳረጋል፡፡ በከተማው መንገደች ላይ ተገቢው ቁጥጥርና የመከላከል ሥራ ስለማይከናወን፣ የተሽከርካሪ አደጋ የዜጎችን ሕይወት በየቀኑ ይቀጥፋል፡፡ በመንገዶችና በግንባታ ሥፍራዎች ተከፍተው የተተው ጉድጓዶች ብዙዎችን ለሕልፈትና ለአካል ጉዳት ዳርገዋል፡፡ በሚገነቡ ሕንፃዎች በአግባቡ ጥንቃቄ ስለማይደረግ አደጋ ይደርሳል፡፡ ሕግ ባለመከበሩ ብቻ የተዝረከረኩ አሠራሮች በዝተዋል፡፡

በመሠረቱ በእንዲህ ዓይነት አካባቢ ሰዎች መኖሪያቸውን መሥርተው ሊኖሩ አይገባም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሚቴን የተባለ በካይ ጋዝ የሚያመነጭ አካባቢ ውስጥ የዕለት እንጀራቸውን ከመፈለግ ጀምሮ መኖሪያቸውን ሲመሠርቱ ዝም ማለት አልነበረበትም፡፡ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ 513/1999 መሠረት የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን በመከተል የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ መገንባት፣ የአካባቢ ኦዲት መካሄዱን ማረጋገጥ፣ አግባብነት ባለው ሕግ መሠረትም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መካሄዱን ማረጋገጥ ግዴታ ነው፡፡ ይህም ግዴታ በከተማ አስተዳደሮች ላይ ተጥሏል፡፡ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ በሥራ ላይ እያለ ወይም ከተዘጋ በኋላ በአካባቢ፣ በሰው ጤና ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ካደረሰ ጥፋተኝነትን ማረጋገጥ ሳያስፈልግ ባለቤቱ ኃላፊ ይሆናል ሲልም ደንግጓል፡፡ ይህ ተከብሯል? መልስ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ዘመን ቆሻሻ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ሀብት ነው፡፡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ያገለግላል፡፡ ቆሻሻ ተከምሮ በካይ ጋዝ ወደ አካባቢ ከሚያመነጭ ወደ ኢንቨስትመንት መቀየር ተገቢ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ቢኖርም ገና ነው፡፡ ቆሻሻ በስፋት ወደ ቢዝነስ ተቀይሮ ለሰው ልጅ ጥቅም መስጠት ሲገባው በአደጋው ክቡር የሆነው ሕይወት ሲያልፍ ያበሳጫል፣ ያስቆጫል፡፡

ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያጋጥማሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን አደጋዎች ለመከላከል የሚያስችል አቅም መገንባት ደግሞ መተኪያ የለውም፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ከአቅሙ በላይ እየተከመረበት ሲቆለል አደጋ አያመጣም ብሎ መዝናናት ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተቻለ መጠን ጉዳቱን ለመቀነስ፣ ቢቻል ደግሞ ተለዋጭ ሥፍራ መፈለግ አንዱ የመከላከል ሥራ ይሆን ነበር፡፡ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ መረባረብ ደግሞ ትልቅ ሥራ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የአካባቢው ሰዎች ባለፉት ዓመታት ሥጋታቸውን ሲገልጹ በአግባቡ አዳምጦ መፍትሔ መፈለግ ተገቢ ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን የቆሻሻ ተራራ ተንዶ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ የሥነ ልቦና ስብራት አስከትሏል፡፡ የተቀሩትን መልሶ ከማስፈርና ከማቋቋም በተጨማሪ፣ ለዘለቄታው የሚበጅ አስቸኳይ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖር አለበት ተብሎ የሚወተወተው ዝርክርክነትን ለማስወገድ ጭምር ነው፡፡ የተዝረከረኩ አሠራሮች የሚጋለጡት በእንዲህ ዓይነት ክፉ ጊዜ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል! reporte

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy