NEWS

የስዊዘርላንዱ ኔስሌ በኢትዮጵያ ፋብሪካ የመክፈት ሀሳብ እንዳለው ይፋ አደረገ

By Admin

March 08, 2017

የስዊዘርላንዱ ኔስሌ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ በወተት ማቀነባበር መስክ ፋብሪካ የመክፈት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የኔስሌ የወደፊት የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ 20 አገሮች ውስጥ እንዲሁም ከአምስት አቅም ያላቸውና ምርጫው ካደረጋቸው አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ ትካተታለች።

በኢኳቶሪያል አፍሪካ ቀጣና የኔስሌ የአፍሪካ ቀንድ ክላስተር ማናጀር የሆኑት አቶ ወሰንየለህ ፍቅሬ፥ በኢትዮጵያ ወደፊት እንደሚገነባ የሚጠበቀው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መቼ ዕውን ሊሆን እንደሚችል የሚወስኑት በአገሪቱ የሚገኘው የወተት ምርትና የአቅርቦት መጠን፣ የወተት ጥራት ደረጃና ጤንነት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና የፋብሪካው ምሥረታ መቼ ሊሳካ እንደሚችል ገና ያልታወቀ ሲሆን፥ ከዚህ ይልቅ የዱቄት ወተት ምርቶቹን እዚሁ ለማሸግ የሚያበቁትን ዝግጅቶች በማድረግ ይህንን የሚያከናውን ፋብሪካ መመሥረቱ እንደማይቀር አረጋግጠዋል።

የማሸጊያ ፋብሪካው በቅርቡ ዕውን ሊሆን እንደሚችል ቢገለጽም፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥና በምን ያህል ወጪ ለሚለው ምላሹ ወደፊት እንደሚታወቅም አስታውቀዋል። ከዚህ ባሻገር ኔስሌ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን የምርቱ አምባሳደር አድርጎ መሰየሙ ይፋ ተፈርጓል፡፡

በመላው ዓለም ከ2 ሺህ በላይ ብራንዶችን የሚያስተዳድረው ኔስሌ፣ ከ10 ሺህ በላይ ምርቶችን በማምረት ከ1 ቢሊየን በላይ የምርት ሽያጭ የሚያከናውን የምግብና የመጠጥ አምራች ኩባንያ ነው።

በአብዛኛው በውኃ፣ በወተት፣ በቡና እንዲሁም በልዩ ልዩ የበለፀጉ ምርቶቹ የሚታወቀው ኔስሌ፣ በኢትዮጵያ የውኃ ማዕድን መስክ ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር አብሮ ለመሥራት መስማማቱ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ሪፖርተር