Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሶማሊያ ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ተግባር አስፈላጊ ነው

0 268

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሶማሊያ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን ወደ አገራቸው መልሶ የማቋቋሙ ተግባር አስተማማኝነት የሚረጋገጠው ከ“አካባቢው ሲመነጭ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ሲሆን ነው” ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገሮች መሪዎች የተሳተፉበት “የሶማሊያ ስደተኞችን መልሶ የማቋቋምና ዘላቂ መፍትሄ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ልዩ የመሪዎች ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ ተካሂዷል።

ልዩ ስብሰባው በቀጣናው አገሮች ለተሰደዱት 900 ሺ ለሚሆኑ የሶማሊያ ዜጎች ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ለማስቀመጥ በኢጋድ የወቅቱ ሊቀ መንበር አማካኝነት የተጠራ ነው።

በቅርቡ በሶማሊያ የተካሄደውና “ስኬታማ ነው” የተባለው ምርጫ ለአገሪቷ መረጋጋትና መፃኢ እድል ብሩህነት አመላካች መሆኑም ለልዩ ስብሰባው መዘጋጀት እንደመነሻ ይጠቀሳል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር፤ ለሶማሊያ ስደተኞችና ተፈናቃዮች ችግር ዘላቂው መፍትሄ ከአካባቢው የሚመነጭ ነው።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ ከአካባቢው የሚነሳ ማኅበረሰባዊ መሰረት ያለው አቀራረብ በቀውስ ወቅት የተጎዱ ሕዝቦችን ድምጽ ለማሰማት ያስችላል። የዚህ ዓይነቱ ተግባር ደግሞ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን ከማሳተፉ ባሻገር ሰብዓዊ ድጋፍን ከልማት ጋር ለማስተሳሰር የሚረዳ ነው።

ለሶማሊያ ዘላቂ መፍትሄ በአገሪቷ ውስጥ ያሉ ኃይሎች በብሄራዊ፣ በቀጣናና በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያመለከቱት።

የአገሪቷን “ብሄራዊ የደህንነት ኃይሉን አቅም መገንባትና ማጠናከር ያስፈልገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአልሸባብ ጋር የሚፋለመውን በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በመደገፍ በአሸናፊነት እንዲወጣ የማድረግ አስፈላጊነትም አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ የሶማሊያን ሕዝብና መንግስት የፖለቲካና የዴሞክራሲ ተቋሞች እንዲጠናከሩ መደገፍም ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፎች በመስጠት፣ ገንዘብና ግብዓት በማቅረብ አገሪቷን ዳግም ለመገንባትና ለማልማት በሚደረገው ርብርብ መሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

ይህም የአገሪቷ መንግስት መሰረታዊ የሆኑ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትና የህዝቡን አኗኗር ለማሻሻል ያግዛል።

የአገሪቷን ሰላም፣ መረጋጋትና የመንግስት ተቋማትን ለማጠናከርና የልማት ተግባራትን ለማከናወን ስደተኞችና ተፈናቃዮችን የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ነው የገለጹት።

“ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ከእኛ ጋር ያለውን ትስስር አጠናክሮ መቀጠል አለበት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ገንቢና ሂደቱን በሚያጠናክሩ ውይይቶች ላይ መመስረት እንዳለበት ነው ያመለከቱት።

ለሶማሊያ ዘላቂ መፍትሄ የተቀናጀና የጋራ ጥረት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ ነው የተመለከተው።

ከኢጋድ አባል አገሮች በተጨማሪ “ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለሶማሊያ ስደተኞች ድጋፉን ማጠናከር አለበት” ያሉት ደግሞ ልዩ ስብሰባውን ያዘጋጀችው ኬንያ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፤ በአገራቸው በርካታ ሶማሊያዊያን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ። እነዚህ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰው ሰላማዊና የተረጋጋ ኑሮ መቀጠል ይፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ የመልሶ ማቋቋም ተግባር መከናወን ይኖርበታል።

ከኬንያ 60 ሺ የሚሆኑ ስደተኞች መመለሳቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በስደተኞቹ ፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ መልኩ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ለዚህም የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው አጽንኦት የሰጡት።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ በበኩላቸው የኢጋድ አባል አገሮች ላቀረቡት የመፍትሄ ሀሳብና ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው አገራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተው፤ ከኢጋድ አገሮች ጋር “በተቀናጀና በጋራ ከሰራን ስኬታማ እንሆናለን” ብለዋል።

አገራቸውን መልሶ ለመገንባትና ለማልማት ስትራቴጂ መቀየሱን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ከህዝባቸው ጋር በአሸናፊነት እንደሚወጡ ነው የገለጹት።የኢጋድ አባል አገሮች የሶማሊያ ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋምና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ነው የተገለጸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy