የሶማሊያ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን ወደ አገራቸው መልሶ የማቋቋሙ ተግባር አስተማማኝነት የሚረጋገጠው አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ሲሆን ነው ሲሉ የኢጋድ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል አገሮች መሪዎች የተሳተፉበት “የሶማሊያ ስደተኞችን መልሶ የማቋቋምና ዘላቂ መፍትሄ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ልዩ የመሪዎች ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ ተካሂዷል።
ልዩ ስብሰባው በቀጣናው አገሮች ለተሰደዱት 900 ሺህ ለሚሆኑ የሶማሊያ ዜጎች ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ለማስቀመጥ በኢጋድ የወቅቱ ሊቀ መንበር አማካኝነት የተጠራ ነው።
በቅርቡ በሶማሊያ የተካሄደውና “ስኬታማ ነው” የተባለው ምርጫ ለአገሪቷ መረጋጋትና መፃኢ እድል ብሩህነት አመላካች መሆኑም ለልዩ ስብሰባው መዘጋጀት እንደመነሻ ይጠቀሳል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢጋድ የወቅቱ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር፥ ለሶማሊያ ስደተኞችና ተፈናቃዮች ችግር ዘላቂው መፍትሄ ከአካባቢው የሚመነጭ ነው ብለዋል።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ከአካባቢው የሚነሳ ማኅበረሰባዊ መሰረት ያለው አቀራረብ በቀውስ ወቅት የተጎዱ ሕዝቦችን ድምጽ ለማሰማት ያስችላል፤ የዚህ ዓይነቱ ተግባር ደግሞ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን ከማሳተፉ ባሻገር ሰብዓዊ ድጋፍን ከልማት ጋር ለማስተሳሰር የሚረዳ ነው።
የአገሪቱን “ብሄራዊ የደህንነት ኃይሉን አቅም መገንባትና ማጠናከር ያስፈልገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአልሸባብ ጋር የሚፋለመውን በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በመደገፍ በአሸናፊነት እንዲወጣ የማድረግ አስፈላጊነትም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ የሶማሊያን ሕዝብና መንግስት የፖለቲካና የዴሞክራሲ ተቋሞች እንዲጠናከሩ መደገፍም ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፎች በመስጠት፣ ገንዘብና ግብዓት በማቅረብ አገሪቷን ዳግም ለመገንባትና ለማልማት በሚደረገው ርብርብ መሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።ይህም የአገሪቷ መንግስት መሰረታዊ የሆኑ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትና የህዝቡን አኗኗር ለማሻሻል ያግዛል።
የአገሪቷን ሰላም፣ መረጋጋትና የመንግስት ተቋማትን ለማጠናከርና የልማት ተግባራትን ለማከናወን ስደተኞችና ተፈናቃዮችን የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ከኢጋድ አባል አገሮች በተጨማሪ “ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለሶማሊያ ስደተኞች ድጋፉን ማጠናከር አለበት” ያሉት ደግሞ ልዩ ስብሰባውን ያዘጋጀችው ኬንያ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ ናቸው።
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፤ በአገራቸው በርካታ ሶማሊያዊያን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፤ እነዚህ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰው ሰላማዊና የተረጋጋ ኑሮ መቀጠል ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ የመልሶ ማቋቋም ተግባር መከናወን ይኖርበታል።
የፌዴራል ሪፐብሊክ ሶማሊያ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ በበኩላቸው የኢጋድ አባል አገሮች ላቀረቡት የመፍትሄ ሀሳብና ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው አገራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተው፤ ከኢጋድ አገሮች ጋር “በተቀናጀና በጋራ ከሰራን ስኬታማ እንሆናለን” ብለዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ