Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የራሱን አመራሮችና ኮሚቴዎች በማዋቀር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ

0 862

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‹‹ሕግ የሚያውቀውን ሰማያዊ ፓርቲ እየመራን ያለነው እኛ ነን›› አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅናን አግኝቶ ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ አመራር የነበሩት እነ አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ አዲስ አመራሮችና ኮሚቴዎች በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸውና ደንብና ሥርዓቱን ጠብቀው ሰማያዊ ፓርቲን እየመሩ የሚገኙት እነሱ ብቻ መሆናቸውን ደግሞ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲን አመራር በሕገወጥ መንገድ እንደተነጠቁ የሚናገሩት የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ወይም አዲስ ፓርቲ የማቋቋም አዙሪት ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ ተናግረው፣ በነበሩበት ፓርቲ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችንና እንቅፋቶችን ገላልጦ በማውጣት ፍርዱን ለሕዝብ የማሳየት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘጠኝ አባላት ያሉት የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴና ሦስት አባላት ያሉት የዕቅድና የስትራቴጂ ኮሚቴ፣ እንዲሁም ሁለቱን ኮሚቴዎች የሚመራና የሚቆጣጠር ብሔራዊ ሸንጎ አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ይልቃል፣ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ቀደም ብለው የተፈጠሩ ችግሮች ለምን እንደተፈጠሩ፣ ችግሩ ምን እንደሆነና ማን ምን እንዳደረገ፣ አዲስ ሊቀመንበር (አመራር) ለመምረጥ ጠቅላላ ጉባዔ እንዴት እንደተጠራ፣ እነማን እንደተገኙና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን እንዴት ሊያፀድቅ እንደቻለ የሚያሳይ በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ በመሰብሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ ማድረግ የኮሚቴዎቹ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሰነድ መልክ ይፋ ለማድረግ ቀናት ቢቀሩም በተለያየ መንገዶች እያሳወቁ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ለምን እንዳልፈለገና አዲሱ አመራር ፓርቲውን እንዲመራ ለምን እንደተፈለገም ጭምር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ይፋ እንደሚያደርጉ የተናገሩት አቶ ይልቃል፣ እሳቸው ይመሯቸው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አሁንም በሁሉም መንገድ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ አመራር መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በእሳቸው አመራር ሥር የነበሩ አባላት እንዳልተገኙ ጠቁመው፣ ከ220 በላይ አባላት የፈረሙበት ማስረጃ ከየት መጥቶ ለምርጫ ቦርድ እንደቀረበ ጭምር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያጋልጡ ገልጸዋል፡፡ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው አባል ተፈራርሞ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት ስለሚችል በቀጣይ እነሱም ጠቅላላ ጉባዔ ሊጠሩ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ይልቃል ከገንዘብ ጉድለት ጋር በተገናኘ በሕግ ይጠየቃሉ ስለመባሉና የፓርቲው አባል ሆነው ስለመቀጠላቸው ተጠይቀው፣ በአዲሱ መዋቅር (የቀድሞው አመራር ባዋቀረው) ውስጥ በብሔራዊ ሸንጎው ውስጥ እንዳሉበትና የሰማያዊ ፓርቲም አባል መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ አመራር አዲስ መዋቅር በመሥራት ኮሚቴና ብሔራዊ ሸንጎ በመሾም የሰማያዊ ፓርቲን የሥራ ሒደት እያንቀሳቀሰ ስለመሆኑ የተጠየቁት አዲሱ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አንድ አባል ወይም አመራር የፓርቲ አባል ሲሆን የሚጣሉበት ግዴታዎችና መብቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ የሺዋስ፣ አመራሩ የተጣለበትን ግዴታና መብት መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ፓርቲውም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈትነውና አጣርተው ሕጋዊ ለሆነው በጠቅላላ ጉባዔ አመራርነቱን እንዲይዝ ለተመረጠው (እሳቸው ለሚመሩት) አካል መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ እሳቸውም የሚያውቁት ሕጋዊና ትክክለኛው ሰማያዊ ፓርቲ እሳቸው የሚመሩት መሆኑንና የመንግሥት ዕውቅናም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ ሊቀመንበርና አመራሮች በፓርቲው ውስጥ በምን ሁኔታ (በአመራርነትና በአባልነት) እየተሳተፉ እንደሚገኙ የተጠየቁት አቶ የሺዋስ፣ ከአቶ ይልቃልና ከፋይናንስ ኃላፊዎች በስተቀር ሌሎቹ ታርመውና ራሳቸውን አስተካክለው ከቀጠሉ መብታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ይልቃልና የፋይናንስ ኃላፊዎች ግን በሕግ የሚጠየቁበት ጉዳይ ስላለ ያ ሳይጠናቀቅ እንደማይችሉ አረጋግጠዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy