CURRENT

የቱሪዝም መለያው ምድረ ቀደምት የሚል አቻ ትርጉም ተሰጠው

By Admin

March 22, 2017

የኢትዮጵያ ላንድ ኦፍ ኦሪጅን በሚል የተዋወቀው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ብራንድ የአማርኛ ትርጉሙ ˝ምድረ ቀደምት˝ በሚል ተተርጉሞ በጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል።በጉባኤው ላይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በየጊዜው የሚነሱ ተመሳሳይ ችግሮችን ለመፍታት አሁንም ከፍተኛ ትኩረትና የቅንጅት ስራ እንደሚያስፈልግ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው እየተደረገ ባለው ውይይት ዘርፉን ለማዘመን ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር አሁንም ሰፊ ስራዎች እንደሚቀሩ ተነስቷል፡፡ከፓርኮች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሱት ችግሮች እየተፈቱ አለመሆኑ እና ከቅርሶች እድሳት ጋር በተያያዘ ደግሞ የነባር ይዞታዎች መጥፋት ችግሮች መኖራቸው እንዲሁም በዘርፉ አሉ ተባሉ ሌሎች ችግሮች በምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።

ለጥያቄዎቹም የምክር ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ምላሽና አቅጣጫዎች ሰጥተዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘርፉ እምቅ ሀብት ያላት ቢሆንም ተጠቃሚ መሆን አለመቻሏን ከግምት ውስጥ በማስገባት የቱሪዝም ትራንፎርሜሽን ምክር ቤት በማቋቋም አሉ የተባሉ ማነቆዎችን የመፈተሽና የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም።

ለሀገራችን በጎ ገጽታ ግንባታ ሥራችን ከፍተኛ ሚና ከመጫወትና ኢኮኖሚዋን ከመደገፍ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለውን ይህን ዘርፍ የማጠናከር ሥራ ለአንድ ተቋም አልያም ለተወሰኑ አካላት የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም አካላት ለዘርፉ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲሚገባቸውም አንስተዋል።

በተለይ የክልልና የፌዴራል የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ቀጣይነት ያለው ሥራት መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።በጉባኤው በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አቶ ሀብቴ ስላሴ ታፈሰ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እጅ የእውቅና ሽልማት ተቀብለዋል፡፡