CURRENT

የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ልማት ሚናቸውን እያሳደጉ ነው ፡- አምባሳደር አያሌው ጎበዜ

By Admin

March 29, 2017

የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገሪቱ ልማት ሚናቸው  እያሳደጉ መሆናቸውን በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያና ቱርክ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት እንደሆኑ የገለፁት አምባሳደሩ ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት አጋጥሞ ለነበረው የምግብ እጥረት ከ2 ሺህ 500 ቶን በላይ ምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶች እርዳታ በመስጠት ለችግራችን ፈጥና ደርሳለች ብለዋል፡፡

አገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት በኩልም ቱርክ ለኢትዮጵያ ባቡር ፕሮጀክት ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ያደረገች ሲሆን በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱርክ ኩባንያዎች ካፒታል ኢንቨስትመንት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የቱርክ ባለሀብቶች በአገሪቱ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደስተኛ መሆናቸውንም አምባሳደር አያለው ጎበዜ ገልፀዋል፡፡

አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ከአናዱሉ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ ቱርክ አፍሪካን እያለማች ያለች ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ እንዳሉት ቱርክ የአፍሪካን ህዝብ እያለማች እንጂ እየበዘበዘች አይደለም፡፡

ቱርክ የምትከተለው ኢንቨስትመንት የሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለአፍሪካ መልካም መሆኑን አምባሳደሩ አስምረውበታል፡፡