Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትራምፕን አስተዳደር የበለጠ ጥርጣሬ ላይ የጣለው ምርመራ

0 343

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ በነበሩበት ወቅት ፕሬዚዳንቱና አማካሪዎቻቸው ከሩስያ ጋር ግንኙነት ማድረግና አለማድረጋቸውን ቢሮው ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የቢሮው ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይና የአሜሪካ ብሔራዊ የፀጥታ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አድሚራል ማይክ ሮጀርስ በአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት የደህንነት ኮሚቴ አባላት ፊት ቀርበው ባደረጉት ገለፃ፣ ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ሴራ መሸረቧንና አለመሸረቧን የመመርመር ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ምርመራው ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እየተካሄደ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ወራትን ይፈጃል የተባለለት ምርመራ ሩስያ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት የኢሜይል መልዕክቶችን በመበርበር ምስጢራዊ መረጃዎች ይፋ እንዲሆኑ ስለማድረጓ ክስ ስለቀረበባት ጉዳይ ጨምሮ ፕሬዚዳንት ትራምፕና አማካሪዎቻቸው እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው ከሩስያ ባለስልጣናት ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

አምስት ሰዓት ከ30 ደቂቃ በፈጀው ማብራሪያ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ “በምርመራ ሂደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው” በማለት የኮሚቴው አባላት ጥያቄ ባነሱባቸው ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሂላሪ ክሊንተን ጥላቻ እንዳላቸውና ከሚጠሏቸው ግለሰብ በተቃሪኒ የተሰለፉትን ሰው እንደሚደግፉ ማወቅ ለአሜሪካ የደህንነት መሥሪያ ቤቶች ቀላል ነው” ያሉት ጀምስ ኮሜይ፣ ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባት የአሜሪካን የዴሞክራሲ ስርዓት ለማፈራረስ ሙከራ አድርጋለች ሲሉ የቀድሞዋን ሶሻሊስታዊ አገር በጥብቅ ኮንነዋል፡፡

ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ “የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ የነበሩት ወይዘሮ ሂላሪ ክሊንተን እንዲሸነፉ ብቻ ሳይሆን ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ጠንካራ ፍላጎት ነበራቸው” ከሚለው አቋማቸው ፍንክች አለማለታቸው አስገራሚ ሆኗል፡፡

የምክር ቤቱ የደህንነት ኮሚቴ አባላት የሆኑ አንዳንድ ሪፐብሊካውያን “ከሩስያ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ዶናልድ ትራምፕ ሳይሆኑ ዴሞክራቷ ሂላሪ ክሊንተን ናቸው” በማለት ላቀረቡት ክስ የፕሬዚዳንት ፑቲን ዓላማ ለሂላሪ ክሊንተን እጩነት እውቅና በመንፈግ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ማድረግ ስለመሆኑ ባለፈው ጥር ወር ላይ በአሜሪካ የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶች አማካኝነት ይፋ የሆነው ሪፖርት ስለሚያመለክት ጀምስ ኮሜይ የአባላቱን ክስ ውድቅ አድርገውታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ “ሩስያ በቀጣዩ ማለትም በ2020ው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ጣልቃ ልትገባ ትችላለች፤ በ2018 በሚደረገው የኮንግረስ አባላት ምርጫ ላይም እጇን ልታስገባ ትችላለች፤ በዴሞክራሲያችን ላይ ግርግር መፍጠር እንደሚችሉ አሳይተውናልና ልንጠነቀቅ ይገባል” በማለት በሩስያ ተግባር ክፉኛ እንደተበሳጩ ፈርጠም ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ከአወዛጋቢው የ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቀን ጥቂት ቀደም ብሎ የፌዴራል ምርመራ ቢሮው ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ “ሂላሪ ክሊንተን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ምስጢራዊ የመንግሥት መረጃዎችን በግል የኢሜይል አድራሻቸው በኩል ስለመለዋወጣቸው ምርመራ ይደረግባቸዋል” ብለው ማሳወቃቸው በህዝብ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት በማሳነስ በምርጫው እንዲሸነፉ ሆነዋል በማለት የሂላሪ ክሊንተን ደጋፊዎች በጀምስ ኮሜይ ላይ የቋጠሩት ቂም አልሻረላቸውም፡፡

“ ‘ጥቁር አሜሪካዊ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን የማይታሰብ ነው’ ” ሲባል የኖረውን አባባል ፉርሽ አድርጋ ለባራክ ኦባማ እድል በመስጠት ታሪክ የሰራችውና ሂላሪ ክሊንተንን የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንቷ ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሳ የነበረችው አሜሪካ፣ ይህኛውን ታሪክ እንዳትደግም ያደረጓት አሁን የአዞ እንባ የሚያነቡት ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ ናቸው” ይሏቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ እና የአሜሪካ ብሔራዊ የፀጥታ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አድሚራል ማይክ ሮጀርስ በአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት የደህንነት ኮሚቴ አባላት ፊት ቀርበው ላደረጉት ንግግር ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አላባከኑም፡፡ እንደተለመደው የእርሳቸው ምርጫ በሆነው የትዊተር ገፃቸው ላይ እርሳቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸውና አማካሪዎቻቸው ከሩስያ ባለስልጣናት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው በመግለፅ ሩስያ በምርጫው ሂደት ውስጥ ጣልቃ ገብታለች ተብሎ የተሰራጨውን መረጃ “ሐሰተኛ ወሬ” በማለት በድጋሚ አጣጥለውታል፡፡ ከማብራሪያው ቀደም ብሎም፣ “የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው የተከናነቡትን አስከፊ ሽንፈት በሩስያ የጣልቃ ገብነት ጉዳይ ለመሸፋፈን መሞከራቸውን ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሀቅ ነው” በማለት ፅፈው ነበር፡፡

የዋይት ሀውስ የፕሬስ አታሼ ሾን ስፓይሰር ጉዳዩን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የፕሬዚዳንት ኦባማ ባለስልጣናትን ሃሳቦች እንደማስረጃነት ከማቅረብ ውጭ አሳማኝ ማስረጃ ከመስጠት የዘለለ ምላሽ አልሰጡም፡፡ ስፓይሰር “በፕሬዚዳንት ትራምፕና በሩስያ ባለስልጣናት መካከል ግንኙነት እንዳልነበረ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለስልጣናት ጭምር የመሰከሩት ሀቅ በመሆኑ ምርመራው ምንም የሚያስገኘው አዲስ ግኝትና የሚያመጣው ለውጥ አይኖረውም” በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡

አወዛጋቢው የ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን አሸናፊ አድርጎ ከተጠናቀቀ በኋላ የአሜሪካ የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶች “ሩስያ በምርጫው ሂደት ጣልቃ ስለመግባቷ መረጃውም ማስረጃውም በእጃችን አለ” ማለታቸውን ተከትሎ የወቅቱ ትሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሩስያና ጎምቱ ሹማምንቷ ላይ የማዕቀብ ናዳ እንዳዘነቡባቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እ..አ መጋቢት 4 ቀን 2017 ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ ከሚገኘው የማራላጎ ሪዞርታቸው ሆነው “የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልኬን አስጠልፈው ሲከታተሉኝ ነበር፤” በማለት ያሰሙትን ወቀሳ የሚያስረዳ ማስረጃ እንደሌላቸው ጀምስ ኮሜይ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ በባራክ ኦባማ ትዕዛዝ ከተፈፀመው ስለላና ብርበራ ጀርባ የብሪታኒያ የደህንነት መስሪያ ቤት እጅ እንዳለበት መረጃ አለኝ ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ የፀጥታ ኤጀንሲ ዳይሬክተሩ አድሚራል ማይክ ሮጀርስ “የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ንግግር ቁልፍ አጋራችን ከሆነችው ከብሪታኒያ ጋር ያለንን ግንኙነት ጥላሸት የሚቀባ ነው” በማለት በጉዳዩ ዙሪያ የሚቀርብ ማንኛውም ገለፃና ክስ በማስረጃ የተደገፈና ጥንቃቄ የታከለበት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤቱ የደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ሪፐብሊካኑ ዴቪን ኑን፣ “የመረጃ ልውውጦችን የሚበረብርና በትራምፕ ማማ ላይ የተገጠመ መሳሪያ እንዳልነበር እናውቃለን” በማለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በባራክ ኦባማ ላይ ያቀረቡትን ክስ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትርና የማዕከላዊ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር የነበሩት ሊዮን ፓኔታ በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያሰሙት ውንጀላ ስህተት መሆኑን አምነው ባራክ ኦባማን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በእርግጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕም ይሁኑ የዋይት ሐውስ አስተዳደራቸው ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ማስረጃ ለማቅረብ ተቸግረዋል፡፡

የፖለቲካ ብስለት የሌላቸውና ዞሮ ዞሮ መዘዙ ለራሳቸው የሚተርፍ ነገር በመጫር የሚታወቁት ፕሬዝዚዳት ዶናልድ ትራምፕ፣ “ባራክ ኦባማ ስልኬን አስጠልፈው የምርጫ ቅስቀሳ መረጃዎቼን ልቅም አደረገው ሲከታተሉኝ ነበር” በማለት ላቀረቡት ወቀሳ ባራክ ኦባማ ወቀሳውን በቃል አቀባያቸው በኩል እንዳጣጣሉት የሚታወስ ነው፡፡

ያም አለ ይህ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ የጀመረው ምርመራ ብዙዎች በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ላይ ያላቸው ጥርጣሬ የበለጠ ከፍ እንዲል እያደረገ ስለመሆኑ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ አሜሪካ የምንጊዜም ባላንጣዬ ናት የምትላት ሩስያ ስሟ በክፉ ሲነሳ ብርድ ብርድ ይላቸዋል የሚባሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተለያዩ ጊዜያት ስለ ሩስያ መልካምነት የተናገሯቸው ንግግሮች፣ የፕሬዚዳንቱ የቀድሞው የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪያቸው ማይክል ፍሌን ከሩስያ አምባሳደር ጋር በነበራቸው ግንኙነት ስልጣን መልቀቃቸው ሲታሰብ ሰውየው ያለሩስያ ድጋፍ ምርጫውን አላሸነፉም የሚሉ ሰዎች ቁጥራቸው እንዲበራከት ምክንያት ሆኗል፡፡

የፌዴራል ምርመራ ቢሮው በምርጫው ወቅት የነበረው የሩስያ ጣልቃ ገብነት ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ማድረጉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካገኘ ለወትሮውም ቢሆን ከጥርጣሬ መረብ ያልወጣው የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጉዞው ከድጡ ወደ ማጡ ይሆንበታል እየተባለ ነው፡፡

 አንተነህ ቸሬ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy