CURRENT

የትራፊክ ሥርዓት የማታውቀው ከተማ

By Admin

March 05, 2017

ጠመዝማዛውን መንገድ ጨርሰው የዳዬ ከተማ መግቢያ ላይ ብቅ ሲሉ በርካታ የሞተር ሳይክሎች ይመለከታሉ፡፡ አልፎ አልፎም ባለ ሦስት እግር ባጃጆች ይታያሉ፡፡ ሞተር ሳይክሎቹ ግን ለከተማው ነዋሪዎች ብቸኛ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡

 መንገዱ ላይ የተኮለኮሉት ሞተረኞች ደንበኛ የተገኘ ሲመስላቸው ተሳፋሪውን ለመውሰድ ይሻማሉ፡፡ ቀልጣፋው የመጣውን ደንበኛ እንደወሰደ ሁሉም ወደ ነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ተራ ጠብቆ መሥራት የሚባል ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ይህ ብቻም አይደል በአንድ ሞተር ላይም እስከ ስድስት ተሳፋሪዎችን መጫን የተለመደ ነው፡፡ ጫት፣ ጣውላ፣ ቆርቆሮና ሌሎች ነገሮችም የሚያስጭን ደንበኛ ከተገኘም ዓይናቸውን አያሹም ሞተረኞቹ፡፡

ካሉት የሞተር ሳይክሎች ብዛት አንፃር የከተማው አስፋልት በጣም ጠባብ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ ከአቅማቸው በላይ ሰውና የተለያዩ ጭነቶችን የደራረቡ ስምንት የሚሆኑ ሞተሮች በጠባቡ የከተማው አስፋልት ላይ ወዲያና ወዲህ ይከንፋሉ፡፡

አልፎ አልፎ ብቅ ከሚሉት ውጪ ሁሉም የሰሌዳ ቁጥር የላቸውም፡፡ በቁጥሩ ፋንታ ‹ፍቅር›፣ ‹ሁሉ በእርሱ ሆነ› የሚሉ የተለያዩ ጥቅሶች በየሞተሮቹ ጀርባ ላይ ሰፍሯል፡፡ እንዲህ ያሉ ሕገ ወጦችን ለመቆጣጠር የተሠማሩ ትራፊክ ፖሊሶች ሚያሽከረክሩት ተመሳሳይ ሰሌዳ አልባ ሞተሮችን መሆኑ ደግሞ ምንድነው ነገሩ? ያሰኛል፡፡

 አካባቢው እንደ ቡና ያሉ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ ምርቶች መገኛ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ብዙም የገንዘብ ችግር የለባቸውም ሊባል ይችላል፡፡ ከማሳቸው ያለ ቡና ሲደርስ አንድ ሞተር ለመግዛት የሚሆናቸውን ያህል ገንዘብ አያጡም፡፡ ከኬንያ ወደ ከተማው የሚገቡ የኮንትሮባንድ ሞተሮች ደግሞ ዋጋቸው ቅናሽ መሆን ደግሞ ነገሩን ቀለል አድርጓል፡፡ በኮንትሮባንድ ገበያ አንድ ሞተር እስከ 29 ሺሕ ብር ይሸጣል፡፡

አብዛኛዎቹ ሞተረኞች በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን  መገመት አይከብድም፡፡ ዋናው ነገር ሞተሩን ስለመግዛት እንጂ እንዴት መጠቀምና ማሽከርከር ይቻላል ስለሚለው ጉዳይ የሚጨነቅም የለም፡፡ በወጉ ሥልጠና መውሰድና መንጃ ፈቃድ ማውጣትም ቦታ አይሰጠውም፡፡

 የተለየ የሚለማመዱበት ቦታም የለም፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ የተለማመዱት እየወደቁ እየተነሱ፣ እርስ በርስ እየተገጫጩና እግረኛ እየገጩም ነው፡፡ ወደ ሥራው የሚገቡት በቅጡ መንዳት ሳይችሉ፣ የተለያዩ ቴክኒኮችን ሳያውቁ ነው፡፡ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ ብቃቱ ሳይኖራቸው ነገር ግን ትርዒት ለማሳየት የሚሞክሩም ያጋጥማሉ፡፡ ሁኔታው በሕይወት የመቆመር ያህል ነው፡፡ ሠርተው ከሚያተርፉት ገንዘብ ውጪ ሌላ አያሳስባቸውም፡፡ አቧራ ለመከላከል ግንባራቸው ላይ ሸብ ከሚያደርጉት ስካርቭ ውጪ እንደ ሔልሜት ያሉ አደጋ መከላከያዎችን እንኳ አይጠቀሙም፡፡

የችግሮቹ መደራረብ ከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንድታስተናግድ አድርጓል፡፡ ‹‹በሞተር አደጋ ስንት ሰው አለቀ! አደጋ በየቀኑ ነው የሚደርሰው›› አለ ተሰማ (ስሙ ተቀይሯል) በማጋነን እጁን አፉ ላይ አድርጎ፡፡ በቅርበት የሚያውቃቸው ጓደኞቹ ሁሉ ተገቢውን ሥልጠና ሳይወስዱ፣ በቂ ክህሎት ሳይኖራቸው ሞተረኛ ሆነዋል፡፡

እሱም በአንድ ወቅት የሞተር ሳይክል ባለቤት ነበር፡፡ እንደ ማንኛውም የአካባቢው ሰው በኮንትሮባንድ ገብቶ በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጥ ሞተር ነበር የገዛው፡፡ የተለማመደውም ያለማንም ዕርዳታ እየተጋጨ፣ እየወደቀና እየተነሳ በራሱ ነው፡፡ መንጃ ፈቃድ የለውም፣ ሞተሩም ሰሌዳ አልነበረውም፡፡

 ይኼ ግን እሱንም ሆነ ደንበኞቹን የሚያሳስብ አልነበረም፡፡ ዋናው ጉዳይ የሞተር ሳይክል ባለቤት ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ለዳዬ ከተማ ወጣቶች ሞተር መተዳደሪያቸው፣ አለኝ የሚሉት ሀብታቸው፣ ከዚያ ሲያልፍም መኩራሪያቸው ነው፡፡ ነገር ግን ተገቢውን ጥንቃቄ ስለማያደርጉ ብዙዎቹ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ተሰማም በተለያዩ ጊዜያት የሞተር አደጋ አጋጥሞት ያውቃል፡፡ የማይረሳው ግን የፊት ጥርሱን ያጣበትን ነው፡፡ አደጋው በደረሰበት ወቅት እየተጋጨ እየወደቀና እየተነሳም ቢሆን መስመሩን ጠብቆ ማሽከርከር ለምዶ ነበር፡፡ ይሁንና ሌሎች አዲስ ለማጅ የሆኑ ሞተረኞች ድንገት መስመር ስተው በመግባት አደጋ የሚፈጠርባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ እንዲህ ባለ አጋጣሚ ነበር ተሰማ የማይረሳው አደጋ ያጋጠመው፡፡

ከዓመታት በፊት ነው፡፡ ወደ አንድ ቦታ በሞተሩ እየሄደ ሳለ ድንገት መስመሩን ስቶ ከገባበት ለማጅ ሞተረኛ ጋር  ተላተሙ፡፡ ‹‹ሞተሬ ከእግሬ ሥር በራ ሄደች፡፡ እኔ ደግሞ ወደ ላይ ተወረወርኩኝና በአፍጢሜ ከአስፋልቱ ጋር ተጋጨሁ፤›› ሲል እንደ ፊልም የሚታየው ትውስታውን በስሜት ሆኖ አወሳ፡፡ ሞተር ሳይክሉ መተዳደሪያው፣ ከሌሎች ጓደኞቹ እኩል ሆኖ የሚታይበት መመኪያው ነበረ፡፡ እንዲህ በቅጽበት ሕይወቱን ሊያሳጣው እንደሚችል ቢያውቅም ሞተረኛ መሆኑ ያኮራው ነበር፡፡

ብዙም ሳይጠቀምበትና ወረቱ ሳይወጣለት የቅርብ ጓደኛው ለሥራ ተውሶት በዚያው ሞተሩን ይዞ ጠፋ፡፡ ሰሌዳ የለው፣ ሌላ የተመዘገበ ሕጋዊ መረጃ የለው፣ ሞተሩን መልሶ ማግኘት አስቸጋሪና የማይታሰብ ሆነበት፡፡ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ሊከሰት እንደሚችል አልጠረጠርም ነበር፡፡ ገዝቶ ለመተካትም ሆነ በሌላ ሥራ ለመሰማራት አልቻለም፡፡ ከሞተሩ የቀረው ነገር ቢኖር ገላው ላይ ያሉት ጠባሳዎችና የወለቀው የፊት ጥርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹መቼም የሚገኝ አይመስለኝም›› ብሎ ያደፈ ሽርጡን አስተካክሎ ተከናንቦ ዓይኑን አስፋልቱ ላይ ውር ውር ወደሚሉት ሞተረኞች ላከ፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች የትራፊክ አደጋ ሰለባ በሆኑ ታካሚዎች መጨናነቃቸውን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ምን ያህል እውነት መሆኑን ለማረጋገጥም በቅርበት ወደ ሚገኘው ዳዬ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ለመሄድ ወሰንን፡፡ ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ ባለመኖሩ ሞተረኛ ለመያዝ ተገደድን፡፡ የሚሠሩበት ወጥ የሆነ ታሪፍ የላቸውምና በ20 ብር ሊያደርሰን ተስማማን፡፡

ሞተሩ ላይ ከመፈናጠጣችን በፊት በጀርባችን አዝለን የነበረው ቦርሳ ቦታ እንዳይዝ ሞተረኛው ተቀብሎን እንደ ሕፃን ልጅ በደረቱ አዙሮ አነገተው፡፡ ከዚያም በአንድ ሞተር ላይ ሦስት ሆነን በአቋራጭ መንገድ ጉዞ ጀመርን፡፡ መንገዱ ወጣ ገባና ለጉዞ የማይመች ዓይነት ነው፡፡ በተለይ መንገዱ ላይ የነበረችውን የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ስናልፍ የምንወድቅ መስሎን ነበር፡፡ አደጋ ሳይደርስብን እንወርድ ይሆን በሚለው ሐሳብ ስለተያዝን እንደ ጢስ የሚበነው አቧራ አልታወቀንም፡፡ ከአፍታ በኋላ ግን ተላመድነው፡፡ ጭንቀቱም ረገብ አለልን፡፡

በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኘው ሞተረኛው ሽብሩ (ስሙ ተቀይሯል) ይባላል፡፡ ሁለት ሞተሮች አሉት፡፡ አንዱን የሚይዝለት ጓደኛው ነው፡፡ እሱ የያዛት ደግሞ ከቀናት በፊት የገዛት አዲስ ሞተሩን ነው፡፡ ሁለቱም ሞተሮቹ ሰሌዳ የላቸውም፡፡ ሞተር መንዳት ከጀመረ ዓመታት ቢያስቆጥርም እስካሁን መንጃ ፈቃድም  አላወጣም፡፡ የማውጣት ሐሳብ ያለውም አይመስልም፡፡

 ‹‹አንድ ሞተር ታርጋ ካለው ጥፋት ሠርቶ ከትራፊኮች ማምለጥ አይቻልም፡፡ በቀላሉ ሊይዙንና ሊቀጡን ይችላሉ፡፡ ታርጋ ከሌለው ግን ማምለጥ ቀላል ነው፡፡ ለዚህም ሁሉም ሞተሮች ታርጋ የላቸውም፡፡ ታርጋ ያላቸው ባለ ሦስት እግር ባጃጆች ናቸው፡፡ እነሱም በሆነው ባልሆነው ስለሚቀጡ ተማረዋል፤›› ሲል ሰሌዳ ማውጣት በቀላሉ ለቅጣት ያጋልጣል ብሎ ስለሚያምን ሞተሩን ሕጋዊ የማድረግ ፍላጎት እንደሌለው ይናገራል፡፡

ትርፍ መጫን ከ800 እስከ 1000 ብር የሚያስቀጣ ቢሆንም የዳዬ ሞተረኞች ግን ትርፍ ያለመጫን የሚያስቀጣ እስኪ መስል ድረስ፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችን ሳይቀር ደራርበው ጭነው ይከንፋሉ፡፡ ነገር ግን ትራፊክ የማይኖርባቸው አቋራጭ መንገዶችን ስለሚጠቀሙ የሚቀጡት ከስንት አንዴ ነው፡፡ ‹‹ትራፊኮች አስፋልት ላይ ብቻ ነው የሚሆኑት፡፡ እኛ ደግሞ ትርፍ ስንጭን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እንጠቀማለን፤›› ሲል ከትራፊኮች ጋር የሚያደርጉትን ድብብቆሽ ሽብሩ ይገልጻል፡፡

እንዲህ ሕጉን ተላልፈው የሚያሽከረክሩበት ሁኔታ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣቸው ይገኛል፡፡ ነገር ግን በእሳት የመጫወትን ያህል ከባድ ከሆነው ድርጊታቸው የመታረም ፍላጎት የላቸውም፡፡ ‹‹በማንኛውም ሰዓት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እኔ ተጠንቅቄ ብነዳ ሌላው አይጠነቀቅም፡፡ ከለማጅ ጋር ድንገት ልላተም እችላለሁ፡፡ ስለዚህም ከቤት ስወጣ ሁሌም እፀልያለሁ፡፡ ሌላ ምንም ማድረግ አይቻልም፤›› የሚለው ሽብሩ በአንድ ወቅት ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ ላይ ያለን አንድ ታዳጊጊ ክፉኛ ገጭቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች አብዛኛውን ጊዜ በአሽከርከሪውና በተጎጂው ወገን መካከል በሚደረግ ድርድር ይቋጫል፡፡ ሽብሩም በወቅቱ ለታዳጊው ቤተሰቦች 5,000 ብር ካሳ በመስጠቱ ጉዳዩ ወደ ሕግ ሳይደርስ እንዲቀር ማድረጉን ይናገራል፡፡

ዕድለኛ ሆኖ እስካሁን በራሱ ላይ አሰቃቂ አደጋ ባያጋጥመውም ጥቂት የማይባሉ እንደሱ ያሉ ሞተረኛ ጓደኞቹ በትራፊክ አደጋ ለቀላልና ከባድ አካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ አንድ የቅርብ ጓደኛውን ደግሞ በሞት ተነጥቋል፡፡ ሪፖርተር ባነጋገረው ወቅትም ሌላ ጓደኛው አለታ ወንዶ በሚባል ቦታ በደረሰበት የግጭት አደጋ ሕይወቱን አቷል፡፡

‹‹በአካባቢው ከሚታሰበው በላይ የሞተር አደጋዎች ይበዛሉ፤›› ያሉት በዳዬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል አስተባባሪው ዶ/ር ሔኖክ ደስታ ናቸው፡፡ ቢያንስ በቀን ሁለት አዳዲስ የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ ይሄዳሉ፡፡ በጥንቃቄ ስለማያሽከረክሩ አደጋ መከላከያ ሔልሜት ስለማያደርጉ በቀላል ግጭት ለከባድ ጉዳት እንደሚዳረጉ ዶ/ር ሔኖክ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከከፍተኛ የጭንቅላት ጉዳት ከደረሰባቸው ጀምሮ የሥሥ ጡንቻዎች ጉዳት የደረሰባቸው ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፤›› የሚሉት ዶክተሩ በሆስፒታሉ አቅም የሚቻላቸውን የመጀመሪያ ዕርዳታ ካደረጉላቸው በኋላ ከአቅም በላይ የሆኑትን ወደ ዲስትሪክት ሆስፒታል እንደሚልኩ ይናገራሉ፡፡

በሆስፒታሉ ማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች አክመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁሌም እንደ አዲስ ከፊታቸው የማይጠፉትን እንዲህ አስታውሰዋል፡፡

አንድ ሞተረኛ መስመሩን ስቶ በእግረኛ ላይ የግጭት አደጋ ያደርሳል፡፡ በግለሰቡ ላይ የደረሰው አደጋ ቀላል አልነበረም፡፡ ከዚህ ቀደምም አይተውት የማያውቁት ዓይነት ነበር፡፡ በደረሰው ግጭት እግረኛው የግንባሩ ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ተነሳ፡፡ በሰውየው ላይ የደረሰውን ጉዳት ዶ/ር ሔኖክ ሲያዩ ለማከም እስኪቸገሩ ደንግጠው ነበር፡፡

ሌላው ተሳፋሪ ጭኖ ሲበር በነበረ ሞተረኛ ላይ ያደረሰው አደጋ ነው፡፡ አደጋው የተከሰተው ፍሬን በመበላሸቱ ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ፍሬን እምቢ ያላቸው አደገኛ ቦታ ላይ ነበር፡፡ ሞተሯ ቁልቁል ከፊታቸው ወደ ነበር ሐይቅ ተወረወረች፡፡ ነገሮች በቅፅበት እንዳልነበሩ ሆኑ፡፡ ከመንገደኛው የበለጠ ጉዳት የደረሰበት በአፍጢሙ ሐይቅ ውስጥ የወደቀው ሞተረኛው ነበር፡፡ የፊት ጥርሶቹ ድዱ ውስጥ ተቀበሩ፡፡ በሞተር አደጋ አንጎላቸው የፈሰሰና ሌላም አሰቃቂ አደጋ የደረሰባቸው የሞት አፋፍ ላይ ሆነው ወደ ሆስፒታሉ የሚላኩ በየጊዜው እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡

 ስለትራፊክ አደጋ እየተንገፈገፉ የሚናገሩት ዶ/ር ሔኖክ ራሳቸው ቀላል የሚባል ቢሆንም በአንድ ወቅት መስመር በሳተ ሞተር ተገጭተው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

‹‹በብዛት የሚያሽከረክሩት ሕፃናት ናቸው፡፡ ሞተሩን የሚገዙትም የወላጆቻቸውን መሬት፣ ከብትና ቡና አሽጠው ነው፤›› የሚሉት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ በረከት አመሎ ብዙዎቹ ሞተረኞች የተለያዩ ቴክኒኮችን እንደማያውቁና የተወሰኑትን በግላቸው ለማስተማር ሞክረው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ በረከት ያሉ አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ሥልጠና የወሰዱት በከተማው በሚገኘው በብቸኛው በሲዳማ ኔት የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱ መሀል ከተማ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ብዙዎቹ የሚያውቁት አይመስልም፡፡ ግቢውም ቢሆን ትምህርት ቤት አይመስልም፡፡ ፀጥ ረጭ ያለ ነው፡፡

 የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተር ወጣት ኃይሉ ሀዬሶን ለማግኘት እየተጣራን እስከ ድርጅቱ የኋለኛው በር ድረስ መግባት ነበረብን፡፡ ከአንድ የሥራ ባልደረባቸው ጋር የተለመዱ የኮምፒውተር ጌሞችን ሲጫወቱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ ከሁለቱ በስተቀር ግቢ ውስጥ ሌላ ማንም አልነበረም፡፡

 ማሠልጠኛ ተቋሙ ሥራ የጀመረው 2007 ዓ.ም. ላይ ነበር፡፡ ሥልጠናው በ15 ቀን የመስክ፣ በአራት ቀን የኮምፒውተር እንዲሁም በሰባት ቀን የክፍል ትምህርት የሚጠናቀቅ ሲሆን አጠቃላይ ክፍያው 1,600 ብር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጠናው ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ቢሆንም ፍላጎቱ ኖሯቸው የተማሩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

እንደ ኃይሉ ገለጻ፣ ማሠልጠኛው ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ በበንሳዳዬ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ሥልጠናውን የወሰዱት 37 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነሱም ውስጥ አብዛኛዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ጀምረው ያቋረጡ ናቸው፡፡ የሚያስገርመው ነገር ሥልጠናውን በተገቢው መንገድ አጠናቀው መንጃ ፈቃድ የወሰዱ ሠልጣኞች አራት ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ወጣቶቹ ለመማር ፍላጎት የላቸውም፡፡ ይኼንንም በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርት አድርገናል፤›› ይላል፡፡

ሳጅን ልባርጌ ጫሚሶ የዳዬ ከተማ የትራፊክ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በዳዬ ከተማ ያለው የባለ ሁለት ጎማ ባጃጆች ብዛት 332 ነው፡፡ ይሁንና ከተማው በዙሪያው ላሉ አምስት ወረዳዎች (አርበጉና፣ ጭራ፣ አሮሬሳ፣ ቦና፣ ቦርሳ) ማዕከል በመሆኑም በወረዳዎቹ ያሉት እስከ 7,000 የሚደርሱ ሞተሮች በሙሉ ውሏቸው በዳዬ ነው፡፡

በከተማው በብዛት የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ በሞተሮች የሚደርስ ነው፡፡ የሕግ ግንዛቤ ዕጥረት ዋናው ችግር ነው፡፡ አደጋ በብዛት የሚከሰተውም በሳምንት ውስጥ ባሉት ሁለት የገበያ ቀናት ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት የትራፊክ ፍሰቱን ለመቆጣጠር ያለው የትራፊክ ፖሊስ ኃይል ብቻ በቂ ባለመሆኑ የፀጥታ ተቆጣጣሪዎች ጭምር በሥራው እንደሚሠማሩ ሳጅን ልባርጌ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በማኅበር በማደራጀት (ስምንት ማኅበራት አሉ) በየ15 ቀኑ የአሽከርካሪዎች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ከፍጥነት በላይ እንዳያሽከረክሩ፣ ትርፍ እንዳይጭኑ፣ ከመስመር ወጥተው እንዳያሽከረክሩና በመሳሰሉት ዙሪያ ነው ሥልጠናው የሚያጠነጥነው፡፡ ይሁንና በሥልጠና ያገኙትን ተቀብሎ ሥራ ላይ ከማዋል አንፃር ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ‹‹ልጆቹ ገና ወጣትና ትኩስ ኃይል ናቸው፡፡ የመቀበል ዕድላቸው ግማሽ በግማሽ ነው፤›› ሲሉ ሳጅን ልባርጌ ክፍተቱን ለመሙላት የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው መጠን ፍሬያማ እየሆነ እንዳይደለ ተናግረዋል፡፡

‹‹ልጆቹ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ በግድ እንደ ወንጀለኛ ተጎትተው ነው የሚማሩት፡፡ በዚህ ሲባሉ በዚያ የሚያመልጡ ናቸው፤›› በማለት ያለው የግንዛቤ ክፍተት ችግሩን ለመቅረፍ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በከተማው የተንሰራፋውን ሰሌዳ አልባ ባጃጆችን የማሽከርከር ባህል በሕጋዊ ለመቀየር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ መንግሥት ለባጃጆቹ ታርጋ ለመስጠት መረጃ ጠይቆን ሠተናል፡፡ የተወሰኑት ሞተሮች አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

አሶሴሽን ፎር ሴፍ ኢንተርናሽናል ሮድ ትራቭል የተባለ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ በየዓመቱ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህም በየቀኑ 3,257 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ ማለት ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የአደጋው ሰለባዎች ወጣች ናቸው፡፡ አመዛኙ አደጋ የሚመዘገበውም በታዳጊ አገሮች ነው፡፡ ቀዳሚዋ ደግሞ አፍሪካ ነች፡፡

 አፍሪካ ከሌሎቹ የዓለም ክፍሎች በተለየ 24 በመቶ ለአደጋው ተጋላጭ ነች፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚከሰተውም በአፍሪካ ነው፡፡ ይሁንና ከሌላው ዓለም አንፃር በአፍሪካ ያለው የተሽከርካሪ ብዛት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለመቶ ሰዎች ያለው የተሽከርካሪ ድርሻ ከአንድ በመቶ ያነሰ ነው፡፡

በአውሮፓ አገሮች በ100,000 ተሽከርካሪዎች የሚደርሰው አደጋ ሁለት ብቻ ነው፡፡ በአፍሪካ ለምሳሌ በኬንያ በ100,000 ተሽከርካሪዎች 19 አደጋዎች ይደርሳሉ፡፡  በትራፊክ አደጋ ብዛት ከዓለም 12 ደረጃ ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ ደግሞ በ10,000 ተሽከርካሪዎች 60.4 አደጋዎች ይደርሳሉ፣ከአመታት በፊት በ 10000 ተሸከርካሪዎች 124 አደጋዎች ይመዘገቡ ነበር፡፡

 በአገሪቱ የሚከሰቱት 68.3 በመቶ የሚሆኑት አደጋዎች በተመቹ መንገዶች የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ አብዛኛው አደጋ የሚደርሰውም በአሽከርካሪው ስህተት ነው፡፡ 85.9 በመቶ በአሽከርካሪው፣ 3.3 በመቶ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶ በእግረኛ ችግር እንዲሁም 0.7 በመቶ ደግሞ በመንገድ ችግሮች የሚከሰቱ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ አደጋዎች የሚከሱቱባቸው ምክንቶች የአሽከርካሪው የሥነ ምግባር ጉድለት ማለትም፣ በፍጥነትና በቸልተኝነት ማሽከርከር፣ የሥልጠና መጓደልና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ጠጥቶና ቅሞ ማሽከርከር፣ በቂ እረፍት ሳያገኙ ለሰዓታት መንዳት፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የመንገዶች መዘጋት፣ የመንገድና የትራፊክ መብራቶች አለመኖር በኢትዮጵያ የብዙዎችን ሕይወት እንዳልነበር እያደረገ ለሚገኘው የትራፊክ አደጋ መንስዔ ናቸው፡፡

አቶ ዮሐንስ ለማ፣ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የመንገድ ደኅንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በ2008 ዓ.ም. ብቻ ከ4,300 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከ12,000 በላይ ደግሞ ለቀላልና ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በዚሁ ዓመት በትራፊክ አደጋ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ በአገሪቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ላይ እስከ አንድ በመቶ ኪሳራ እንደሚያደርስ ይገመታል፡፡

ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚመዘገበውም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ  ነው፡፡ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር፣ ያለው የትራፊክ ፍሰት ከፍተኛ መሆንና የመንገድ አለመመቸት በክልሎቹ እየታየ ላለው ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ መመዝገብ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በእነዚህም ምክንያቶች እየተከሰተ ያለው የትራፊክ አደጋ በየቀኑ በርካቶችን ለሞት፣ ለቀላልና ለከባድ የአካል ጉዳት እየዳረገ ይገኛል፡፡ የጤና ተቋማቱ የድንገተኛ ሕክምና መስጫ ክፍሎች አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ በደረሰባቸው ሰዎች እንዲሞላ እያደረገ ይገኛል፡፡ የአደጋው ሰለባዎች ራሳቸውን ችለው እንዳይንቀሳቀሱ፣ ሠርተው እንዳይኖሩ፣ ከቤተሰቦቻች ጋር እንዲቸገሩ ሆኗል፡፡ እንደወጡ የቀሩም ብዙ ናቸው፡፡

የትራፊክ አደጋ አይደርስብኝም ጠንቃቃ ነኝ ብሎ እምነት ማሳደር ከማይቻልበት ደረጃ ላይም ተደረሧል፡፡ ለዚህም መስመር ስተው በሰዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚወጡ ተሸከራካሪዎችን መመልከት በቂ ነው፡፡ የአደጋው አስከፊነት ወላጆች ተረጋግተው እንዳይኖሩ አድርጓል፡፡ የመኪና ድምፅ በሰሙ ቁጥር ልጄን ብለው የሚበረግጉ ብዙ ናቸው፡፡ በትራፊክ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡና አዕምሯቸውን የሳቱም ያጋጥማሉ፡፡

አደጋውን ካደረሱ በኋለ በዚያው የሚሰወሩ አሽከርካሪዎች መኖር ደግሞ እስከቅርብ አመታት ድረስ ተጎጂዎች ተገቢውን ህክምና እንዳያገኙ ያደርግ ነበር፡፡ ይህ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ መልክ ይዟል፡፡ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መጠን በድንገተኛ ሕክምና 2,000 ብር በተመላላሽ ለሚታከሙ ደግሞ እስከ 40,000 ብር የሚደርስ ህክምና ተጎጂዎች ያገኛሉ፡፡

 ይህ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል ሆስፒታሎች የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸውን ዓለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያክሟቸው የሚያስገድድ ነው፡፡ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲም ተገቢውን በጀት ይዞ ገንዘብ እያሠራጨ ይገኛል፡፡ ይሁንና በግንዛቤ ችግር ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ ፈንዱን በተገቢው እየተጠቀሙት አለመሆኑን በመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የለውጥ ሥራ አመራርና መልካም አስተዳደር ኃላፊ አቶ ዳዊት አያሌው ይናገራሉ፡፡

በቅጽበት ጊዜ ውስጥ የብዙዎችን ሕይወት እንዳልነበር እያደረገ የሚገኘው የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እያደረሰ ካለው ችግር አንፃር እየተሰሩ ያሉት ስራዎች በቂ አለመሆናቸውን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይህንን አገራዊ ችግር ለመቆጣጠር በኤችአይቪ ላይ የተደረገውን ዓይነት ጠንካራ ዘመቻ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ከጥር 18 እስከ ግንቦት 2009 ዓ.ም. የሚቆይ የትራፊክ አደጋን መቀነስ አላማው ያደረገ አገራዊ ንቅናቄም ተጀምሯል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የበጀት አመትም በ10,000 ተሽከርካሪዎች የሚደርሰውን አደጋ ወደ 21 ዝቅ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ይሁንና እንደ ዳዬ ያሉ የተለየ የትራፊክ ችግር ባለባቸው ቦታዎች የተለየ ትኩረት አድርጎ መሥራት ግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም በዳዬ የሚታየው ነገር በመላ አገሪቱ የትራፊክ ሥርዓት እንዲከበር የተለያዩ ቁጥጥሮችን ማድረግ ብቻ ሳይሆን የትራፊክ ሕግ በወሬ እንጂ በተግባር በማይታወቅባቸው ቦታዎች እንዲከበር ከዜሮ መጀመር እንደሚያስፈልግም የግድ እንደሚል ጥርጥር የለውም፡፡