HISTORY

የትግራይ ሴቶችና የህወሓት ስኬት -የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ

By Admin

March 31, 2017

የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ በህወሓት ዓላማ ዙሪያ ተደራጅቶ የታገለው፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበሩ፣ ብሔራዊ መብቱን ለማረጋገጥ፣ ማህበራዊና ኦኮኖሚያዊ ለውጥ በማምጣት በአጠቃላይ ደግሞ የነበረውን ስርዓት ከመሠረቱ ለመለወጥ ነው። በትግሉ ሁሉም የትግራይ ህዝብ በህወሓት አላማ ተደራጅቶ በፅናት ታግሏል፤ ክቡር መስዋዕትነትም ከፍሏል። የትግራይ ሴቶችም እንደ ግማሽ የትግራይ ህዝብ  አካል እንደመሆናቸው በትግሉ የድርሻቸውን ፈፅመዋል።

ህወሓት ከምስረታው ወቅት ጀምሮ የሴቶችን እኩልነት የማረጋገጥ አላማ ይዞና በፕሮግራሙም አስፍሮ የተነሳ ድርጅት ነው። ህወሓት ያለ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ የትግራይ ህዝብ ትግል ለድል አይበቃም የሚል ፅኑ እምነትም ይዞ ታግሏል። ከዚህ እምነት በመነሳት ከትግሉ መጀመር አንስቶ የትግራይ ሴቶች ወደ ትግሉ እንዲሠለፉ መርቷል።

የትግራይ ሴቶች በሁሉም የትግሉ አውዶች እየገቡ በፅናት ታግለዋል። በሠራዊት ውስጥ ገብተው ተዋግተዋል፣ አዋግተዋል፣ ተሠውተዋል፣ ቆስለዋል፤ ጠላትን አሸንፈዋል። ደጀን ላይ ሆነውም የቆሠለ አንስተው አክመዋል፣ መረጃ አቀብለዋል። ልጆቻቸውን አሳድገው ለትግል አሰልፈዋል። ትምህርት፣ ህክምና፣ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ተቋም ለመመስረት በተደረገው ጥረት እንዲሁም ማህበራዊ ለውጦች እንዲመጡም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

የትግራይ ሴቶች በትግሉ መሳተፍ የጀመሩት የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል በጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራቶች ነው። በከተማ የነበሩ ሴቶች በህቡዕ ስምሪት ተሳትፈዋል። በገጠር የነበሩት ደግሞ ታጋዮችን እየመገቡ፣ የጠላትን መረጃ እየሠጡና የትግሉን ሚስጢሮች እየጠበቁ የትግራይ ህዝብ ትግል በእግሩ እንዲቆም ተረባርበዋል።

በዚህ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ሴቶች መካከል አንዷ ደሃብ ተስፋይ ነች። ደሃብ ተስፋይ በ1935 ዓ.ም በምዕራብ ትግራይ በዓዲነብሪኢድ ወረዳ ተወለደች። እንደ ልጅ ተጫውታ ሳትጠግብ በዘጠኝ ዓመቷ ተዳረች። ያለዕድሜዋ በማግባቷ ምክንያት በትዳር ላይ ጥላቻ አድሮባታል። ወደደችም ጠላችም በትዳር መቀጠል ስለነበረባት አማራጭም ስላላገኘች በ15 ዓመቷ አንድ ልጅ እስከትወልድ ደረስ በትዳር ቆየች። ኋላ ላይ ግን ከባሏ ተፋትታ ወደ ወላጆቿ ተመለሠች።

ደሃብ በዘጠኝ ዓመት ዕድሜዋ ተድራ በ15 ዓመቷ መፋታቷ በብዙዎቹ የገጠር አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በትግራይ ሴቶች ህይወት የሚታይ መራራ እውነት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የሚደርስባቸው መደባዊና ብሔራዊ ጭቆና፣ እንዲሁም ከቤተሰብና ከትዳር አጋር የሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት ወሰን አልነበረውም። እንደ ዜጋ የመሬት ባለቤት መሆን የማይችሉና ከመሬት ከሚገኘው ምርት ተጠቃሚ አልነበሩም። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም ከፍተኛ በሆነው ባህላዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ ይገደዱ ነበር። ይህ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የበታችነት የትግራይ ሴቶችን ኑሮ መራራና አስከፊ እንዲሆን አድርጐታል። ደሃብ ተስፋይ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የእነዚህ ጭቆናዎች ሠለባ ነበረች። ከመጀመሪያ ባሏ ከተፋታች ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ በ17 ዓመቷ ሁለተኛ ባል አገባች። ከሁለተኛ ባሏ ሰባት ልጆች አከታትላ ወለደች። በትዳሯ ደህና የሚባል መሬትና ሀብት ቢኖራትም የእኔ ነው የምትለው ንብረት ግን አልነበረም ።

በዚህ ሁኔታ እያለች ነበር የትግራይ ህዝብ ትግል የተጀመረው። ባለቤቷ አቶ ይርጋአለም ገብረማርያም በ1967 ዓ.ም በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጋዮች ጋር ተዋወቁ። ለታጋዮች ምግብ ማቅረብ፣ መንገድ መምራት፣ መረጃ ማቀበልን የመሳሰሉ ድጋፍ እየሠጡ ከቆዩ በኋላ በግንቦት ወር 1967 ዓ.ም የትግሉ መደበኛ አባል ሆኑ።

ከዚህ በኋላ የአቶ ይርጋአለም ባህሪ ፍጹም እየተቀየረ መጣ። አስተሳሰባቸው ሆነ ተግባራቸው እንደ ታጋዮች ሆነ። ቀደም ሲል በሚስታቸው ላይ ያደርሱት የነበረውን ጭቆና ትተው ባለቤታቸውንና ትዳራቸውን ማክበር ጀመሩ። ይህ ሲሆን ደሃብ ስለ ህወሓት ታጋዮች አታውቅም፤ የምታውቀው ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው ታጣቂዎች መሆናቸውን ብቻ ነበር። እየዋለች እያደረች ግን ለሴቶች የሚጠቅም አላማ የያዙ መሆናቸውን እየተገነዘበች መጣች። ታጋዮች በረሃብ፣ በእርዛትና በችግር ሰውነታቸውን ጐድተው በየበረሀው የሚውሉበት ዓላማ እሷንም የሚመለከት መሆኑን ተረዳች።

ከዚህ በኋላ እሷም እንደ ባለቤቷ የትግሉ አካል ሆነች። ምግብና ውሃ ከማቅረብ ባሻገር ሚስጢራዊ መልዕክቶችን ይዞ ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ የማድረስ ተልዕኮ ጀመረች። ባለቤቷም ጠንካራ ታጋይ ሆነው መንቀሳቀሳቸውን ቀጠሉ። ሆኖም ብዙ ሳይቆዩ በ1969 መጨረሻ ላይ በተሓህትና ኢድሕ መካከል በተካሄደ ጦርነት በክብር ተሠው።

ደሃብ ከባለቤቷ መሰዋት በኋላ ይበልጥ ጠነከረች። መጀመሪያ ኢድሕ ቀጥሎ ደግሞ ደርግ እየተቀያየሩ ሀብቷንና ንብረቷን ቢዘርፏትና ቢያቃጥሉባትም፤ ብሎም የተለያዩ ግፎችን ቢያደርሱባትም በዚህ ተሸማቅቃ ከትግሉ አልተለየችም። በአንድ በኩል ልጆች እያሳደገች በሌላ በኩል ደግሞ የትግሉን ሥራ እየሠራች ከቆየች በኋላ ለትግል የደረሱ ልጆቿን መርቃ በትግሉ እንዲሳተፉ አዘመተቻቸው። ከፊል፣ ዘመመሽ፣ አባዲ፣ ማሚት፣ ድራር፣ ለገሠ፣ ፍፅምቲ፣ ፍትሃ ነገስት የተባሉ ስምንት ልጆቿን ለትግሉ አበርክታለች።

በዚህ ሁኔታ ከመላው ቤተሰቦቿ ጋር የታገለችው ደሃብ ተስፋይ ማህበራት ሲቋቋሙ የሴቶች ማህበር ሠብሳቢ ሆና ሴቶችን በማነሳሳት፣ ሴቶች አስተባብራ በአውደ ውጊያ እየገባች ቁስለኞችን በማንሳትና በመንከባከብ መሪ ሆና ታግላለች። በ1976 ዓ.ም ደግሞ የሸንጐ ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በማቋቋም ሂደት በትጋት መሳተፏን ቀጠለች።

የትግራይ ህዝብ ትግል እንደ ደሃብ ያሉ ብዙ ታጋዮች አፍርቷል። የትግራይ ሴቶች የትግራይ ህዝብ ትግል ለድል እንዲበቃ ያልሠሩት ተአምር የለም። እማማ ነጂያ ቢተው ከብዙዎቹ አንዷ ናቸው። እነ እማማ አለማሽ ተክሉ፣ ጠዓሞ መሐመድ፣ እማማ ፀሃይዩ ፍቃዱ፣ እማማ አምለሱ ዕዳጋ ዓርቢ፣ አበባ ገብረ ስላሴ /አበባ ፎሮ/፤ እማማ  ሻሹ ደላ፣ አልጋነሽ አምበራ፣ አምለሱ እንዳባፃሕማ፣ አሚና ዓዲት፣ ዛህራ በራህለይ፣ ራሕማ፣ ንግስቲ አበርገለ፣ ታቦቱ እምባሰ ነይቲ፣ ፀጋ ሳምረ፣ ሮማኖ፣ ተበርህ ፍትሒ ባይቶና ሌሎችም መሪዎች ሆነው ታግለዋል።

የትግራይ ሴቶች የህወሓት አላማዎችን ከግብ ለማድረስ በሚችሉት ሁሉ ታግለዋል፣ ክቡር መስዋዕትነትም ከፍለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደጀን ላይ የታጋዮችን ስንቅና ትጥቅ በማሟላት፣ ሸንጎና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በማቋቋም፣ መረጃ በመሰብሰብና የድርጅቱንና የትግሉ የሚጠይቃቸውን ተግባራት እንዲሁም ፖለቲካዊና የህቡዕ ስምሪት ሥራዎችን ሠርተዋል። ከዚህም ባለፈ መሣሪያ አንግበው በትጥቅ ትግሉ በቀጥታ በመሳተፍ ታግለዋል።

የሌላ ብርቱ ሴት ታጋይ ታሪክ ደግሞ ይኸው፡- ከትግራይ ሴቶች መካከል ማርታ /ካሕሳ ተስፋይ/ ተጠቃሽ ናት። ማርታ በሚባል የትግል ስም በታኅሳስ ወር 1968ዓ.ም ወደ ህወሓት ትግል የተቀላቀለችው ካሕሳ ተስፋይ፣ ወደ ትግሉ ስትቀላቀል የ18 ዓመት ልጃገረድ ነበረች። ማርታ በህወሓት የትጥቅ ትግል ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ታጋይ ከመሆኗ በተጨማሪ አራት ዓመታት ብቻ በቆየችበት ትግል ምርጥ አብነት ሆና ያለፈች ታጋይ ነች።

በትግሉ ከገባችበት ወቅት ጀምራ ከኢድሕ፣ ደርግና ኢህአፓ ጋር በተካሄዱ ውጊያዎች በከፍተኛ ጀግንነት ግዴታዋን ፈጽማለች። በኋላም ታህሳስ 10 ቀን 1972 ዓ.ም ሽሬላ በተባለ አካባቢ ከኢህአፓ ጋር በተካሄደው ውጊያ ክቡር መስዋዕትነት የከፈለች ጀግና ናት።

የማርታን ፈለግ ተከትለው ህይወት ላፍላፍ፣ ሮማን ገብረስላሴ፣ ይብራለም አለማየሁ፣ ሕሪይቲ ጓል ቀሺ፤ አረጋሽ አዳነ፣ ፀሀይነሽ መስፍን፣ ሕርይቲ ምሕረተ አብ፣ ልዕልቲ ሃብተማርያም፣ ገነት ሃይሉ፣ አልጋነሽ ገብረ መድህን፣ የውብማር አስፋው፣ መብራት በየነ፣ ለምለም ሰሑል፣ ምንትዋብ አፅብሃ፣ ፅጌ ሰሎሞን፣ ርግበ ሰሎሞን፣ ዘውዲቱ ካሕሳይ፣ ጓል ዓብዱና የተባሉ ሌሎች የትገሉን ጎራ ተቀላቅለዋል። እነዚህ ታጋዮች የትጥቅ ትግሉ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እያለ ባልተጠናከረበትና በበርካታ ጠላቶች ተከቦ ከፍተኛ ርብርብ በሚያደርግበት ወቅት በፅናት ታግለው የህወሓት ትግል ህልውና በማረጋገጥ ሚናቸውን ተጫውተዋል።

በከተማ ሆነው የትግሉን ሥራ እያከናወኑ እንዲቆዩ የተመደቡት ሴቶች በበኩላቸው በጠላት ጉያ ስር ሆነው የተለያዩ ፖለቲካዊና የህቡዕ ስምሪት ግዳጆችን ተወጥተዋል። በ1970 ዓ.ም የደርግ አፈና እየተጠናከረ ሲመጣ ግን በብዛት ወደ ትግል ሜዳ መግባት ጀመሩ። በዚህ ወቅት ወደ ትግሉ ከተቀላቀሉ ሴቶች መካከል ትረፉ ኪዳነማርያም፣ ቅዱሳን ነጋ፣ ሙሉ ሐጎስ፣ ትዕበ መስፍን፣ አልጋነሽ ገብረመድህን፣ እቴነሽ ሐዱሽ፣ ዘመዳ ሐጐስ፣ አዜብ መለስ፣ አልጋነሽ መለስ፣ ኤልሳ አስፍሃ፣ አስቴር፣ አፀደ ገ/ስላሴ፣ ማሕታ አምባየ፣ ሽሻይ ሃብተስላሴ፣ ኤልሳ ተስፋይ፣ አወጣሽ ወልደጀወርጊስ፣ አኸዛ ብርሃነ፣ ያለም ሃይለስላሰ፣ ሐርነት ዮውሃንስ፣ ብርዛፍ ተስፋሁነኝ፣ ዘውዱ ካሕሳይ፣ ፅገ ሃዋዝ፣ ካሰች አስፋው፣ ሮማን ምሕረተአብ /ሐለፋይ/፣ ሙሉ ባንዲት፣ አስያ ጓል በሽር፣ ማሚት ገ/ሄር፣ ሳባ ተካ፣ ሳባ መጅሙዕ፣ ከበዱ፣ ያለም ስዩም፣ ፅገ ሃይሉ፣ አዜብ በቀለ፣ ፈተለወርቅ ገ/ሄር /ምንጀርኖ/፣ ንግስቲ ገብረ ክርስቶስ፣ ትርፈ አስፋው፣ ግደይ ጓል አዳል፣ ፋለወርቅ ፍፁም፣ መአዛ አለማየሁ፣ አበባ ፍስሃ፣ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

የትግሉን መሠረት በማቆም እና በማጠናከር ደረጃ ክቡር መስዋዕትነት ከፍለው ያለፉ የህወሓት ሴት ታጋዮች ብዙ ናቸው። ወደር የሌለው ጀግንነት ፈፅመው ከተሰዉት መካከል ልዕልቲ፣ አልጋነሽ፣ መብራት ሃይለ፣ አልማዝ አለሙ፣ ርግበ ገ/ሄር፣ አልማዝ ገ/ሄር፣ ዘውዱ ገብረ፣ ብርሽዋ ተጠምቀ፣ ግደይ ገ/ስላሴ፣ በላይነሽ ሃይለስላሴ፣ አመተፅዮን ገብረኪደን፣ ግደይ ነጋሽ፣ አዜብ ረዳኢ፣ኤልሳ ረዳኢ በሺዎች ከሚቆጠሩት መካከል ናቸው።

ከመጀመሪያው ጉባኤ በኋላ ህወሓት በትግራይ ገጠሮች ተቀባይነቱ እየሠፋ በመምጣቱ ወጣት አርሶ አደሮች ወደ ትግሉ መጉረፍ ጀመሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴት አርሶ አደሮችም የህወሓት ሠራዊትን ተቀላቀሉ። በውጤቱም ከህወሓት ታጋይ 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ነበሩ።

እንግዲህ በርካቶቹ ታጋይ ሴቶች ጀግንነታቸው የሚጀምረው ገና ወደትግል ሜዳ ለመሄድ የቆረጡ ጊዜ፣ ገና የሚወዷቸውን ልጆቻቸውን ሊልኩ በልባቸው የወሰኑ ሰዓት፣ ባሎቻቸውም ገና ወደ ትግል ሊሄዱ እንደሆነ ሲያውቁ ፈቃዳቸውን በሰጡበት ቅጽበት ነው። ላመኑበት ነገር እስከምን ድረስ ቆመው እንደሚዘልቁም ከእነዚህ ታጋይ ሴት ታሪኮች ማየት ይቻላል። በእርግጥ ያልሰማናቸውና ያልተነገሩ ብዙ ታሪኮች አሉ፤ ሁሉም ግን አንድ መልዕክት አላቸው፤ ሴት የወንድ ከሚባል የትግል አውድማ መገኘት እንደምትችል ብሎም የድል ቁልፍ መሆኗን።

ሃሴት ፍስሃ፣ «ቅያ ተጋድሎ» በሚል በትግርኛ ከታተመ መፅሃፍ በትርጉም የተወሰደ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/society/item/11323-2017-02-18-19-16-54#sthash.1Dw0iR3V.dpuf