CURRENT

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳዑዲ ጋር የተደረሰውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት አፀደቀ

By Admin

March 11, 2017

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተደረሰውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት አፀደቀ።

አሜሪካ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስዳደር ወቅት አቋርጣው የነበረውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያፀደቀው።

ተንታኞች ሪያድ በየመን በምታደርገው የአየር ላይ ጥቃት ንፁሃንን እየገደለች ነው የሚል ትችት ይሰነዝሩባታል።

ሳዑዲ እና አሜሪካ ባለፈው አመት የ1 ነጥብ 15 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የሳዑዲ የጦር አውሮፕላኖች በየመን በቀብር ስፍራ ላይ ባደረሱት ጥቃት በርካታ ንፁሃን ተገድለዋል በሚል የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱን ውድቅ አድርገውታል።

በስምምነቱ ሳዑዲ ከዋሽንግተን ታንኮች እና ጥይት የማይበሳቸው ተሽከርካሪዎች ለመሸጥ ነበር የተስማማችው።

ሪያድ ከፈረንጆቹ መጋቢት 2015 ጀምሮ በየመን በከፈተችው ዘመቻ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የየመንን ጉዳይ የሚከታተል አጣሪ ቡድን ይፋ አድርጓል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጦር መሳሪያ ሽያጩን ማፅደቁ የትራምፕ አስተዳደር በየመን ጦርነት ከሳኡዲ ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ያሳያል እየተባለ ነው።