Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስተጓጎልና ነዳጅ እንዳዳይገባ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 77 ግለሰቦች ተከሰሱ

0 422

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በክሱ 12 ኤርትራውያን ተካተዋል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆንና ነዳጅ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለማድረግ፣ በኤርትራ ሥልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉ 77 ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ሁሉም ተከሳሾች ከጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ውህደት በመፍጠር ‹‹አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ›› እየተባለ ለሚጠራው ድርጅት አባል በመሆን፣ ዓላማውንና ተልዕኮውን ለመፈጸም ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ወስደው የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ ‹‹አደምዳማት›› በተባለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ማሠልጠኛና ሌሎች ማሠልጠኛ ቦታዎች ገብተው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተለያዩ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ በቡድን ተከፋፍለው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በመሀል ፀገዴ፣ ከምዕራብ አርማጭሆ እስከ መተማ፣ ታችና ላይ አርማጭሆ፣ ወልቃይት፣ መተማና ቋራ ወረዳዎች በመከፋፈል፣ የመንግሥት ሠራተኞችን በማማረር በመንግሥት ላይ ለማሳመፅ፣ ነዳጅ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለማድረግ፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር እስረኞችን ማስለቀቅ፣ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ዓላማቸውን ማስፋፋት፣ ቋራ ላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛና ቤዝ መመሥረትና ሌሎች ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ተዘርዝሯል፡፡

ተከሳሾቹ ለእያንዳንዳቸው 18,000 ብር እና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ተሰጥቷቸው ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሐረና አካባቢ ተነስተው ተከዜ ወንዝን በመሻገር ኅዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ፣ በትግራይ ቃፍታ አድርገው ሁመራ ወረዳ እንድሪስ የተባለ ቦታ ላይ ኅዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር በሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ (የፋይናንስ ኃላፊ)፣ አቶ ነዓምን ዘለቀ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ኮሎኔል ፍፁም (ኤርትራዊ) ለተከሳሾቹ በሰጧቸው ተልዕኮ መሠረት ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ድርጊቶች በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረግና አባላትን በመመልመል ማደራጀት ላይ እንዲሰማሩ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ከተከሳሾቹ መካከል ነዋሪነታቸው ትግራይ ክልል የነበሩት ሚፍታህ ሼክ ሱሩር፣ ግርማ ፈቃደ፣ ለማ እሸቴ፣ ከአማራ ክልል አብርሃም ደርበው፣ ሸጋው ፈንታ፣ ከኦሮሚያ መስፈን ሁሬሳ፣ ከደቡብ ክልል ገረመው ጌታቸው፣ ከኤርትራ እሸቴ ዘለቀ፣ እማዋየው ዘለዓለም፣ ምሥግና ይርጋን ጨምሮ በድምሩ 77 መሆናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ከ77ቱ ተከሳሾች መካከልም 12ቱ ኤርትራውያን ናቸው፡፡reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy