NEWS

የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ድርቅ ተጨማሪ 165 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

By Admin

March 21, 2017

በአውሮፓ ህብረት የዓለምአቀፍ ትብብርና ልማት ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ እንዳስታወቁት በአፍሪካ ቀንድ ኣካባቢ የተከሰተው ድርቅ ላስከተለው ጉዳት ተጨማሪ 165 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ኮሚሽነሩ በደቡብ ሱዳንና በሌሎች የቀጠናው ሀገራት ረሃብ ለተጋረጠባቸውና አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊየን ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚውል መሆኑን ጠቅሰው፤ ፈጣን እርዳታ በተደረገ ቁጥር የሰዎችን ህይወት መታደግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ድጋፉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተመሳሳይ ተግባር እንዲያከናውን ለማሳየት የታለመ ነው ብለዋል ኮሚሽነር ሚሚካ፡፡

በህብረቱ የሰብዓዊ እርዳታና ቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነሩ ክሪስቶስ ስታይሊያኒድስ እርዳታው በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ረሃብ አስከፊ ጉዳት እንዳያደርስ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከአሁኑ እርዳታ ውስጥ 100 ሚሊየን ዩሮው በደቡብ ሱዳን ባለው ብጥብጥ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ የሚውል ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 30 ሚሊየን ዩሮው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለተፈፀመባቸውና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሁም ለሴቶች እና ህጻናት ደህንነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

70 ሚሊየን ዩሮው ደግሞ የደቡብ ሱዳን የሚፈናቀሉ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ጎረቤት ሀገራት ማለትም ለኢትዮጵያ ፣ለኡጋንዳ እና ለኬንያ ድጋፍ ማድረግ የሚስችል ነው ተብሏል፡፡

ህብረቱ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በኬንያ የተከሰተውን ድርቅ ጉዳት እንዳያደርስ 65 ሚሊየን ዩሮውን መድቧል፡፡አሁን የተደረገው ድጋፍ ህብረቱ ባለፈው ዓመት በኢልኒኖ በተከተው ድርቅ ላጋጠመው ጉዳት ያደረገውን 400 ሚሊየን ዩሮ ለማጠናከር ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም ለአዲሱ የሶማሊያ መንግስት ህብረቱ ባለፈው የካቲት ወር ያደረገውን የ200 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ የሚያጠናክር መሆኑን ማሳያ ነው መባሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡