CURRENT

የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ነዋሪዎች ከቆሼ አካባቢ እንዲነሱ እየተደረገ ነው

By Admin

March 13, 2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቆሼ አካባቢ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ አካባቢ የማዛወር ስራ እየሰራ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ።በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከትናንት በስቲያ ምሽት የቆሻሻ ክምር በመናዱ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።በቆሻሻ ክምር መናድ ምክንያት እስካሁን የ46 ሰዎች ህይወት ማለፉ ሲገለጽ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በወቅቱም የከተማ አስተዳደሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ ፖሊስና የአካባቢው ኅብረተሰብ ባደረጉት ርብርብ የበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሕይወት መታደግ ተችሏል።የአደጋውን መጠን የመቀነስ ስራም ተሰርቷል።

የአደጋው መጠን አሁንም ሊጨምር ይችላል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ የአካባቢው ነዋሪዎችን የአደጋ ተጋላጭነት መቀነስ የሚያስችል ስራ ይሰራል ብለዋል።

የቆሻሻ መናድ አደጋ ከደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ሌሎች የአደጋ ተጋላጭ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናግረዋል።የአደጋው ተጎጂዎች ህክምና እየተከታተሉ ሲሆን ህይወታቸውን ያጡ ወገኖች የቀብር ስነ-ስርዓትም ዛሬ ከሰዓት እንደሚፈጸም ይጠበቃል።