NEWS

የእርዳታ አቅርቦት በወቅቱ ለማድረስ እየተሰራ ነው- ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

By Admin

March 08, 2017

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች መንግስት ምግብ፣ ምግብ ነክና የመኖ አቅርቦት በአስተማማኝ ሁኔታ በወቅቱ እንዲደርስ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ድርቅ በተከሰባቸው በደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የምግብ፣ ምግብ ነክና መኖ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የሰው ሕይወት የመታደግ፣ የእንስሳቱን ጉዳት የመቀነስና የእንስሳት ኃብቱን ጠብቆ የመዝለቅ አማራጭ ተይዞ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የዘንድሮው የድጋፍ ፍላጎት አዲስ ካጋጠመው ድርቅና ካለፈው ዓመት ከመጣው የእርዳታ ፈላጊ ህብረተሰብ ጋር የተዳመረ መሆኑን አስታውሰው፤ በሁለቱ ድምር ውጤቶች ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ርብርብና ትኩረት እንደሚጠይቅም ነው የተናገሩት።

መንግስት የድርቁን የጉዳት መጠን ጥልቀትና ስፋት በዝርዝር በማጥናት የአንድም ሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በእንስሳት ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም “በቀጣይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል አቅጣጫ ተግባራዊ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

ድርቁ በተከሰተባቸው በተለይም በኦሮሚያ ቦረና፣ በባሌና ጉጂ ዞኖች ቆላማ አካባቢዎች፣ በሶማሌ ክልል፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ጉዳቱ ከባድ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዘንድሮ በአጠቃላይ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፤ ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለድርቅ አደጋ ቢጋለጡም በራስ አቅም መታደግ መቻሉ ይታወሳል።

መንግስት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅዱን የፕሮጀክቶችና የልማት መርሃ ግብሮች ሳይጎዳ የሚያስፈልገውን ሀብት የመመደብና በወቅቱ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የተዘጋጁ የውሃ ጉድጓዶች በጥልቀት ተቆፍረው ውሃ ቶሎ እንዲወጣ የማድረግና የተለያዩ አማራጮችን የመጠቀም ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ የአርብቶ አደሩን እንስሳት ህይወት ለመታደግ የሚያስችሉ ስራዎችም ተግባራዊ እየሆኑ በመምጣታቸው የሚያበረታታ ውጤት መታየቱን አመልክተዋል።

መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ በተቻለ መጠን ብክነትና ጥፋት ሳይደርስበት ተጠቃሚዎቹ ዘንድ በወቅቱ ለማድረስ የሚያስችል ክትትልና ያንንም ሊያረጋግጥ የሚችል ስርአት መዘርጋቱን አረጋግጠዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ የመንግሥታቱ ድርጅት መጠየቁ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ኢዜአ