CURRENT

የወሰን ማካለል ጉዳይ የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም – ጠ/ሚ ኃይለማርያም

By Admin

March 08, 2017

የወሰን ማካለል ጉዳይ “በምንም ዓይነት የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም” አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።

ሴቶችና ህጻናት በወሰን አካባቢ በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8) አዲስ አበባና ድሬደዋ አስተዳደርን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ሴቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት በማድረግ አክብረዋል።

በዚሁ ወቅት የሁሉም ክልል ተወካይ ሴቶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ጥያቄ አቅርበው ማብራርያ ተሰጥቶባቸዋል።

በወሰን አካባቢ በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ሴቶችና ህጻናት ዋነኛ ተጎጂ በመሆናቸው መንግስት ችግሩን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቧል።

በቅርቡ በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች እሴቶቻቸውን ጠብቀው ለዘመናት በሰላም የኖሩ ቢሆንም በክልሎቹ አመራር አባላት የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ግጭት ውስጥ ሊገቡ መቻላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው አብራርተዋል።

በክልሎቹ ወሰን አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ከሃብት ጋር የተያያዘ ሳይሆን በአንዳንድ አመራር አባላት ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኦሮሚያ ክልል ከትግራይ በስተቀር ከሁሉም ክልሎች ጋር እንደሚዋሰን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለበርካታ ዓመታት በሰላም በኖሩ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ አመራር አባላት መለየታቸውንም አስታውቀዋል።

በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል ምንም ችግር አለመኖሩን ያነሱት አቶ ኃይለማርያም፥ ጥቂት ኃላፊነት የማይሰማቸው ሃይሎች ባደረጉት የተሳሳተ ቅስቀሳ ግጭት እንዲፈጠርና ሴቶችና ህጻናት የበለጠ ተጎጂ እንዲሆኑ ማድረረጋቸውን ጠቁመዋል።

ግጭቶች ሲከሰቱ ሴቶች ካላቸው ተፈጥሮ አኳያ ቀዳሚ ተጎጂ ናቸው፤ ከችግሩ ለማምለጥ ልጆቻቸውንም ጭምር ይዘው ሲሸሹ የከፋ ጉዳት ይደርስባቸዋልም ነው ያሉት።

በኦሮሚያ ክልል ቦረናና ጉጂ ዞን የተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር አብዛኞቹ በህዝቡ ውሳኔ የተከለሉ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም፥ መንግስት የህዝቡን ውሳኔ ወደ መሬት እንዳይወርድ ችግር የሚፈጥሩ አመራር አባላትን የመለየት ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፥ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ችግሩን ለመፍታት በጋራ እየሰሩ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።