Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጪ ንግዱ የገባበት አዙሪትና መውጫው

0 362

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሁለተኛ ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት የግብርና፣ የአምራች ኢንዱስትሪውና የማዕድናት ምርቶች የወጪ ንግድ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ4 ነጥብ 2 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ገልጸዋል። ይህ ቅናሽ ለአለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት የቀጠለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አፈጻጸሙን ለማሻሻልም ከተለመደው ወጣ ያለ መንገድ መከተል እንደሚገባ አመልክተዋል። «በመሆኑም ለሁሉም ዓይነት የወጪ ንግድ ገቢ መቀነስ ጥቅልና ተመሳሳይነት ያላቸው ምክንያቶች እንደሌላቸው ታሳቢ ያደረገና በመንግሥት መዋቅሩ ከታጠረ ግምገማ በመውጣት ዘርፉ ከሚመለከታቸው ተዋንያን፣ ባለሀብቶችና ማህበሮቻቸው ጋር ጥልቀት ያለው ግምገማና አሳሪ ማቆዎችን የመፍታት ጥረት ተጀምሯል» ብለዋል።

በዚህ ረገድ በቅርቡ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ከቆዳና ቆዳ ወጤቶች እንዲሁም ከሥጋና የቁም እንስሳት አምራቾችና ላኪዎች ጋር ውጤታማ ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገልጻሉ። በውይይቱም በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ አብዛኞቹ ነባር ፋብሪካዎች በተሻለ ደረጃ የሚያመርቱም ቢሆንም፤ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በአገር ውስጥ እንዲሸጡ የሚገደዱበትን ምክንያት መፍታት እንደሚገባ  የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህሩ አቶ ታደለ ፈረደ ግን የምርቶች የወጪ ንግድ አፈጻጸም በሁለተኛው ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ደካማ መሆኑን አስታውሰው ችግሩን ለመፍታት መጀመሪያ ምክንያቱ መታወቅ አለበት ባይ ናቸው። በዚህ ረገድ «ለምርቶች የወጪ ንግድ አፈጻጸም እያሽቆለቆለ መምጣት ምክንያቱ ምንድነው የሚለውን መንግሥት ራሱ ያወቀው አይመስለኝም» የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ ችግሩ በስብሰባና በግምገማ የሚመለስ ጉዳይ ባለመሆኑ ጠለቅ ያለ ጥናት እንደሚያስፈልገው ይጠቁማሉ።

እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴር ሁሉም የዘርፍ መስሪያ ቤቶች በወጪ ንግዱ ውስጥ እጃቸውን እንደሚያስገቡ የሚናገሩት አቶ ታደለ «ለመሆኑ የወጪ ንግዱ ባለቤት አለው ወይ» ብለው ይጠይቃሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ዘርፉን በበላይነት ይዞ የሚመራው አንድ ባለቤት ስለሌለው ተጠያቂ የሚሆን አካል እንዳይኖር አድርጓል።

ከሴክተር መስሪያ ቤቶች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዘረጋውና አሁን ሥራ ላይ ያለው መዋቅራዊ አደረጃጀት የተወሳሰበና እንደ «የተቀቀለ ፓስታ» ዓይነት ነው። ማን ምን እንደሚሠራም ለማወቅ የሚያስቸግር መሆኑን ከሁለት ዓመታት በፊት በተሠራ ጥናት ለማሳየት ሞክረን ነበር ይላሉ። በመሆኑም ተደጋጋሚ የሆነውን የወጪ ንግድ ማነቆ ለመፍታት ግምገማና ውይይት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመራ መዋቅራዊ አደረጃጀት ማቋቋም እንደሚገባ ይመክራሉ።

የኢኮኖሚ ባለሙያው «እስከ 1990ዎቹ ድረስ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ኤጀንሲ የሚባል ራሱን የቻለ ተቋም ነበር። መነሻው ምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት በአንድ ደብዳቤ ፈርሷል» ይላሉ። አሁንም ቢሆን ችግሩን መፍታት የሚቻለው በዚሁ መንገድ ዘርፉን በባለቤትነትና በበላይነት የሚመራ፤ ችግር ሲደርስም ተጠያቂ የሚሆንና ኃላፊነቱን የሚወስድ ራሱን የቻለ ተቋም በማቋቋም መሆኑን በመፍትሔነት ያቀርባሉ። የሌሎች አገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይኸው መሆኑን ይናገራሉ።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የጥናትና ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኑረዲን ጁሃር በበኩላቸው፤ የመንግሥትን አሠራር ብቻ ከመገምገም ወጥቶ ባለሀብቱንና የግል ዘርፉን ያሳተፈ አካሄድ መሄድ ያስፈልጋል በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ይስማማሉ። ይሁን እንጅ ይህ ብቻውን በቂ መፍትሔ ይሆናል ብለው አያምኑም።

ባለ ድርሻ አካላቱንና ባለሀብቱን ማወያየቱና ሁሉንም ያሳተፈ ግምገማ ማድረጉ ለችግሩ መፍትሔ በተወሰነ ደረጃ እንደሚያስገኝ  የሚያመላክቱት አቶ ኑረዲን፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ግን ከዚህም ባሻገር ለየብቻ በየዘርፉ ሠፋ ያለ ጥናት መደረግ አለበት ይላሉ።

«በስብሰባ ላይ ብዙ ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት ነው የሚያንፀባርቁት። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የሚነሱት ጉዳዮች ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሔ ላይሆኑ ይችላሉ» የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኑረዲን፤ ጥናት ግን ችግሩን በትክክል ለመለየት ስለሚያግዝ መፍትሔውን የበለጠ ሳይንሳዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ይናገራሉ። ምክንያቱም ጥናት አፈጻጸሙን ብቻ ሳይሆን በፖሊሲ ደረጃም ያሉትን ችግሮች ለማወቅና ፖሊሲውን ለማሻሻል የሚያስችሉ መሠረታዊ ነጥቦችን ለማግኘት ያስችላልና ነው።

ከተለመደው የመንግሥት ባለሥልጣናት ስብሰባና ግምገማ ወጣ ብሎ የግል ዘርፉንና ባለሀብቶችን ያሳተፈ ውይይት ከማድረግ በተጨማሪ በምሁራንና ባለሙያዎች ጥናት የተደገፈ አካሄድን መከተል እና ተጠያቂነት ያለው ተቋም እንዲኖር ማድረግ  ችግሩን ለመፍታት ወሳኝ እንደሆነ ምሁራኑ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።   ይበል ካሳ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy