Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዋጋ ጭማሪ ለምን ይከሰታል?

0 1,131

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግሥት ከጥር ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው የደመወዝ ማስተካከያ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው ዝቅተኛ ደመወዝ 582 ብር የነበረውን መነሻ ደመወዝ ወደ 860 ብር ከፍ በማድረግ መድረሻ ጣሪያ አንድ ሺ 439 ብር ያደረሰ ነው። በማስተካከያው ከፍተኛ ደመወዝ ፕሣ – 9 ላይ አምስት ሺ 781 ብር የነበረውን፣ ወደ ሰባት ሺ 647 በማሳደግ እና ጣሪያው 10 ሺ 946 በማድረግ ስኬሉ እንዲሻሻል አድርጓል።

የአገሪቱ ዋጋ ግሽበት ደግሞ ባለፈው ጥር ወር ከነበረበት 6 ነጥብ 1 በመቶ በየካቲት ወር ወደ 7 በመቶ ከፍ ማለቱን ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በመሆኑም የደመወዝ ስኬል ማስተካከያው ጥናት ላይ ተመርኩዞ የተደረገ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስ ባለሙያዎች ማህበር አባል የሆኑት የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ሰኢድ ኑሩ እንደሚሉት፣ ደመወዝ በሚስተካከልበት ወቅት ጥናት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። በተለይ ጥናቱ ሠራተኛው ለሚሰራው ሥራ ወይም ለሚያከናውነው ነገር የተሻለ ደመወዝ እንዲያገኝ በማድረግ ማትጋት ላይ እና ሥራውን በአግባቡ የሚሰራ ሠራተኛ ከማይሰራው ጋር ማበላለጫ የሚሆንበት መንገድ ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡

የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ጥናት ሲደረግ በመጀመሪያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የደመወዝ ማስተካከያውን መሸከም ይችላል ወይ? በመቀጠል የመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦቱ በቂ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት ያነሳሉ። እነዚህ ካልታዩ የዋጋ ንረት እንደሚከሰት ያብራራሉ፡፡

የደመወዝ ማስተካከያ በሚደረግበት ወቅት የህብረተሰቡ ፍላጎት አብሮ የሚጨምር በመሆኑ ነጋዴው የሸቀጥ ዋጋ ይጨምራል የሚሉት ዶክተር ሰኢድ፣ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ የተፈለገውን ያህል ደመወዝ ቢስተካከል አቅርቦቱ ከነበረበት መጠን መጨመር ካልቻለ የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር እንደማይቻል ይጠቁማሉ።

በቅርቡ ለመንግሥት ሠራተኛው የተደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ጥናት ላይ፤ ዘንድሮ ምን ያህል አቅርቦት አለ? ተጠቃሚውን የሚያረካ ነው ወይ? የሚሉ ጉዳዮች ካልታዩ የዋጋ ንረቱ የተጋነነ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡ የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረ ግን ገበያው የተረጋጋ እንደማይሆንና ለዚህም በድጋሚ የደመወዝ አከፋፈሉ ሥርዓት መጠናት እንዳለበት ያመለክታሉ።

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ አቶ ኑረዲን ጁሀር፣ የዋጋ ንረት የሚመጣው ደመወዝ ሲስተካከል ብቻ ሳይሆን የሰው የመግዛት አቅም እየጨመረ ሲመጣ የሚከሰት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአገሪቱ ደመወዝ ተስተካከለ ተብሎ የሸቀጦች ዋጋ በእጥፍ መጨመር እየተለመደ መምጣቱን ይገልፃሉ።

ደመወዝ ማስተካከያውን ተከትሎ የተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ የገበያ ፍላጎት ስለጨመረ ነው? ወይስ ነጋዴው እራሱ የፈጠረው ነው? የሚለው መመለስ እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሸቀጥ አቅርቦቱ ምን ያክል እንደሆነ መታወቅ እንዳለበት ያነሳሉ፡፡ የዋጋ ጭማሪው በነጋዴው ከሆነ የተፈጠረውን ጭማሪ የመቆጣጠር ሥራ መሰራት እንዳለበትና በገበያው ያለው የአቅርቦትና የፍላጎት መጠን በጥናት መስተካከል እንዳለበት ያስረዳሉ።

አቶ መስፍን ከተማ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ሲሆኑ፣ የደመወዝ ማስተካከያ ጥናት ሲደረግ ማስተካከያው የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ያማከለ መሆኑን፣ የመንግሥት በጀት አቅምና የሸቀጥ አቅርቦቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መታየት እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡

በሌላ በኩልም የደመወዝ ማስተካከያ ሲደረግ የገበያው ሁኔታ ከግምት ሳይገባ ህብረተሰቡን ለዋጋ ንረት የሚያጋልጥ ከሆነ አላማውን እንዲስት ሊያደርገው እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ ማስተካከያው የዋጋ ግሽበቱን፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱን፣ የመንግስት የመክፈል አቅምን፣ አቅርቦትና ፍላጎቱን ምርታማነትን እነዚህን ነገሮች ያገናዘበ ከሆነ ግቡን ሊመታ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ የተደረገው ደመወዝን ከገበያ ጋር ለማቀራረብ የመንግሥት የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን መንግሥት ገልጿል። በየጊዜው የደመወዝ ማስተካከያ በሚያደርግበት ወቅት ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት የሚሯሯጡ ሆነ ዋጋ የሚጨምሩ አካላት አሉ፡፡ ስለሆነም ምክንያታዊ ያልሆነው የዋጋ ጭማሪ የንግድ ሥርዓቱን በማበላሸት የግብይት ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ ስለሚፈጥር የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝና ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መጋቢት 7ቀን 2009 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል፡፡ መርድ ክፍሉ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy