Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዘገየው የሕዝብን ተሳትፎ የመቀበል ፋይዳ

0 381

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአንድ አገር የዴሞክራሲ ሥርዓቶች ስለመዳበራቸው፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስለመፈታታቸውና ጠንካራ የሆነ ለውጥ ስለመመዝገቡ ከሚመዘንባቸው መሥፈርቶች ውስጥ አንዱ የሕዝብ ተሳትፎ ያለበት ደረጃ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበለፀጉ አገሮች ከሚታወቁባቸው ባህሪያት አንዱና መሠረታዊ ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰደው፣ ውጤታማ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ መኖር እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ በዋናነት የሕዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥባቸው በተቋማት ደረጃ የሚታይ ሲሆን ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት መካከልም የሕዝብ ምክር ቤቶች፣ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራትና ሚዲያ ይገኙበታል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 43(2) ላይ የዜጎችን በተናጠልም ሆነ በጋራ ያላቸውን የመሳተፍ መብት ይገልጻል፡፡ ‹‹ዜጎች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን ይበል እንጂ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት የሚያመለክተው ግን በኢትዮጵያ የሕዝብ ተሳትፎ ደካማ መሆኑን ነው፡፡

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ‹‹መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያስጠና የቆየውን የጥናት ውጤት ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳሮማሪያ ሆቴል ይፋ ባደረገበት ጊዜ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ ውስንነት እንዳለበት አረጋግጧል፡፡ ‹‹ሕዝብ ይወክሉኛል፣ የእኔን ችግር፣ ሐሳብና አስተያየት እንደኔ ሆነው ለመንግሥት አካላት ያቀርቡልኛል፣ አስፈጻሚው እኔን ማገልገሉን ይከታተሉልኛል፣ ይቆጣጠሩልኛል የሚላቸው የሕዝብ ምክር ቤቶች የሕዝብ እንደራሴነታቸውን በትክክል ሲወጡ፣ የሕዝብ ተሳትፎን በሚያረጋግጥ ሁኔታ መሥራት ሲችሉና አስፈጻሚውን በሙሉ አቅሙና በሕገ መንግሥቱ መሠረት መቆጣጠር ሲችሉ ሕዝብ በተወካዮቹ በኩል ተሳትፏል ማለት ይቻላል፤›› ሲልም ሪፖርቱ የተሳትፎን መሟላት ቅድመ ሁኔታ ይገልጻል፡፡

የብዙኃንና የሙያ ማኅበራትም በጀርባቸው ያለውን በርካታ አባላቸውን ወክለው የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስና በመልካም አስተዳደር ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ በማሳደግ መንግሥትና ሕዝብን የማገናኘት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት፣ ሚዲያው ትክክለኛ የሆነውን ሚናውን መጫወት ሲችል እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ቁልፍ ሆነው ከወጡ የአመራር ችግሮች ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ አንዱ ሲሆን፣ አሁን በአገሪቷ ውስጥ ያለው የሕዝብ ተሳትፎ ውስንነቶች እንዳሉበት ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በራሱ ከሚያመጣው ችግር በበለጠ ለሌሎች ችግሮች መንስዔ ከመሆን ባሻገር የዴሞክራሲ ባህል እንዳያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍንና ሕዝብ ባለው ሁኔታ እንዳይረካ በማድረግ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር ያደርጋል በማለትም ይገልጻል፡፡

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ አመራሩ ጋ የሚታይ ክፍተት አለ፡፡ ምንም እንኳን በጎና ጅምራቸው የሚያስመሠግኑ ሥራዎችን ብንሠራም እንቅፋት የሆኑ፣ ማነቆ የሆኑና በተፈለገው ደረጃና ጥልቀት እንዳንሄድ፣ የሕዝብ ወሳኝነት ጫና ፈጣሪነት፣ የበላይነት ሚናና ተያያዥ ጉዳዮችን ወደማረጋገጥ ደረጃ አልደረስንም፤›› ብለዋል፡፡

በዋናነት በአስፈጻሚው አካል የሚፈጠሩ እንቅፋቶችን የጠቀሱት አቶ ዓባይ በአደረጃጀቶች፣ በምክር ቤቶችና በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ያሉ እጥረቶችና ውስንነቶች የሕዝብን ተሳትፎ ገትተውት እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡

በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአቅም ግንባታና የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ተፈራ በዬራ በበኩላቸው፣ ‹‹በሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ ከሌለ ዴሞክራሲ ሊጎለብት አይችልም፡፡ ዜጎችም መብቶቻቸውን መጠየቅ አይችሉም፡፡ ሞጋችና ንቁ ማኅበረሰብ መፍጠር ያስቸግራል፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ወሳኝ የሆነ የዴሞክራሲ ማዳበሪያና መገለጫ የሆነ ጉዳይ በኢትዮጵያ ለማጎልበትና ለማዳበር ሲባል ይህ ጥናት እንደተካሄደ ተገልጿል፡፡ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር ሕዝቡ በንቃት፣ በብቃትና በተደራጀ ሁኔታ እንዳይሳተፍ የሚያደርጉ ማነቆዎችና መንስዔዎቻቸውን በመፈተሽ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማመንጨት ታሳቢ ተደርጎ የተሠራው ይህ ጥናት፣ በዋናነት የሕዝብ ምክር ቤቶች አስፈጻሚው አካል ሕዝብን በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ እንዲያሳትፍ ከመከታተልና ከመቆጣጠር አኳያ ያሉባቸውን ችግሮችና መንስዔዎች ለይቶ አስቀምጧል፡፡

የጥናቱ አስፈላጊነትም በአገራችን የሕዝብ ተሳትፎ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ፣ በሒደቱም ያስከተላቸውን ችግሮች ለይቶ በማውጣት የመንግሥት አካላት ሊወስዷቸው የሚገቡ ዕርምጃዎችን ማመላከት፣ መንግሥትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሕዝቡን የነቃና የተደራጀ፣ ሞጋች እንዲሁም ጫና ፈጣሪነትን ተሳትፎ ለመልካም አስተዳደርና ለልማት፣ እንዲሁም ለሰላም ያላቸውን አስተዋጽኦ አስፈላጊነት ልዩ ትኩረት እንዲያደርጉና ሌሎች ተጨማሪ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን በራሳቸው ጭምር እንዲያመነጩ በር መክፈትና ሌሎችም ጥቅሞች እንዳሉት አቶ ተፈራ ገልጸዋል፡፡

ይህ ጥናት ትኩረት ያደረገው በከተሞችና በአራት የገጠር ወረዳዎች ሲሆን፣ አራት ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተካተዋል፡፡ በእነዚህ ክልሎች የሚገኙ ብዙኃን ማኅበራት፣ የሕዝብ ምክር ቤቶችና የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የጥናቱ የትኩረት መስኮች ሆነው ቀርበዋል፡፡

የጥናቱ ተሳታፊዎችን በተመለከተ ከትግራይ ክልል 171 (59 ሴቶችና 112 ወንዶች)፣ ከአማራ ክልል 130 (29 ሴቶችና 101 ወንዶች)፣ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 132 (35 ሴቶችና 97 ወንዶች)፣ ከኦሮሚያ ክልል 89 (23 ሴቶችና 66 ወንዶች)፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር 63 (21 ሴቶችና 42 ወንዶች)፣ ከአዲስ አበባ መስተዳድር 83 (22 ሴቶች 61 ወንዶች)፣ ከፌዴራል ተቋማት 59 (10 ሴቶችና 49 ወንዶች) ሲሆኑ በአጠቃላይ 199 ሴቶችና 528 ወንዶች በድምሩ 727 ሰዎች በጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡

ይህን ጥናት ያቀረቡት ወይዘሮ ውብአምላክ እሸቱ በጥናቱ ጎልተው የወጡና ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ በሰጠው መብት መሠረት አገራዊና አካባቢያዊ በሆኑ በሚመለከቱት ጉዳዮች ላይ በበቂ ሁኔታ እንዳይሳተፍ ማነቆ የሆኑ ዋና ዋና ችግሮች፣ መገለጫዎቻቸውና ለችግሮቹ የሚጠቀሱ ዋና ዋና መንስዔዎች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡

በዚህ ጥናት ግኝት ተደርጎ የተወሰደው የመጀመሪያው ጉዳይ ‹‹የሕዝብን አቅም፣ ሚናና ኃይል በሚገባ አለመረዳት›› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ችግር ሕዝብ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፍ፣ ሐሳብና አስተያየቱን እንዳይሰጥ በማድረግ በሕዝብ ተሳትፎ ሊገኝ ይችል የነበረውን ያህል ውጤት እንዳይመጣ ጋሬጣ የሆነ ችግር እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ በዚህም የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር የሕዝብን አቅም፣ ሚናና ኃይል በሚገባ ካለመረዳት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ቁልፍ ችግር መሆኑን ወይዘሮ ውብአምላክ ገልጸዋል፡፡

ሕዝብን ከማሳተፍ ጋር ተያይዞ የታየው የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር በሦስት አካላት ዘንድ ማለትም በአስፈጻሚው፣ የሕዝብ ተሳትፎ በሚረጋገጥባቸው ተቋማትና በሕዝቡ ዘንድ መታየቱን የሚገልጹት ወይዘሮ ውብአምላክ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ አካላት የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር ጎልቶ የታየው በአስፈጻሚው ላይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከምክር ቤቶች ጋር ተያይዞ በአስፈጻሚዎች የአመለካከትና የግንዛቤ ችግሮች በተለያየ ገጽታ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ምክር ቤቱ እንዲሰበሰብ አለመፈለግ፣ የሕዝብ ተወካዮች የመረጣቸውን ሕዝብ ለማወያየት ሲሄዱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠርና እንደ ሥጋት በማየት ሕዝቡ እንዲሰበሰብ ሁኔታዎችን አለማመቻቸት፣ በተለይ አዲስ አመራር አካላት የምክር ቤቱን ተግባርና ኃላፊነት አሳንሶ ማየት፣ አስፈጻሚው አካላት ዘንድ ምክር ቤቱ ይቆጣጠረኛልና የበላይ ነው የሚል አስተሳሰብ አለመኖር፣ ምክር ቤቱ ከተጠናከረ ይሞግተኛል፣ ጫና ያበዛብኛል ብሎ መፍራትና እንዳይጠናከር መፈለግ፣ ምክር ቤቶች ሥራ የላቸውም የሚል የተሳሳተ አመለካከት መኖር፣ የምክር ቤቱን ሥራ እንደ ደጋፊ ሳይሆን እንደ ስህተት ፈላጊ አድርጎ የማየት የአመለካከት ችግርና ጠንካራ የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ወክለው አስፈጻሚ አካሉን የሚሞግቱ ወይም የሚተቹ የምክር ቤት አመራሮችና አባላት ሲገኙ የሕዝብ ሥልጣን ውክልና እንዳላቸው ያለማመን፣ በምክር ቤቱ የሚሰጡ አስተያየቶችን ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን ለመጉዳትና ለማጋለጥ እንዳደረገው አድርጎ መውሰድና ጠንካራ አቋም ይዞ ሲተች ምክር ቤቱ ‹‹ሊያጠፉን ነው›› የሚል ጩኸት እንደሚበረታ፣ ምክር ቤቱን እንደ አጋዥ ቆጥሮ ተገቢ ሚናውን እንዲጫወቱ ባለመደረጉ የተነሳ የሕዝብ ውክልናን በአግባቡ እንዳይወጣና በዚያውም የሕዝብን ተሳትፎ ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረገው በጥናቱ ተገልጿል፡፡

አስፈጻሚው በብዙኃንና በሙያ ማኅበራት ላይ ያለው የአመለካከትና የግንዛቤ ችግርን በተመለከተ አስፈጻሚው ማኅበራት የሕዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አካላት እንደሆኑ አለመቁጠርና ማኅበራቱን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና መመርያዎች ሲወጡ ሥርዓት ባለው ሁኔታ አሳትፈው አስተያየታቸውን አለመሰብሰብ፣ አንዳንዴም መመርያዎች ከወጡ በኋላ እንዲያውቁት እንደማይደረግም ተገልጿል፡፡ ‹‹መንግሥት ሁሌ የራሱን ወገን ጉዳይና ፍላጎት ብቻ ይዞ የሚሠራ ከሆነ አስቸጋሪ ይሆናል፤›› በማለትም የሚያስከትለውን ችግር ጥናቱ አብራርቷል፡፡

አስፈጻሚው በሚዲያው ላይ (በመንግሥት ሚዲያ) ላይ ያለው የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር በተመለከተ ከሚዲያው የሚነሱ ጥያቄዎችን በትክክል ተረድቶ ምላሽ አለመስጠት፣ ሚዲያው የመንግሥት ብቻ አንዳንዴም የኢሕአዴግ ነው ብሎ ማሰብ፣ በሚዲያ የሚዘገበው ጉዳይ ከአስፈጻሚ አካላት ፍላጎት ውጪ ከሆነም ‹‹የእኛ ሚዲያ አይደለም እንዴ?›› ማለትና የሕዝብ ድምፅ ጭምር እንዳልሆነ ማሰብ፣ ስኬታቸው ብቻ እንጂ ድክመታቸው እንዲዘገብ አለመፈለግ፣ ወዘተ የሚሉ ችግሮች በአስፈጻሚው ላይ እንደተስተዋሉ የጥናቱ ግኝት አብራርቷል፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሕዝብ ተሳትፎ የማይተካ ሚና ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ይህን ሚናውን በአግባቡ እንዳይጫወት ከሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አንዱ ተደማጭ አለመሆንና ምላሽ ማጣት እንደሆነ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡ የምክር ቤቶች ተደማጭነት አነስተኛ በመሆኑ አስፈጻሚው የሚሰጠውን አስተያየት ‹‹እንደ ግብዓት እንወስደዋለን›› የሚል መልስ መስጠቱ የተለመደ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ሌላው በዚህ ጥናት ውስጥ ግኝት የሆነው ጉዳይ በተፅዕኖ ሥር መውደቅ ነው፡፡ ከምክር ቤቶች የሥራ ባህሪና ተልዕኮ አኳያ በአስፈጻሚው ተፅዕኖ ሥር መውደቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሥራ መደበላለቅ፣ በሙስና እንዲተሳፉ በር መክፈቱንና ወደ ምክር ቤት የሚመጡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን በቀላሉ ለመፍታት አዳጋች መሆኑን የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡ በተፅዕኖ ሥር መውደቅ በብዙኃንና በሙያ ማኅበራትም አካባቢ የሚታይ ችግር እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ የሚዲያ አመራሮች በአስፈጻሚ ጫና ስለሚደርስባቸው ሚዲያው በራሱ አቋም እንዳይንቀሳቀስ እንዳደረገ፣ ሚዲያውን የሚጎትቱት አካላት በርካታ እንደሆኑ፣ እንደ ሚዲያ ተቋም ያለበት ትልቁ ፈተና ‹‹የማይታየው እጅ›› እንደሆነና ጣልቃ ገብነቱና ተፅዕኖው ፊት ለፊትና በድብቅ እንደሚደረግ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ ጥናት ግኝት ተደርጎ የተወሰደው ሌላው ጉዳይ የነፃነትና የዴሞክራሲ ችግሮችን የሚመለከተው ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎን ከሚገድቡና ከሚገቱ ችግሮች መካከል አንዱ በዜጎች ላይ የሚደርሰው ኢዴሞክራሲያዊ አያያዝ እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ዜጎች በግላቸውም ሆነ በማኅበራት ተደራጅተው ወይም ባላቸው ኃላፊነት በሚመለከታቸው ጉዳይ ሲሳተፉና ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ፣ ከአስፈጻሚው አካል የሚደርስባቸው ዛቻ፣ ማስፈራራት፣ ጥቃት፣ አድሎዓዊነት፣ ወዘተ ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቱ አብራርቷል፡፡ በግልም ሆነ በቡድን በአገራዊና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን በብዙ አካላት ዘንድ የተነሳሽነትና የቁርጠኝነት ማነስ የሕዝብ ተሳትፎን እየተፈታተነ እንደሆነ የጥናቱ ውጤት ያሳያል፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥባቸው ተቋማትን የሚያጋጥመው ሌላው ችግር የማስፈጸም አቅም ክፍተት እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ስለሕዝብ ውክልና ግንዛቤ የሌላቸውና በምክር ቤት አባልነት ለመወዳደር መመዝገባቸውንና መመረጣቸውን የማያውቁ የአቅም ውስንነት ያለባቸው የምክር ቤት አባላት መኖር አንዱ ችግር መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

የአሠራር ችግር የጥናቱ አንዱ ግኝት ነው፡፡ ከአሠራር ጋር የተገናኙ ችግሮች የሕዝብ ተሳትፎን ከማነቅ ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ የክትትል፣ የድጋፍና ቁጥጥር ችግር፣ የሕዝብ ቅሬታና የአቤቱታ ማስተናገጃ ሥርዓት አለመኖር፣ የተጠያቂነት ችግር፣ የሕዝብ ምክር ቤት የአባልነት ሥነ ምግባር ደንብ አለመከበር፣ ተገቢ አጀንዳ የመቅረፅና ትክክለኛ የተሳትፎ መንገዶችን አለመጠቀምና ቀልጣፋና ወጥነት ያለው አሠራር አለመኖር ከአሠራር ጋር ተያይዘው የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

ፍትሐዊ የተጠቃሚነት ችግር ጥናቱ ይፋ ካደረጋቸው ችግሮች አንዱ ነው፡፡ የዜጎችን የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመንግሥት የተሠሩ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አለማከፋፈል፣ የማኅበር አባላትን በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚነታቸውን አለማረጋገጥ፣ ለተደራጁ ወጣቶች የብድር፣ የዋስትና፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎች አገልግሎት ችግር መኖር፣ ለወጣቱ የመኖሪያ ቤትና የመሥሪያ ቦታ ከመስጠት ጋርም ችግሮች መኖራቸው፣ አንዳንዴም በባሰ ሁኔታ አንድ ሰው በሥሩ የሦስት ሰው መታወቂያ ለይስሙላ በመሰብሰብ ከዚያ የሚገኘውን ጥቅም ሙሉ በሙሉ አጠቃሎ መውሰድ ከእኩል ተጠቃሚነት ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮች መሆናቸው በጥናቱ ተብራርቷል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ደካማ መሆን ደግሞ አንዱ የጥናቱ ውጤት ነው፡፡ በምክር ቤቶች በኩል ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተናበው አለመሥራት፣ በአስፈጻሚ አካላትና በአፈ ጉባዔዎች ዘንድ የሥልጣን ግጭት መኖሩ፣ ተግባብቶ በቅንጅት ያለመሥራት፣ በቋሚ ኮሚቴዎች መካከል ያለመስማማትና በቅንጅት ያለመሥራት ችግር፣ ወዘተ የሚሉ በዋናነት ተለይተዋል፡፡

በሕግ አወጣጥ ሒደት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የብዙኃን ማኅበራትና ኅብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ እየተሳተፉ አለመሆኑን፣ በዚህ ረገድ የሕዝብ ምክር ቤቶች ከአስፈጻሚው አካል ጋር በመሆን የሚወጡ ረቂቅ አዋጆች ላይ የሕዝብ ውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ ለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ ጥራት ያለው መረጃ ከማቅረብ ጋር ተያይዞም በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ዘንድ ችግሮች እንዳሉ ጥናቱ ዳስሷል፡፡

እነዚህ ዋና ዋና የጥናቱ ግኝቶች ሆነው ሲቀርቡ በዚህ ጥናት ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

የመጀመሪያ አስተያየት ሰጪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው፣ ‹‹ጥናቱ ጥሩና ወደፊት ለምንሠራቸው ሥራዎች የመፍትሔ አቅጣጫን ይዞ የመጣ ነው፤›› ካሉ በኃላ፣ ‹‹ታች ያለው አመራር የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግር አለበት፡፡ ከላይ ደግሞ እኔ ትክክል ነኝ ብሎ ማሰብ፣ ማሸማቀቅ፣ ችግርን ወደ ውጭ መግፋት ይታበይታል፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት አስፈጻሚው አካል በሥሩ ባሉ ሠራተኞች የሚገመገምበት አሠራር ቢዘረጋ ጥሩ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት የሰጡት አቶ ዓለምነው መኮንን (የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ) ሲሆኑ፣ ‹‹በእነዚህ በተነሱ ችግሮች ዙሪያ በኅብረተሰቡና በእኛ መካከል ልዩነት የለም፡፡ ልዩነት ያለው መልስ አሰጣጣችን ላይ ነው፡፡ መልስ አሰጣጣችን ተደማጭነታችንን እያቀለለና የእምነት መዳከም እያመጣ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)  በበኩላቸው፣ ዜጎች ስለሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች በተመለከተ የጠለቀ ዕውቀት ስለሌላቸው አገሪቱ ሞጋችና መብቱን ደፍሮ መጠየቅ የሚችል ዜጋ እንዳላፈራች ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ አኳያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ሆኑ ሌሎች ተቋማት አንዱ የተጣለብን ኃላፊነት ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን ድንጋጌና መሠረታዊ ነፃነቶች የማስተማር ሥራ በስፋት እየተሠራ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼንን ሥራ በዋናነት ሚዲያዎች መሥራት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ቅሉ ግን ሲሠሩ አይታዩም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ለአብነት ያህልም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተፈጥሮ የነበረውን ችግር መሥሪያ ቤታቸው መርምሮ ሰኔ 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ያቀረበውን ሪፖርት በሚዲያ ማስተላለፍ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ምክር ቤቱ አንድ ቀን ሙሉ ሲወያይበት የነበረውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት የመንግሥት ሚዲያዎች ሁለት ነገሮች ብቻ በዜና መልክ ተናግረው እንዳለፉ፣ በቅሬታ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው፣ ‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ጠንካራ መንግሥት መሆን አለበት፡፡ ጠንካራ በሚሆንበት ጊዜ ያስቀመጥናቸው ሕጎችና አሠራሮች በጥልቅ ይፈጸማሉ፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ዓውደ ጥናት የመጨረሻ ንግግር ያደረጉትና መድረኩን የዘጉት አቶ ዓባይ ፀሐዬ ናቸው፡፡ በመዝጊያ ንግግራቸው፣ ‹‹ጠንከር ብለን መሬት የሚወርድ መፍትሔ ካላመጣን ሁሌ ችግር እየተናገርን መኖር ፋይዳ የለውም፡፡ ዛሬ የተወያየንበት ጉዳይ የሚሰጠው መልዕክት አለ፡፡ በምክር ቤትና በሙያ ማኅበራት አካባቢ መሻሻሎች ያሉ ቢሆንም፣ መሠረታዊ ለውጥ ግን ማምጣት አልቻልንም፡፡ የፓርላሜንታዊ ሥርዓታችንን ሳንቀይር፣ አብላጫ ወንበር የያዘ ገዢ ፓርቲ መኖር እንደ ችግር ሳንቆጥር አሠራርንና  አፈጻጸምን በተለይ አመለካከት ላይ ያሉ ችግሮችን መቀየር የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ዝግ አይደለም፡፡ በዚህች አገር አሠራር ዕለት በዕለት የምንፈጽማቸው ሥርዓቶች አሉ፡፡ አስፈጻሚው ለምክር ቤት የሚያቀርበው ሕግ ካለ፣ ሹመት ካለ፣ ሪፖርት ካለ፣ በጀት ካለ የሚፈጸመው በጥድፊያ ነው፡፡ በሰዓታት ውስጥ እንዲፀድቅ ነው የሚፈልጉት፡፡ በተለይ ሹመትና ሪፖርት፡፡ ሕዝቡም ለውጥ አያመጣም ስለሚል አይመጣም፡፡ አይሳተፍም፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም የሚለው ነገር ስለሌለ (እንዲገባው ግን ጥረት ያደርጋል) ሕግ ሆኖ ይፀድቃል፡፡ አባላቱ የሚከራከሩበት ሥርዓት የለም፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ክፍተት ድርጅታዊ አሠራርም የሚገታው እንደማይመስላቸው የተናገሩት አቶ ዓባይ፣ ይህን ለማድረግ ግን መጀመሪያ መስተካከል ያለበት ኢሕአዴግ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ለአመራሩ ጠንከር ያለ ጥያቄ ከቀረበ፣ በጀቱን አናፀድቅም የሚል አካል ካለ አካኪ ዘራፍ የሚል አመራር ነው ያለን፡፡ ይህ ደግሞ በልመናና በማሳሰቢያ አይስተካከልም፡፡ እጅና እግራችንን ካላሰርን፣ በሕዝቡና በሕግ ካልታሰርን እንዘቅጣለን፡፡ ይህች አገር እንዳትፈርስ፣ ወደ ትርምስ እንዳትገባ ከተፈለገ መንገዱ እሱ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ይህች አገር ትቀጣጠላለች፡፡ ስለዚህ የኢሕአዴግ አመራር ለራሱ ሲል ይስተካከል፣ ሕዝቡም ለራሱ ሲል ይህንን ያስተካክል፡፡ እዚህች አገር ሊፈነዱ የተቃረቡ ችግሮች አሉ፡፡ ጊዜ ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ መደራደር እሳቱ እንዲቀጣጠል መጋበዝ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ሁሉ ችግር በፍጥነትና በጥልቀት ማስተካከል አለብን፡፡ ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ በመሥራት ዛሬ ነገ ሳንል ከችግራችን ልንወጣ ይገባል፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy