Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የይሓ ጥንታዊ ቤተመቅደስና መካነ ቅርሶች ኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ እንዳላት ምስክር ናቸው

0 890

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የይሓ ጥንታዊ ቤተመቅደስና መካነ ቅርሶች ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ እንዳላት ይበልጥ ምስክርነት የሚሰጡ መሆናቸውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በጀርመን የአርኪኦሎጂ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ላለፉት ስምንት ዓመታት ዕድሳት ሲደረግለት የቆየው የይሓ ቤተ መቅደስ (ቤተ ሙክራብ) በመጠናቀቁ ከትናንት ጀምሮ ለቱሪስት አገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

14 ሜትር ከፍታ ያለው ቤተ መቅደስ ስነ ሕንጻው የተለየና ሲሚንቶም ሆነ ሌላ የማያያዣ ግብአት ሳይኖረው ጥርብ ድንጋዮች እርስ በራሳቸው ተሳስረው ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ትናንት በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት፣ የይሓ ቤተመቅደስና መካነ ቅርስ የቅድመ አክሱም ታሪኮችን፣ ሀብት፣ እውቀትና ብዙ ሚስጥር የያዘ ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡አሁን በጀርመን ባለሙያዎች እየተደረገ ያለው የጥናትና ምርምር ሥራ ቅርሱና ታሪኩ ለቀጣዩ ትውልድ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቤመቅደሱና ቅርሱ ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ታሪክ እንዳላት ምስክር መሆኑን ጠቁመው፣ ከጥገና ሥራው ጎን ለጎን እየተካሄደ ያለው የመካነ ቅርስ ጥናትና ምርምር ሥራ ሳይቋረጥ  መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከአሁን በፊት በይሓ ከተማ ግንባታው ቢጀመርም እየተጓተተ ያለው ሙዚየም ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ባለስልጣኑ ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ዮናስ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የይሓ ታሪካዊ ስፍራን በቀን በአማካይ 17 ጎብኚዎች እየተመለከቱት መሆኑን ገልጸው፣ “የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ከተሟሉ የጎብኚዎችን ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል፡፡”በይሓ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ በጥናትና ምርምር የተገኙ ቅርሶች ኢትዮጵያ በጥንት ጊዜ በእርሻ፣ በንግድ፣ በስነ ሕንጻና ቤተ መንግስት  ደርሳበት የነበረውን እድገት የሚያመላክቱ ናቸው” ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይለ ናቸው፡፡

በተ-መቅደሱ የስነ ሕንጻ ጥበብ ቴክኖሎጂ ባደገበት በአሁኑ ዘመን እንኳ ሊሰራ የማይችል መሆኑን  የፖርቹጋል ተመራማሪዎችም ምስክርነት የሰጡበት ታሪከዊ ሥፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳዊት እንዳሉት፣ ግንቡ በዕድሜ ብዛት ምክንያት በላዩ ላይ እጽዋት በቅለው የመሰነጣጠቅ አደጋ ደርሶበት ነበር፡፡የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከጀርመን ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ቅርሱን ከአደጋ ለማትረፍ ላከናወኑት ሥራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምርቃው ላይ የተገኙ የጀርመን አርኪኦሎጂካል ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳሬክተር ፕሮፌሰር ፍሬደሪክ መልስ በበኩላቸው፣ በይሓ የጀመሩት የጥናትና ምርምር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡የቅርስ ዕድሳቱንና የጥናትና ምርምር ሥራው ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን እንደሚያከሂድ ገልጸዋል፡፡

የይሓ ታሪካዊ ቦታ ከአባ ገሪማ ጥንታዊ ገዳምና ከአድዋ ተራራዎች ጋር በአንድ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ የሚመለከተው አካል ጥረት እንዲያደርግ የጠየቁት ደግሞ የአካባቢውን ማህበረሰብ ወክለው ንግግር ያደረጉ አባ ተክለመድህን ሀጎስ ናቸው፡፡” ወደ ታሪካዊ ሥፍራ የሚያስገባ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ የሌለው በመሆኑ ቤተመቅደሱ የታሪካዊነቱን ያህል እየተጎበኘ አይደለም” ብለዋል፡፡

የይሓ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ ዕድሜ በታሪክ ተመራማሪዎችና በመፅሀፈ ገድል መካከል ልዩነት እንዳለው ጠቁመው፣ የታሪክ ተመራማሪዎች በ800 ዓመተ ዓለም መገንባቱን ቢገልጹም በመፅሀፈ ገድል በ3 ሺህ 610 ዓመተ ዓለም  መገንባቱን የሚገልፅ የፅሁፍ ማስረጃ መኖሩንና ይህም ትክክለኛው መሆኑን ተናግረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy