በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት በተለይም የበለጸጉቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደራዊ ሰፈሮች በሌሎች አገሮች ዘንድ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ መካከልም በሌሎች አገራት ግዛት ውስጥ በርካታ የጦር ሰፈርና ማዛዣዎች በመገንባት ልዕለ ሃያሏ አገረ አሜሪካን የሚስተካከላት የለም።
የፔንታጎን መረጃ እNደሚያሳየው፤ አሜሪካ እ.አ.አ እስከ 2015 ስምንት መቶ ወታደራዊ ሰፈሮችን በሌሎች አገሮች ገንብታለች። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ 72 ዓመታት፤ የኮሪያ ጦርነትም ከተቋጨ ከ65 ዓመታት በኋላ አሜሪካ በጀርመን 174፣ በጃፓን 113፣ በደቡብ ኮሪያ ደግሞ 83 የጦር ሰፈር እንዳላት ሲታሰብ አገሮች ለወታደራዊ ሰፈሮች የሚሰጡት ግምትና ቦታ ላቅ ያለ መሆኑን እንረዳለን።
ይህ በሌሎች አገራት ድንበር ውስጥ የራስን የጦር ሰፈር የመገንባት ተግባር ዘመናዊ ጦር ማቋቋም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ተሞክሮ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህንን እውነታ ወደ አህጉራችን በተለይም ወደ ቀጣናው አምጥተን ስንመለከተውም በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ በስፋት መከናወን ጀምሯል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ በቀይ ባህር ላይ ሁለት ወታደራዊ ሰፈር ገንብታለች። በኤርትራ አሰብ እና በሶማሌላንድ በርበራ ወደቦች ላይ። ሳውዲአረቢያም በተመሳሳይ በቀጣናው ላይ ያላት የጦር ሠፈር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በኤርትራ አሰብ እና በጅቡቲ የጦር ሠፈሮችን ገንብታ አካባቢውን ለብሄራዊ ጥቅሟ አውላለች።
በተለይም የሁለቱ አገራት በቀጣናው ወደብ ላይ የጦር ሠፈር የመገንባት እሩጫ ከዓመታት በፊት ይሰጠው የነበረው ትርጉም በሶማሊያ ያሉ የባህር ላይ ወንበዴዎችን ለመቆጣጠር የሚል ነበር። አሁን ደግሞ የመን ምክንያት ሆናለች። በእርግጥ አንዳንድ ተንታኞች ከየመንም ባሻገር በሱኒ እና ሺያዎች በሌላ አገላለጽ በሳውዲአረቢያ መሩ ቡድንና በኢራን መካከል ያለ አካባቢውን የመቆጣጠር ፍላጎትና ፉክክር ነው።
ለኢትዮጵያ ወሳኝ በሆነው የጅቡቲ ወደብ ላይም አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቻይናና ሌሎች አገሮች የጦር ሰፈር የገነቡ ሲሆን፤ ግብፅና ቱርክም እስከአሁን ፈቃድ እንደገኙ ይፋ የሆነ ነገር ባይኖርም «የእንግባ» ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል። ግብፅም ከተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ጋር በጋራ በመሆን በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ ላይ የጦር ሠፈር ለመገንባት ፈቃድ አግኝታለች፡፡
አዲስ ዘመን በዚህ ዙሪያ ያነጋገራቸው ተንታኞችና የአካባቢው ፖለቲካ አዋቂዎች ይህ የአገራቱ የጎረቤቶቻችንን ወደብ እና የባህር ወሽመጥ የመቀራመትና ወታደራዊ ሠፈር የማቋቋም እንቅስቃሴ ስጋትም ቱሩፋትም እንዳለው ተናግረዋል። ስጋቱን ከቱሩፋቱ አንጻር ስንመዝነው የስጋት ትንሽ፣ የአደጋም ቀላል የለምና መንግሥት ጉዳዩን በቅርበት ተመልክቶ አዋጭ የሆነውን መንገድ መከተል ይኖርበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሁለት ወራት በፊት እንደተናገሩት፤ አገራቱ በቀጣናው ወደቦች ዙሪያ እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በበጎ የምትመለከተው ነው። መንግሥት ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው በቂ ጥናት ሳያደርግ ወጪና ቀሪውን ሳይመዝን ነው ተብሎ አይገመትም። አይታሰብምም። ስለሆነም አሁንም መንግሥት አካባቢውን ነቅቶ ሊጠብቅ፤ የአገራቱን እንቅስቃሴም እግር በእግር እየተከታተለ መወሰድ ያለበትን ዕርምጃ ሁሉ ሊወስድ ይገባል። ምክንያቱም ትናንት የነበረው ዛሬ እንደሌለ ሁሉ፤ የዛሬው እውነታ ነገም ሊኖር አይችልም፤ ቀጣናው ምሥራቅ አፍሪካ ነውና።
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር መሆኗ ሲታወስና ገቢና ወጪ ንግዷም ሆነ ሌሎች ገበናዎቿ ሁሉ በጎረቤት አገሮች ወደቦች የሚገቡና የሚወጡ መሆናቸው ከግምት ውስጥ ሲገባ፤ የጎረቤቶቻችን ወደብ የእኛም ወደብ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም። ስለሆነም አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት በወደብ ላይ ብቻ እንዳይወሰን እየተደረገ ያለው ጥረትና ትስስር መቀጠል አለበት።
ጎረቤቶቻችን ወደባቸው ተፈጥሮ የሰጣቸው ትልቁ ሀብታቸው ነው። ሀብታቸው ስለሆነም አልመተውም ይሁን ለምቶላቸው በእጅጉ እየተጠቀሙበት ነው። በንግድ ልውውጡ ሂደት ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪም ወደቦቻቸውን ለጦር ሰፈርነት በማከራየት ላቅ ያለ ገንዘብ እያገኙ ናቸው።
ለአብነት ያህል ብንመለከት እንኳን፤ ጅቡቲ በዓመት ከአሜሪካ 63 ሚለዮን ከቻይና ደግሞ 100 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች። ስለሆነም ጅቡቲ በወደቧም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ብቻ ከኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ ጥቅም ስለማግኘቷና እያገኘች ስለመሆኗ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። አለበለዚያ ዳፋው ቀላል አይሆንም። ለዚህ ነው የጎረቤቶቻችን ወደብ የእኛ ወደብ ነው ብሎ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ማለታችን።
በተለይም በኤርትራ አሰብ የገቡ አገሮች ከወደብ ኪራይ ባሻገር ለኤርትራ መንግሥት ወታደራዊ ድጋፍ የማድረግ ዝንባሌና እንቅስቃሴ እነዳላአቸው ዓለም አቀፍ ዘገባዎች ያሳያሉ። የእኛ መንግሥትም ይሄንን ጉዳይ ቸል እንደማይለው አስታውቆ አስጠንቅቋል። ይሄ ተገቢና ወቅታዊ ምላሽ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክርቤት ያላትን ወንበር ተጠቅማ ጫና መፍጠርና በኤርትራ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ መዕቀብ እንዳይጣስ ማሳሰብና ጠንክራ መሥራትም አለባት። ይገባልም፡፡ addiszemen