NEWS

የፋይናንስ እጥረትና የዲዛይን ችግሮች ቤት ፈላጊዎች በጊዜ እና በጥራት ቤት እንዳያገኙ ምክንያት ሆነዋል ተባለ

By Admin

March 11, 2017

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቤት ፈላጊዎችን በጊዜ እና በጥራት ቤት እንዳያገኙ ማድረጉን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጥናት አመላከተ፡፡ጥናቱ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በ18 ወራት ውስጥ 50 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ቢያቅድም፥ ግንባታውን ብቻውን በማከናወኑ ቁጥራቸው 900 ሺህ የሚደርሱ ቤት ፈላጊዎችን ጥያቄ አሟልቶ መመለስ እንዳልቻለ አሳይቷል።

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤትና ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ የጥናት ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ምክክር አድርጓል።

በምክክሩ ላይ በቀረበው ጥናት በግዥ፣ በኮንትራት ውል እና በግብዓት አቅርቦት ላይ የተቀናጀ መረጃ እና ግልፅነት አለመኖሩ ተመላክቷል፡፡

የተቋማቱ አመራሮች እና ፈጻሚዎችም በስብሰባ አብዛኛውን ጊዜ ማሳለፍ አገልግሎቱ ላይ ችግር የፈጠረ ሌላው ግኝት ነው፡፡

የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት መሬት ተረክቦ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሲገነባ፥ በቂ ገንዘብ ያለመመደብ እና የመሰረተ ልማት አውታሮች አለመሟላት በእቅዱ ዙሪያም ሳይመክር ወደ ሥራ የመግባት ችግርም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡የቤቶች ግንባታ ቅድመ ጥናት አለማድረግ፣ የዲዛይን ችግሮችና የግብዓት እጥረቶችም ሌሎች በጫና ፈጣሪነት የተጠቀሱ ናቸአው፡፡

ለአብነትም በጀሞ ሳይት የብሎክ 220 ህንጻ የመዝመሙ ምክንያት የቅድመ አፈር ጥናት አለመከናወኑ ሲሆን ይህ ደግሞ ነዋሪዎችን ለእንግልት እና ለተጨማሪ ወጪ ዳርጓቸዋል፡፡

ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ህንጻዎች ተገንብተው ወደ ህብረተሰቡ ከተላለፉ በኋላ ክትትል እንደማይደረግባቸው አንስተው፥ የመፀዳጃ ቤት ቱቦዎች መፈንዳት፣ የመሰረተልማት ሥራዎች በተለይም የውሃና የመብራት ችግሮች ይስተዋላሉ ነው ያሉት፡፡

ለፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ ሰራተኞች የፀደቀው ጥቅማጥቅም ባለመተግበሩ ምክንያት፥ በ2008 ዓ.ም ብቻ ከ2 ሺህ 280 ሰራተኞች መካከል 645ቱ ሥራቸውን የለቀቁ ሲሆን ይህም በቤቶች ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ዘጠኝ ተቋራጮችም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ጥፋታቸው ሳይገለፅላቸው መሰናበታቸውም አላግባብ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ምክትል ዋና እንባ ጠባቂዋ ወይዘሮ ሰራዊት ስለሽ ከህግ ክፍተት ጋር በተያየዘ ለተነሱ ችግሮች፥ የወጡ አዋጆችን ማስፈፅሚያ ደንቦችን በማውጣት ሥራዎችን ሙሉ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡የህብረተሰቡን የቤት ፍላጎት ለማሟላትም ሌሎች አማራጮች ቢፈለጉ የሚል ጥቆማን አቅርበዋል ምክትል ዋና እንባ ጠባቂዋ፡፡