CURRENT

የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ምዝገባ በኢንተርኔት ሊደረግ ነው

By Admin

March 31, 2017

በቀጣዩ ዓመት የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ምዝገባ በኢንተርኔት ኦንላይን ሊደረግ ነው።

የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ምዘና ኤጀንሲ አሁን ላይ በአዲስ አበባ በ152 የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ፥ የሙከራ ስራ የጀመረ ሲሆን 146 ትምህርት ቤቶች ላይ ጥሩ ውጤት ታይቷል ብሏል።

ኢትዮጵያ ለ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ተፈታኞች የምዝገባ ወረቀት (ፎርም) ከለንደን የምታስገባ ሲሆን፥ ለአንድ ፎርም አንድ ፓውንድ የሚጠጋ ሂሳብ ታወጣለች።

በኤጀንሲው የፈተናና ምዘና ውጤት ጥንቅር ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ አበራ፥ የኦንላይን ምዝገባው መጀመር ለወረቀት ፎርም ግዥ የሚወጣውን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ማዳን ያስችላል ብለዋል።

አቶ ዮሴፍ የኦንላይን ምዝገባው ከምዝገባ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ስህቶቶችንም ለመቀነስ ያግዛል ነው ያሉት።

ሁሉም የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የኦንላይን ምዝገባውን ለማከናወን የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።