Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልተኖረ ተስፋ…

0 1,730

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዕትብታቸው የተቀበረባትን ሀገር ድንበር ተሻግረው ወደ ባዕድ ሀገር ለሚገቡ ሰዎች የተሰጠ ስያሜ ነው- ስደተኛ፡፡ ስደት ሰዎች በባዕድ ሀገር ለመኖር የሚያደርጉት ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ከምጣኔ ሀብት ጋር በተያያዘ የተደረጉ ጥናቶች ስደት ለተቀባይ ሀገራትም ሆነ ለመነሻ ሀገራት ጠቀሜታ እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡ ስደተኞቹ ያልተማሩ ከሆኑ ግን በተቀባይ ሀገራት ዜጎች ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸው አይቀርም፡፡

ከስደት ጋር የተያያዙ ውጣውረዶች ቢቀረፉና የሰው ልጅ ወደሚፈልገው የዓለማችን ክፍል በነጻነት ተንቀሳቅሶ መስራት ቢችል የዓለማችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ67 ወደ 147 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

የልማታዊ ኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በታዳጊ ሀገራትና በበለጸጉ ሀገራት መካከል ያሉ የሰራተኞች እንቅስቃሴ መሰናክሎችን ማቃለል ውጤታማ የድህነት ቅነሳ መሳሪያ ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡

ከዓለማችን ስደተኞች ሲሶ ያህሉ በ20 ሀገራት ውስጥ ይኖራሉ፡፡  አሜሪካ 19 ከመቶ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ስደተኞች  ኑሮ የመሰረቱባት ቀዳሚ ሀገር ነች፡፡ በጀርመንና ሩስያ ደግሞ በእያንዳንዳቸው 12 ሚሊዮን ስደተኞች ኑሮ መስርተዋል፡፡ ሳውዲ አረቢያ 10 ሚሊዮን፣ እንግሊዝ ዘጠኝ ሚሊዮን እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ስምንት ሚሊዮን ስደተኞች  ሰርተው የሚኖሩባቸው ሀገራት ናቸው፡፡

ህንድ 16 ሚሊዮን ገደማ ዲያስፖራዎች ያሏት ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን ሜክሲኮ በ12 ሚሊዮን ሩስያ ደግሞ በ11 ሚሊዮን ይከተሏታል፡፡

ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለስደት አይነተኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሰራተኛው ሀይል የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ወደ ባዕድ ሀገር ይጎርፋል፡፡ ሁከትና ብጥብጥ አላስቆም አላስቀምጥ ያላቸው ዜጎችም ስደትን ብቸኛ አማራጫቸው ያደርጉታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለኑሮ ምቹ አካባቢ ፍለጋ፣ ጋብቻና መሰል ማህበራዊ ግንኙነቶችም ከሀገር ሀገር ለሚደረግ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በምዕራብ አውሮፓ እየተስፋፋ የመጣውን የእስልምና ኃይማኖት ተከትሎ የስደት ፖለቲካዊ ገጽታ ከሀገራዊ ደህንነትና ሽብርተኝነት ጋር እየተቆራኘ መጥቷል፡፡ ለዚህ ማጣቀሻ ይሆን ዘንድም ጂላንድስ ፖስተን የተሰኘው የዴንማርክ ዕለታዊ ጋዜጣ በወርሃ መስከረም 1998 ዓ.ም “mohameds ansigt” ወይም “የሙሃመድ ገጽታዎች” በሚል ርዕስ ያወጣቸው የነቢዩ ሙሀመድን የፊት ገጽታ የሚያሳዩ 12 የካርቱን ምስሎች በበርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያስነሳውን ቁጣ ይጠቅሳሉ፡፡

የስደትን ፖለቲካዊ አንድምታ የሚያጠኑ ባለሙያዎች ደግሞ  የ1998ቱን የፈረንሳይ አመጽ እንደ ማጣቀሻ ያነሳሉ፡፡ በጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም የሀገሪቱ ፖሊስ ክሌቺ ቦይስ በተሰኘችዋ ግዛት በሚገኝ አንድ የግንባታ ቦታ ተፈጸመ የተባለውን ስርቆት ለመመርመር በቦታው ሲደርስ የአካባቢው ወጣቶች ሰበሰብ ብለው ምርመራውን ለማደናቀፍ ይሞክራሉ፡፡

ይህን ተከትሎ ፖሊስ በአንድ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ውስጥ ከደበቃቸው ሶስት ወጣቶች ውስጥ ሁለቱ መሞታቸው ሲሰማ ስራ ያልነበራቸው ወጣቶች አመጹን አቀጣጠሉት፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስከ ማውጣት ተደርሷል፡፡ ይህ አመጽ ስምንት ሺህ ያህል ተሸከርካሪዎችን ዶግ አመድ አድርጓል፤ ሁለት ሺህ 760 ዜጎችንም ዘብጥያ አውርዷል፡፡

ሲ ኤን ኤን የተባበሩት መንግሥታትን የስደተኞች ኮሚሽን የ2016 ሪፖርት ዋቢ አድርጎ እንዳስነበበው የስደተኞች ቁጥር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከነበረው እጅጉን አሻቅቧል፡፡ ከዓለማችን ህዝብ አንድ ከመቶ ያህሉ ስደተኞች ናቸው፡፡

እ ኤ አ በ2015 ዓ.ም የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ሪፖርት እንደሚያሳየው የስደተኞች ቁጥር 65.3 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም ፕላኔታችን ካሏት 7.5 ቢሊዮን ሰዎች ውስጥ ከ113ቱ አንዱ ስደተኛ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ይህ አሀዝ በጊዜ ሲመነዘር ደግሞ በየደቂቃው 24 ሰዎች ለስደት ይዳረጋሉ፡፡ ከ10 ዓመት በፊት   በየደቂቃው ስድስት ሰዎች ብቻ ለስደት ይዳረጉ እንደነበር ስንገነዘብ አሀዙ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ በአራት እጥፍ ማደጉን ለመረዳት አንቸገርም፡፡

ለአሀዙ በፍጥነት ማደግ እንደ አፍጋኒስታን፣ ሶርያና ደቡብ ሱዳን በመሳሰሉ ሀገራት የተቀሰቀሱት ግጭቶች ምክንያቶች ሆነው ቀርበዋል፡፡ ከግማሽ በላይ (54%) የሚሆነው ስደተኛ ከሶርያ፣ አፍጋኒስታንና ጎረቤት ሶማሊያ መሆኑም በሪፖርቱ ይፋ ሆኗል፡፡

በዚሁ ጊዜ ከቀረቡ የጥገኝነት ማመልከቻዎች /ጥያቄዎች ውስጥ አንድ መቶ ሺህ ያህሉ ቤተሰብ ከሌላቸው ወይም ከቤተ ሰቦቻቸው ከተነጠሉ የአፍጋኒስታን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና የሶርያ ህጻናት የቀረቡ ናቸው፡፡

እኤአ በ2015 ብቻ 200 ሺህ የአፍጋን፣ ሶማሊያና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን 107 ሺህ አንድ መቶ የሚሆኑት ደግሞ በሌሎች ሀገራት እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡

ቱርክ 2.5 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስጠለል የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር ነች፡፡ ፓኪስታን 1.6 ሚሊዮን፣ ሊባኖስ 1.1 ሚሊዮን፣ ኢራን 979 ሺህ እንዲሁም ኢትዮጵያ 736 ሺህ ስደተኞችን በማስጠለል ከሁለተኛ አስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ስደተኞች በባህርም ሆነ በየብስ የሚያደርጉት ጉዞ በአደጋ የተሞላ በመሆኑ ጉዳዩ እጅጉን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡

“አስፈሪ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በየዓመቱ ባህር ላይ ህይወታቸውን ያጣሉ፤ ጦርነትን ሽሽት በየብስ የሚንቀሳቀሱትም ሀገራት ድንበሮቻቸውን በመዝጋታቸው ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል”…ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፡፡

በ2016 ዓ.ም ተግባራዊ የሆነው የአውሮፓውያን ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር የስደተኞችን እንቅስቃሴ አልገታውም፡፡ ይልቁንም የስደተኞችን ጉዞ ውስብስብና በአደጋ የተሞላ አድርጎታል፤ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተዋንያንም ሰፊ በር ከፍቷል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ጣልያንን ከረገጡ 181 ሺህ 436 ስደተኞች ውስጥ 90 ከመቶ ያህሉ ከሊቢያ ተነስተው በጀልባ ሜዲትራንያንን ያቆራረጡ ናቸው፡፡ ከነዚህ ስደተኞች ውስጥ  21 ከመቶው ናይጄሪያውያን፣ 11 ከመቶው ደግሞ ኤርትራውያን መሆናቸውን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የጣሊያንን ምድር ከረገጡ ስደተኞች ውስጥ ከ25 ሺህ የሚልቁት ቤተሰብ አልባ ወይም ከቤተሰቦቻቸው የተነጠሉ ህጻናት መሆናቸው ደግሞ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ሪፖርቱ በግልጽ አስቀምጧል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ወደ ጣሊያን ሲያመሩ ከሞቱ ወይም ደብዛቸው ከጠፋ አምስት ሺህ 96 ስደተኞች ውስጥ 90 ከመቶ ያህሉ የባህር ላይ ተጓዦች ናቸው፡፡ ይህ አሀዝ ወደ ጣሊያን ለመጓዝ ባህር ከሚያቋርጡ 40 ሰዎች ውስጥ አንዱ ህይወቱን እንደሚያጣ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ባሻገር  ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ሌሎች ወንጀለኞች ስደተኞች ላይ የሚፈጽሙት ከጠለፋ፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት፣ ከድብደባና የግዴታ ክፍያ ጋር የተያያዙ ሪፖርቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ዜጎቿ በሀገራቸው ጥረው ግረው እንዲለወጡ የሚያግዙ ርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ አሁንም ቢሆን የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አማራጭ ርምጃዎችን ከመውሰድ ወደ ኋላ አላለችም፡፡ በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ሀብት ንብት አፍርተዋል፤ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወገኖቻቸው የስራ እድሎችን እስከ መፍጠርም ደርሰዋል፡፡

ይህ ማለት ግን የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው በሀገራቸው ሰርተው ህይወታቸውን ለመለወጥ ከመታተር ይልቅ እጅና እግራቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው የውጪውን ዓለም የሚናፍቁ፣  በህገ ወጥ ደላሎች “ላም አለኝ በሰማይ…” ዓይነት ስብከት ለስደት እጃቸውን የሰጡ ዜጎች የሉንም ማለት አይደለም፡፡

በርካታ ወገኖቻችን በህገ ወጥ ደላሎች የተባ ምላስ ተታልለው ያላቸው ጥሪታቸውን አሟጠው፣ የሌላቸው ደግሞ ተበድረው ተለቅተው ለህገ ወጥ ደላሎቹ አስታቅፈው አስፈሪ የስደት ጉዞ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በዚህ አስከፊ ጉዞ ላይ እያሉ ህይወታቸውን ያጡ፣ ለአካላዊና እዕምሯዊ ጉዳት የተዳረጉ፣ ካሰቡት ቦታ ሳይደርሱ የሌሎችን ሀገራት ወህኒዎች የሚያሞቁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠራቸው፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት የሀገሪቱ ዜጎች በተለይም ወጣቱ በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባለፈ የዜጎቹን ክብርና ህይወት ለመጠበቅ ሲባል ወደ ተወሰኑ ሀገራት የሚደረጉ የውጭ አገር ስምሪቶችን ሳይቀር ሰርዞ ከተቀባይ ሀገራት ጋር ድርድሮችንና ስምምነቶች እስከ ማድረግ ደርሷል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት በህገ ወጥ መልኩ ወደ ሌላ ሀገር ለመሸጋገር ሲሉ ተይዘው በተለያዩ ሀገራት እስር ቤቶች የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ከየሀገራቱ መንግሥታት ጋር በመነጋገር ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡም ስልጠናን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እስከ ማድረግ ደርሷል፡፡

ህብረተሰቡን ስለ ስደት አስከፊነት ከማስተማርና ከማስገንዘብ ጎን ለጎን በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚሳተፉ አካላትን ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድም ተዘርግቷል፡፡ ያም ቢሆን በህገ ወጥ መንገድ የሚደረገውን ስደትና በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያንን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አለመቻሉን ፍርድ ቤቶቻችንን ያጨናነቁት መዛግብት ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ለማሳረጊያ ያህል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ውሳኔ ካገኙ መሰል መዛግብት ውስጥ የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

አህመድ አሊ አህመድ ይባላል፡፡ በሌላ ግብረአበሩ አማካኝነት ካሰባሰባቸው አህመድ ሰይድ፣ እንድሪስ ሙፍቲን፣ ፋጡማ እንድሪስና ፋጡማ ሰይድ፣ ከእያዳንዳቸው አምስት ሺህ ብር ተቀብሎ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ሲሆን ከከሚሴ ዞን ባቲ ከተማ ራሱ በሚያሽከረክረው መኪና ጂቡቲ ሊያደርሳቸው ጉዞ ይጀምራል፡፡

ተከሳሽ ካሰበው ቦታ ከመድረሱ በፊት አፋር ክልል ውስጥ እንዳለ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ፖሊስም አስፈላጊውን መረጃ አጠናቅሮ ጉዳዮን ወደ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መራው፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አግባብ ካለው የሀገሪቱ ህግ ጋር አገናዝቦ በተከሳሹ ላይ የ18 ዓመት ጽኑ እስራትና የሰባት ሺህ ብር ቅጣት ወስኖበታል፡፡

አቶ በቀለ ናጋሳ ኡርጌሳ  በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጀልዱ ወረዳ ጨለንቆ ቀበሌ ወደ ሚገኘው የአቶ ገቢሳ ቤት መመላለስ አብዝቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ልጃቸው ደስታ ገቢሳን ለስራ ወደ ውጪ ልላካት የሚል ነበር፡፡ ልጅም ወላጅ አባትም በደላላው በተነገራቸው የማይያዝ የማይጨበጥ ተስፋ ተሞልተው ሃሳቡን ተቀበሉት፡፡ ለዚህም የጠየቀው ሰባት ሺህ ብር ተከፍሎት ልጃቸውን በቦሌ በኩል ወደ ዱባይ ይልካታል፡፡

ደስታ ደላላው የሰጣትን ተስፋ ለራሷ ኖራ ለቤተሰቦቿ መትረፍ ሳትችል ወደ እናት ሀገሯ ተመለሰች፡፡ “ያዛኝ ቅቤ አንጓቹ” ደላላም አይኑን በጨው አጥቦ ድጋሚ የአባቷን ቤት አንኳኳ፡፡ ድጋሚ ወደ ሌላ ሀገር መልሶ ሊልካት አባቷንም እሷንም አግባብቶ ተጨማሪ 10 ሺህ ብር ከተቀበለ በኋላ ደስታን ወደ ሳውዲ አረቢያ ላካት፡፡

ደስታ እዚህም ደላላው የሰጣትን ተስፋ እውን ሆኖ አላገኘችውም፡፡ ድጋሚ ወደ ሀገሯ ባዶ እጇን ተመለሰች፡፡ ይኼኔ በደላላው መጭበርበራቸው የተገለጠላቸው አባት ለህግ አቤት አሉ፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትም ግለሰቡ የኢፌዴሪ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 598/1/ ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ያለምንም ህጋዊ ፈቃድ ኢትዮጵያውያንን የመላክ ወንጀል ክስ፣ መርምሮ የስድስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራትና የአንድ ሺህ ብር ቅጣት ወስኖበታል፡፡

ሀየሎም አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የተባለው ተከሳሽም እንዲሁ ሰይድ አህመድ፣ ኑርየ ሰይድ፣ ሀብቶም ዝግቡ፣ ይማም ጌታሁንና መሀመድ አወል የተባሉ የአማራና የትግራይ ተወላጆችን “ሳውዲ እልካችኋለሁ፤ ስራም አስቀጥራችኋለሁ” በሚል አግባብቶ ከእያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ብር ተቀብሎ ራሱ በሚያሽከረክረው መኪና ወደ ጂቡቲ ጉዞ ይጀምራል፡፡

ከሌሊቱ አስር  ሰዓት ገደማ በአፋር ብሔራዊ ክልል ሚሌ ከተማ እንደ ደረሰ በአካባቢው ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ተይዞ ህግ ፊት ቀረበ፡፡

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረበለትን ያለ ህጋዊ ፈቃድ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ የመላክ ሙከራ ወንጀል፣ አግባብ ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ የስድስት ዓመት ጽኑ እስራትና የአራት ሺህ ብር ቅጣት አስተላልፎበታል፡፡

እነዚህን ለአብነት አነሳሳን እንጂ መሰል የፍርድ ቤት መዛግብት በጣሙን በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ምንም እንኳን ችግሩን ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ቢኖሩም ለሆዳቸው ባደሩ ህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚደረጉ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እምብዛም አለመቀነሱን ያሳያል፡፡

በሌለ ዳቦ የወጣቱን ኃይል ሆድ የሚያስጮሁ፣ በማይያዝ በማይጨበጥ ተስፋ የዜጎችን በሀገራቸው ሰርቶ የመለወጥ ተስፋ ያኮሰመኑ፣ ራሳቸው ያልኖሩትን ተስፋ ለሌሎች እየሰጡ የአምራቹን ሰርቶ የመቀየር ወኔና ሞራል  እየሰለቡ ለአስከፊ ስደት የሚዳርጉ ሕገ ወጦችን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም በቃ ሊላቸውና ሊያስቆማቸው ይገባል፤ ሰላም ይብዛልን፡፡ ከእንግዳ መላኩ /ኢዜአ/

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy