Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያገረሸው የባሕር ላይ ውንብድና

0 423

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዚህ ሳምንት በሶማሊያ ጠረፍ በሚገኙ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የነጋዴ የነዳጅ ታንከር በመጠለፉ በመርከብ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ መሸበርን መቀስቀሱን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ከ2012 ጀምሮ በሶማሊያ ጠረፍ ዳርቻ ከተካሄደው የመጀመሪያው የተሳካ ዋነኛ የንግድ መርከብ ጠለፋ ወዲህ የመርከብ ካምፓኒዎች ለባሕር ላይ ውንብድና (ለሽፍቶች) አደጋ የመጋለጣቸው ጉዳይ ከፍተኛ የውይይት ርእስ ሆኖ ነበር፡፡

ኤምቲ አሪስ13 የተባለችው መርከብ እ አ አ መጋቢት 13 ከጅቡቲ ወደ ሞቋዲሾ እየተጓዘች ነበር፡፡ ቀድሞ በተነገራት ሁኔታ በሶማሊያ ጠረፍ ጠልቃ ከመሄድ ይልቅ በአጭሩ በማቋረጥ በአፍሪካ ቀንድና የየመን ደሴት በሆነችው ሶኮትራ መካከል ተጓዘች፡፡ የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ከባሕር ዳርቻው 17 ኪሎ ሜትር ስኪፍ ተብለው በሚጠሩት ፈጣን ጀልባዎች መሳሪያዎቻቸውን በመርከብዋ ምድብተኞች ላይ በማነጣጠር ደፈጣ ውስጥ አስገቡዋቸው፡፡

መርከቧና ስምንት የሲሪላንካ መርከበኞች በሽፍቶቹ ታገቱ፡፡ ለመልቀቅ ገንዘብ ይሰጠን ድርድር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህ ካልሆነም በአካባቢው የፑንትላንድ ባለስልጣናት ላይ ዝተዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት በሶማሊያ በሚገኙ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የታገቱት መርከበኞች ቁጥር 16 የደረሰ ሲሆን ቀሪዎቹ ስምንቶቹ ደግሞ የኢራን ተወላጆች ናቸው፡፡

ታጣቂ ጠባቂዎች ሳትይዝ ወደ ሶማሊያ ጠረፎች ተጠግታ ለምታልፍ መርከብ ደስታን ይሰጣል ይላል የኔፑቲን የባሕር ላይ ደህንነት ቃልአቀባይ፡፡ ይኸው ድርጅት በአሁኑ ሰአት 70 ለሚሆኑ መርከቦች በትጥቅ ጥበቃ የሚያደርግ ሲሆን በዚሁ ወር ቃል አቀባዩ ይህንን የተናገረው እጅግ ከፍተኛ አደጋ አለበት ተብሎ የተለየውን የምእራብ ሕንድ ውቅያኖስን አካባቢ በሚያልፉበት ወቅት ነበር፡፡

የታጠቁ ቡድኖችን በተለምዶ ቀድሞ በአልግሎት ላይ የነበሩ ወታደሮችን ቀጥሮ ማሰራት በብዙ የመርከብ ካምፓኒዎች በጣም ውድ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ የመርከብ ኢንዱስትሪው ትንተና እንደሚለው ብዙዎቹ መርከቦች በተለይ ከፍተኛ ነጻ ቦርድ ቨርቲካል እርቀታቸው ከባሕሩ ወለል እስከ መርከቡ ጫፍ ድረስ የሆኑት ፍጥነታቸውን በመጨመር ከመማረክ ማምለጥ ይችላሉ፡፡

በቅርብ ዓመታት የአውሮፓ ሕብረትና ሌሎችም ሀገራት ቻይናን ጨምሮ የሶማሊያ የባሕር ወንበዴዎችን ለመከላከል በየመን ጠረፍ አካባቢ ተከታትለው የሚሄዱ መርከቦችን ለመጠበቅ የባሕር ኃይል ቃኚ መድበዋል፡፡ ሆኖም አካባቢው በጣም ሰፊ ስለሆነ መርከቦቻቸው ችግር ላይ ላለ መርከብ የሚደርሱት አንዳንድ ጊዜ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ሽፍቶቹ ከገቡ በኋላ የመታገት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ብዙዎቹ የባሕር ኃይል መርከቦች በጉዳዩ እንዳይገቡ ሕጉ ይከለክላቸዋል፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ የባሕር ወንበዴዎችን ለመግታት ዋነኛው ምክንያት በቦታው ላይ የታጠቁ ጥበቃዎች መኖርና ፍጥነትን የመሰለ ምርጥ ተሞክሮ በመያዝ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ሰኞ እለት የተማረከው መርከብ ዝቅተኛ የሆነ ቁመት የነበረውና አዝጋሚ በሆነ ሁኔታ ይጓዝ የነበረ ነው፡፡ ይህ አዲሱ እገታ በባሕር ላይ ለሚፈጸመው ጥቃት የበለጠ ጥንቃቄ እንዲደረግ የማንቂያ ደወል ነው ወይንስ የአዲስ ዙር ውንብድና ለመጀመሩ ማሳያ ምልክት ነው የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡

በአስጨናቂ ሁኔታ ብዙዎቹን የሶማሊያ ጠረፍ አሳ አስጋሪዎችን ከአስር ዓመታት በፊት ወደ ባሕር ሽፍትነት እንዲሰማሩ ያደረጋቸው ሁኔታ ዛሬም እዛው አለ፡፡ ዛሬ ሶማሊያ በተስፋፋ ድሕነትና ረሀብ ተወጥራ ተይዛለች፡፡ ለወጣቶች ጥቂት የስራ እድል ብቻ ነው ያለው፡፡ በጠረፉ አካባቢ የእስያ አሳ አጥማጆች በሚፈጽሙት ሕገወጥ አሳ ማጥመድ በድርጊታቸው በመቆጣት እጅግ እያደገ የመጣ ሰፊ የአካባቢው ነዋሪ ተቃውሞ አለ፡፡

ኦሽን ቢዮንድ ፕሬሲ የተባለው ድርጅት እንደሚለው አንዳንዶቹ የውጭ መርከቦች በፑንትላንድ ባለስልጣናት የተሰጠ አጠራጣሪና የማይታመን ፈቃድ ያላቸው ናቸው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ከእነሱ የሚያገኘው ምንም ጥቅም የለም፡፡

በሶማሊያ የባሕር ላይ ውንብድና ጣሪያ የነካው በ2010 እኤአ ነው፡፡ በታገቱ መርከቦችና ገንዘብ በተጠየቀባቸው እስረኛ የባሕር ኃይል ብዛት ሲታይ መሆኑ ነው፡፡ ኋላ ላይ የመርከብ ካምፓኒዎች የታጠቁ ጠባቂዎችን በመስመር አሰማርተው ሽፍቶቹን የሚከቡ አስፈላጊ ሲሆንም እንዲመለሱ የማስጠንቀቂያ ተኩስ የሚከፍቱ አደራጅተው ነበር፡፡

ይህ ውጤታማ በሆነ መልኩ የባሕር ወንበዴዎቹን የንግድ ሞዴል ሰብሮት ቆይቷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ወደ መርከቦች የሚቀርቡት በምሽት ወይም ጫት የሚባለውን ናርኮቲክ ቅጠል ከወሰዱ በኋላ ነበር፡፡ ድልድዮች ላይ ተኩስ በመክፈት ካፒቴኑ መርከቡን እንዲያዘገይና እንዲያቆም አስገድደው መሰላል በመጠቀም ይገባሉ፡፡

የባሕር ላይ ሽፍቶቹ መርከቡን ከምድብ ተኞቹና ከጭነቱ ጋር ይይዙና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ይጠይቃሉ፡፡ ከ2010 እኤአ በኋላ ይህንን ከቅጣት ጋር ማድረግ አልቻሉም፡፡ አሁን ግን ብዙ መርከቦች የታጠቁ ጥበቃዎች ሳይይዙ እንደሚሄዱ ዜናው ስለተሰራጨ የሶማሊያ የባሕር ላይ ሽፍቶች ትርፋማ ወደሆነው የቀድሞው ንግዳቸው የባሕር ላይ ውንብድና እየተመለሱ ነው፡፡

ጠላፊዎች ዘይት የጫነ መርከብ በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ላይ አግተው ገንዘብ መጠየቃቸውን የአውሮፓ ሕብረት ጸረ ሽፍታ የባሕር ኃይል አስታውቋል፡፡ የአውሮፓ ሕብረት ኃይል ከመርከብዋ ማስተር ጋር ግንኙነት ያደረገ ሲሆን መርከቡና ምድብተኞቹ በምርኮ የተያዙት ሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ ጠረፍ ላይ አርፈው በነበረበት ወቅት መሆኑን ገልጿል፡፡

ጠመንጃ አንጋቾቹ የጠየቁት የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ዝርዝር አልተናገሩም፡፡ የአወሮፓ ሕብረት በአካባቢው የባሕር ላይ ውንብድናን ለመከላከል እየረዳ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ ይህ የአሁኑ የመጀመሪያው ጠለፋ መሆኑ ነው፡፡

መርከቡ ከጅቡቲ ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ነበር የሚያመራው፡፡ ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ጀልባዎች መከበቡን የጭንቀት ድምጽ ሲያስተላልፍ ነበር፡፡ የሲሪላንካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 8 ዜጎቹ በመርከብዋ ውስጥ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ ጠመንጃ አንጋቾቹ ለአካባቢው ባለስልጣን እንደገለጹት አሳ አጥማጆች መሆናቸውንና መገልገያ መሳሪያዎቻቸው ሕገወጥ በሆኑ አሳ አጥማጅ መርከቦች እንደወደሙባቸው ተናግረዋል፡፡

መርከብዋ በተያዘችበት አካባቢ አሉላ በተባለችው ከተማ የአውራጃው ኮሚሽነር የሆኑት አሊ ሽሬ ሞሀመድ ኡስማን ለቢቢሲ እንደገለጹት ጠመንጃ አንጋቾቹ በእርግጥ አሳ አጥማጆች ናቸው ወይንስ የተደራጁ ሽፍቶች የሚለውን በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አሊ ሽሬ ሞሀመድ ኡስማን መርከብዋን ያገቱት ሰዎች አሳ አጥማጆች መሆናቸውን በአካባቢው በሚካሄደው ሕገወጥ አሳ ማጥመድ እየተሰቃዩ መሆናቸውን የገለጹ መሆኑን ተናግረው ሽፍቶች መሆናቸውን ካረጋገጥኩ በፍጥነት አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ እጠይቃቸዋለሁ ወይንም መርከብዋን እንዴት እንደምናድን እናያለን ብለዋል፡፡

መርከቡ የጫነው ዘይት ሲሆን ንብረትነቱ የአረብ ኢምሬት ነው፡፡ ባንዲራውን በተመለከተ አወዛጋቢ ሪፖርቶች አሉ፡፡ በአካባቢው የጸረ ሽፍታ ዘመቻዎችን የሚያካሂደው የአውሮፓ ሕብረት ባሕር ኃይል ድርጊቱ የሽፍቶች እንቅስቃሴ ነው ለማለት ገና ነው ብሏል፡፡ ለማጣራት ወደ አካባቢው አውሮፕላን መላኩን ገልጿል፡፡

መርከቡ ውስጥ 8 ሰዎች እንዳሉበት እንዲሁም 12 ‚000 ቶን ጭነት እንደያዘ ታውቋል፡፡ በሶማሊያ ጠረፎች ገንዘብ ለመቀበል ሲሉ ሲካሄድ የነበረው የባሕር ላይ ውንብድና በቅርብ ዓመታት ትርጉም ባለው ደረጃ ቀንሶ የነበረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዓለምአቀፍ ወታደራዊ የቅኝት ኃይል በስፍራው በመሰማራቱና ለአሳ አጥማጁ ማሕበረሰብ እገዛ በመደረጉ ምክንያት ነበር፡፡

የባሕር ላይ ሽፍቶቹ የፈጠሩት ቀውስ ጣራ በነካበት 2011 እኤአ 237 ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን አመታዊው ለሽፍቶቹ የወጣው ገንዘብ ሲሰላ 8 ቢሊዮን ደርሶ ነበር፡፡ በአካባቢው ጥቂት አነስተኛ የሆኑ አሳ አጥማጅ ጀልባዎች ተይዘው ነበር፡፡ ሚዲያ ካፕሽን ኮሊን ስለሽፍቶቹ ሪፖርት ሊያደርግ ሄዶ የነበረ ቢሆንም በእነሱው ታግቷል፡፡ በ2015 የሶማሊያ ባለስልጣናት ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ስራ እንዲፈጠር ዋስትናን ካላረጋገጠ በባሕሮች ላይ የሚካሄደውን ሕገወጥ አሳ ማጥመድ ካልተዋጋ የባሕር ላይ ሽፍትነት እንደሚመለስ አስጠንቅቆ ነበር፡፡

ከጂኦፖሊሲቲ አማካሪ ድርጅት የወጣው አዲስ ሪፖርት በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ የሚካሄደው የባሕር ሽፍትነት ዓለምአቀፉን ማሕበረሰብ በዓመት 8.3 ቢለዮን ዶላር እንደሚያስወጣው አስታውቋል፡፡ አጠቃላይ ድምሩ በ2015 13 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እንደነበር አንድ ሽፍታ በዓመት 79 ሺ ዶላር እንደሚያገኝም ገልጿል፡፡

በኢኮኖሚክ ኢንተለጀንስ ስፔሻላይዝ ያደረገው ጂኦፖሊሲቲ በሶማሊያ ጠረፎች በየዓመቱ ከ200 እስከ 400 የሚቆጠሩ ሽፍቶች እንደሚንቀሳቀሱ ገልጿል፡፡ የባሕር ላይ ውንብድና በአፍሪካ በሜዲትሬንያን ባሕርና በፓስፊክ ውቅያኖስ ጠርዝ ትልቅ ችግር እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ ጂኦፖሊሲቲ አስጠንቅ ቋል፡፡

ከባሕር ላይ ውንብድና ሽፍቶቹ አጠቃላይ ያገኙት ገቢ በ2010 75 ሚሊዮን እስከ 238 ሚሊዮን ደርሶ ነበር ይላል ጥናቱ፡፡ ግለሰብ ሽፍታ ደግሞ ከ33‚000 አስከ 79‚000 በዓመት እንደሚያገኝ ጥናቱ ይገልጻል፡፡

ወንድወሰን መኮንን

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy