የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲት ሃገራቸው ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናገሩ፡፡ፕሬዝደንቱ ይህን የተናገሩት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተላከ ደብዳቤን በቤተመንግስታቸው በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡
ፕሬዝደንት ኪር በአዲስ አበባ ጉብኝትና ውይይት ካደረጉ በኋላ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን አብረው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ የትብብር ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን መልዕክት ለፕሬዝደንቱ ያስረከቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ እንዳሉት መልዕክቱ የተፈራረሟቸውን የትብብር ስምምነቶች መተግበርና ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሁለቱ ሃገራት ጎረቤታም ብቻ ሳይሆኑ በህዝብ ለህዝብና መንግስት ለመንግስት ያላቸው ሁለንተናዊ ግንኙነት የተጠናከረ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ይህን ግንኙነት በኢኮኖሚያዊና በንግድ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የሱዳን ትሪቢዩን ዘገባ እንዳመለከተው ሁለቱ ሃገራት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያሳድጉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የበለጠ ተቀራርቦ በጋራ መስራት ላይ ያለውን መልካም እድል ለመጠቀም ትኩረት ይደረጋል ብለዋል ሳልቫኪር፡፡
በቀጠናው ባሉ የጸጥታ ጉዳዮችና በአህጉሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡