Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዱከም በ400 ሚሊዮን ብር የሚገነባ ግዙፍ የመዝናኛ ፓርክ ሊኖራት ነው

0 1,401

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፕሮጀክቱ ባለቤት አሥር ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የመገንባት ዕቅድ አላቸው

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ የተመሠረተው ዲዝኒላንድ ፓርክ፣ በአሁኑ ወቅት አሜሪካን ጨምሮ በሦስት አገሮች ወደ 11 ፓርኮች ይዞታነት ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ ፓሪስ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ቶኪዮ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ ሻንጋሃይ የተቀላቀለቻቸው ትልልቅ ከተሞች የዲዝኒላንድ መዝናኛ ፓርኮች መገኛ ማዕከል በመሆን ይታወቃሉ፡፡ በእነዚህ ፓርኮች ዝነኛ የሆሊውድ ፊልሞችን ጨምሮ ትልልቅ የሙዚቃ ድግሶችን በማስተናገድ ይታወቃሉ፡፡

እንዲህ ያሉ መዝናኛ ፓርኮች ያሏቸውን ዘመናዊ የመዝናኛ ይዘት በማሟላት ተመጣጣኝ ደረጃ ያለው መዝናኛ ፓርክ በኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ እንቅስቃሴ የጀመረው ኩባንያ፣ በዱከም ከተማ በአሥር ሔክታር መሬት ላይ የሚንሰራፋ ፓርክ ለመገንባት መነሳቱን አስታውቋል፡፡ አለታላንድ ቢዝነስ ግሩፕ በተሰኘው ኩባንያ ሥር የሚመራው ወሊማ ሪዞርትስ ኤንድ አሚዩዝመንትስ የተባለው ድርጅት፣ ከሚያስተዳድራቸው አንዱ እንደሚሆን የሚጠበቀው ግዙፉ የመዝናኛ ፓርክ፣ ከ400 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ፋይናንስ እንደሚጠይቅ የአለታላንድ ግሩፕ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አሥራት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአምስት ዓመታት ቀድሞ በዱከም ከተማ ገደራ ሆቴልን በ22 ሚሊዮን ብር በመግዛትና ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ዕድሳት ሲያከናውን መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ሙሉቀን፣ በዚህ ይዞታው ሥር የሚገኘውን ይህንን ሆቴል ጨምሮ ከኋላው በሚገኝ ቦታ ላይ እንደ ዲዝኒላንድ ዓይነት ግዙፍ የመዝናኛ ማዕከል የመገንባት ፍላጎት በመያዝ፣ ኩባንያው ለዱከም ከተማ አስተዳደር የቦታ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እስኪሰጠው እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ለመዝናኛ ማዕከሉ ግንባታ ለልዩ ልዩ የውኃ መዝናኛዎችና ለአረንጓዴ ሥፍራ የሚውለው የሰባት ሔክታር መሬት ጥያቄ ምላሽ ካገኘ፣ ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡  እንደ አቶ ሙሉቀን ማብራሪያ እንዲህ ያለውን ግዙፍ መዝናኛ ማዕከል መገንባት ኢትዮጵያ የምታቀርባቸው የቱሪስት አገልግሎቶች የተሟሉ እንዲሆኑ ከማስቻል አልፈው፣ በምሥራቅ አፍሪካ የቱሪዝም ገበያ ጥሩ ተፎካካሪ እንድትሆን እንደሚያስችላት ጠቅሰዋል፡፡ መዝናኛ ፓርኩ ኮንፈረንስ ቱሪዝምን መሠረት ያደረገ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታን ጨምሮ ለኮንሰርት፣ ለልዩ ልዩ ስብሰባዎች የሚውል እንደ ሚሊኒየም ያለ ትልቅ አዳራሽ መገንባት በፓርኩ ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ሥራዎች መሆናቸውን አቶ ሙሉቀን አብራርተዋል፡፡

መዝናኛ ፓርኩ ከቤት ውስጥ ልዩ ልዩ መጫወቻዎች ባሻገር ከቤት ውጭ የሚካሄዱ አዳዲስ መጫዎቻዎችንም እንደሚያካትት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሮለር ኮስተር፣ ፍላይግ ታወር፣ ስፔስ ሻት፣ ዎነደር ዊል የተባሉ በአየር ላይ የሚቀዝፉ እስከ አራት ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ልዩ ልዩ የጨዋታ መኪኖችን እንደሚያመጣ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውኃ ትርዒቶችን አካቶ የኦሊምፒክ ደረጃ ያለው መዋኛ ገንዳ፣ የካምፕ አገልግሎትና የመሳሰሉትን መዝናኛዎች እንደሚያቀርብም ተብራርቷል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም መስክ መዝናኛን ጨምሮ የሚያንቀሳቀሰው አለታላንድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በቅርቡ ግንባታውን አጠናቆ በሐዋሳ ከተማ ሥራ ለማስጀመር የተሰናዳውን ሆቴል በ230 ሚሊዮን ብር እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡ ሮሪ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ሆቴል፣ ካሉት 100 ክፍሎች ውስጥ 56ቱን ክፍሎች በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ብሔር ብሔረሰቦች በሚወክሉ ሥያሜዎች እንዲጠሩ ማድረጉንም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሆቴሉ ይህንን ጨምሮ ለሕፃናት የቤት ውስጥ መጫወቻ ቦታ በማዘጋጀት ማስተናገድ እንደጀመረም አስታውቋል፡፡

ከአንድ ወር በኋላ ሥራ መጀመሩን የሚያበስረው ይህንን ሆቴል ጨምሮ በአገሪቱ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸው አሥር ተጨማሪ ሆቴሎችን የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው የአለታላንድ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሲላ አስታውቀዋል፡፡

ከሆቴልና መዝናኛው ዘርፍ ባሻገር በማኑፋክቸሪንግ መስክም በተለይ በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታወቀው አለታላንድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በዱከም ከተማ የኮስሞቲክስ ፋብሪካ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

በሐዋሳ ከተማ ሲገባ ትልቁና የመጀመሪያ የሆነውን ብረት ማቅለጫ ፋብሪካን ጨምሮ የፓስታና መኮረኒ ማምረቻ፣ በገላን ከተማ የወረቀት ፋብሪካ እንዲሁም በዱከም የውበት መጠበቂያ ኮስሜቲክሶችን የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የሁሉም ፋብሪካዎች ግንባታ በመገባደድ ላይ ሲሆን፣ የማሽን ተከላ እየተካሄደ እንደሚገኝም አቶ ሀብታሙ አብራርተዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አለታላንድ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ከ13 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ በዓመት 300 ሺሕ ቶን ብረት የማምረት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በክልሉ በዚህ ደረጃ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ሲገነባ የመጀመሪያው እንደሆነና ይህ ፋብሪካ ለግንባታ የሚሆኑ ብረቶችን በደቡብ ክልል ማምረት መቻሉ ከሌሎች አካባቢዎች የሚጓጓዘውን መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የግንባታ ሥራዎችን እንደሚያፋጥን አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ፡፡ ይህ ፋብሪካ ከስምንት እስከ 24 ሚሊ ሜትር መጠን ያላቸውን የአርማታ ብረቶች በማምረት የክልሉን የብረታ ብረት ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለሌሎች ገበያዎችም ሊያቀርብ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ በሐዋሳ ከተማ የሚገነባው ሌላው ፕሮጀክት የፓስታና የዱቄት ፋብሪካ ነው፡፡ በ190 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚገነባው ይህ ፋብሪካ በ2010 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራሉ ከተባሉት ውስጥ ሲመደብ፣ ከውጭ የሚገባውን የፓስታና የማካሮኒ መጠን ለመተካት እንደሚያግዝና ለ200 ሰዎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በገላን ከተማ በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ80 ሚሊዮን ብር ካፒታል ግንባታው ተገባዶ እንደሌሎች ፋብሪካዎች ማሽን እየተገጠመለት የሚገኘው የወረቀት ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ ለማንኛውም ዓይነት የሕትመት አገልግሎት የሚውል ወረቀት የሚያመርት ሲሆን፣ በዓመት ሰባት ሺሕ ቶን ያመርታል ተብሏል፡፡ ለ60 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡

አለታላንድ ግሩፕ እየገነባቸው ከሚገኙት አራተኛው የሆነው ለውበት መጠበቂያ የሚሆኑ ቅባቶች ማምረቻ ፋብሪካ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ለውበት መጠበቂያነት ከሚውሉት ቅባቶች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅ በዚህ መስክ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 80 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በ12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አብዛኛው የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የማሽን ተከላ እየተካሄበደት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ሁሉም የአለታላንድ ግሩፕ ፋብሪካዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራ የሚጀምሩ ከሆነ፣ ከ540 በላይ በተለያየ የሥራ መስክ የሚሰማሩ ሠራተኞች ያስፈልጓቸዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ እንደሚናገሩት፣ ኩባንያው በአባታቸው የቡና ንግድ መነሻነት ቀስ በቀስ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ የበቃ ሲሆን፣ ወደፊት የሚከፈቱትን ፋብሪካዎች ጨምሮ ሰባት ድርጅቶች በሥሩ የሚያስተዳድር ግሩፕ ኩባንያ እየሆነ መጥቷል፡፡ በንግድ፣ በእርሻ ሥራ፣ በፋብሪካ፣ በመዝናኛ እንዲሁም በአስመጪና ላኪነት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶችንም ከወዲሁ በማስተዳደር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንሳቅሰው አለታላንድ ግሩፕ ከ20 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን መቅጠር የሚችሉ ኩባንያዎችን እያስፋፋ እንደሚቀጥል ባለሀብቱ ጠቅሰዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy