NEWS

ዶክተር መረራ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

By Admin

March 10, 2017

ዶክተር መረራ ጎዲና ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።የተከሰሱበት የህግ አንቀጽ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ሊያሰጥ የሚችል በመሆኑ ነው የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገው።ተከሳሹ ዋስትና ህገመንግስታዊ መብት በመሆኑና ያለምንም ተጨባጭ ማሰረጃ ነው የታሰሩት በሚል ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ነበር።ጠቅላይ አቃቤ ህግም የተጠረጠሩበት ወንጀል ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል የመናድ ሙከራ በመሆኑ፣ በዋስትና ቢወጡ መረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በሚል እና ከሀገር ይወጣሉ በሚል ዋስትናው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ግራ ቀኙን መርምሮ ተጠርጣሪው በተከሰሱበት የህግ አንቀፅ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ15 አመት በላይ፣ በእድሜ ልክ አልያም በሞት ሊያስቀጣ የሚችል በመሆኑ ዋስትናው ተቀባይነት የለውም ሲል ብይን ሰጥቷል።ዝርዝር የክስ መቃወሚያ ለመስማትም ለሚያዚያ 16 ቀን 2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።