Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዶክተር መረራ ጉዲና ሁለት ክስ ተመሰረተባቸው

0 685

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ሁከት እንዲከሰትና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ የሁከት ጥሪ አስተላልፈዋል በሚል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ሁለት ክስ ተመሰረተባቸው።ክሱ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነው የቀረበባቸው።ተከሳሹ ዶክተር መረራ “የኦፌኮ አመራርነታቸውን እና የፖለቲካ ድርጅቱን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የፖለቲካዊ፣ የሃይማኖታዊ ወይም የአይዶሎጂ አላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተፅዕኖን በማሳደር የሃገሪቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማናጋትና ለማፈራረስ በማቀድ ተቀሳቅሰዋል” ይላል የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ።የአዲስ አበባ ከተማና የፌንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ተቃውሞን እንደ መነሻ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በ2006 ዓ.ም በፖለቲካ ድርጅታቸው የስራ ከፍፍል በማድረግ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ደጋፊዎቻቸውን ወደ ሁከት እንዲገቡ ማድረጋቸውም በክሱ ተጠቅሷል።“በ2008 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ አካባቢ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን የአምቦ ካራ የመንገድ ግንባታ በመቆራረጥ፣ ካምፕ በማቃጠል፣ በተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ላይ ከ2 ሚሊየን 957 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት እንዲወድም አስደርገዋል” ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።“በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ ከ42 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ንብረቶች ላይ ጉዳት እና ውድመው እንዲደርስ በማስደረግ፤ በደቡብ ምዕራብ ሽዋ ዞን ወሊሶ፣ አመያ፣ ጎሮ፣ ቶሌ፣ ኢሉ፣ ቀርሳ፣ ወንጪ ወረዳዎች ግምታቸው 17 ሚሊየን 352 ሺህ 482 ብር የሚሆኑ በቀበሌ መስተዳደር፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ በኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩ የአበባ ድርጆቶች፣ የአትክልት ማምረቻ እና የተለያዩ ንብረቶች እንዲወድሙ እና ጉዳት እንዲደርስ አስደርገዋል” የሚለውም በክሱ ተጠቅሷል።ተከሳሹ በመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም በኢሬቻ አከባበር ስነ ስርአት ላይ የመንግስት ታጣቂዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ በወሰዱት ግድያ 678 ሰዎች ተገድለዋል በማለት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን) ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሁከት ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ክሱ ያስረዳል።በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ ትግሉን እናስቀጥላለን በማለት ባደረጉት የሁከት ጥሪ ከመስከረም 2009 ዓ.ም በኋላ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት መጥፋት እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረስ እንዲሁም በመንግስት ተቋማት ከ215 ሚሊየን 468 ሺህ ብር በላይ ንብረት ውድመትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ከ1 ቢሊየን 168 ሚሊየን ብር በላይ የንብረት ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።በተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ከሚገኙ ከአንዳንድ የኦነግ ደጋፊዎች ለብጥብጥ ማከናወኛ የተሰበሰበ ገንዘብ በኦፌኮ ፓርቲ የፋይናንስ ሃላፊ በኩል እንዲላክ ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል የሚለውም በአቃቤ ህግ ክስ ተመላክቷል።በሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተላለፍ ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም በቤልጂዬም ብራሰልስ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ግንቦት ሰባት ቡድን መሪ እና ከሁለተኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተው በመወያየታቸው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን በመተላለፍ እና የሽብር ተልዕኮ መስጠትና መደገፍ ወንጀል ተከሰዋል።የሽብርተኛ ቡድን በመደገፍ እና በማነሳሳት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የሽብር ወንጀልም ክስ ቀርቦባቸዋል።ዶክተር መረራ ጉዲና ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን፥ በጠበቃቸው አማካኝነት ክሱ ላይ መቃወሚያ እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።ፍርድ ቤቱም በመቃወሚያው ላይ የአቃቤ ህግ ምላሽን ለመስማት ለየካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።በዚሁ የክስ መዝገብ ስር ያሉት የኢሳት ቴሌቪዥን ተቋምና የጣቢያው ሃላፊ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ባለቤቱ ጃዋር መሃመድ፣ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ተቋም ላይ ክስ ለመመስረት እስከ የካቲት 30 2009 በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዟል።FBC

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy