ግብፅ ከዓባይ ወንዝ የምታገኘው ዓመታዊ የውኃ ድርሻ አንድ ጠብታ እንኳን ቢቀንስ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ከአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመምከር የሚታወሱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ፣ ዳግም በተቀሰቀሰው የግብፃውያን ማዕበል ከመጠለፋቸው ጥቂት አስቀድሞ የመከላከያ ሠራዊቱ አገሪቱን ለማዳን በወሰደው ዕርምጃ ቤተ መንግሥታቸውንና ሥልጣናቸውን ለቀዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ መሪ በኋላም ፊልድ ማርሻል የተባሉት አብዱልፈታህ አልሲሲ ግብፅን ለማረጋጋት ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲን ካስወገዱ በኋላ፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በመመሥረት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን አመቻችተዋል፡፡
በዚህ ተግባራቸው ዕውቅናን ያተረፉት የቀድሞው ጄኔራል ይህንኑ ዕውቅና በመጠቀም ራሳቸውን በዕጩ ፕሬዚዳንትነት አቅርበዋል፡፡ ከጦር ሠራዊቱ በፈቃዳቸው በመልቀቅ የጀመሩት ፕሬዚዳንታዊ መንገድም ድል አቀዳጅቷቸው፣ ዛሬ ሦስተኛ የፕሬዚዳንትነት ዓመታቸው ላይ ይገኛሉ፡፡
የግብፅ ውስጣዊ ፖለቲካን በማረጋጋትና በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የግብፅን የውጭ ፖለቲካ በማስተካከል ለመወደስ በቅተዋል፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የፖለቲካ መካረር በማርገብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔን በማበጀታቸውም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በአፕሪል 2015 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብፅ የውኃ ድርሻ ላይ የፈጠረውን ሥጋት በመተባበር መፍትሔ ለመስጠትም፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኢትዮጵያና ሱዳን ጋር የመርህ መገለጫ ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም ለዘመናት የቆየውን የግብፅ ግትርነት በመቀየር ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላትና ይህንንም ሌሎች ተጋሪ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ መጠቀም እንደምትችል በፊርማቸው በማፅደቅ፣ በግብፅ የመንግሥታት ታሪክ የዓባይ ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ የተለየ የፖለቲካ አቋም የያዘ መሪ ያደርጋቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን መሪዎች በፊርማቸው ባፀደቁት የመርህ መገለጫ ስምምነት መሠረት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ መጠናት አለባቸው የተባሉ ሁለት ጥናቶችን ለማድረግ፣ ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎች ኮንትራት ፈርመው የጥናት ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራ መግባት አለመቻላቸውና ለዚህ ምክንያት የሆነው በሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ይህንን ተከትሎም በእኩል የተጠቃሚነት መርህና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት የፖለቲካዊ አለመግባባቶችን መፍታት የመረጡ ናቸው በሚል የተወሰዱት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፖለቲካ ላይ ጫና በመፍጠር የበላይነትን ለመያዝ እየተጉ ስለመሆናቸው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከወራት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ በማፋፋም የግብፅ መንግሥት አካላት ሚና እንዳለበት የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ መክሰሱና ማስረጃዎች እንዳሉትም መግለጹ ይታወሳል፡፡ ግብፅ የተሰነዘረባትን ክስ በይፋ ያስተባበለች ሲሆን፣ ባፈው ሳምንት ለ28ኛው ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ የተገኙት ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየታቸው ይታወቃል፡፡
‹‹ግብፅ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ምንም ዓይነት ሴራ ውስጥ አትገባም፡፡ የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ ለሚጥሩ ሦስተኛ ወገኖችም በፍፁም የዕርዳታ ትብብር አታደርግም፡፡ ይህ ሁለቱ አገሮች የትብብር ምዕራፉን ከጀመሩበት የመጀመሪያ ዕለት አንስቶ እርግጥ የሆነ የሚያቆራኘን ሀቅ ነው፤›› በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አረጋግጠውላቸዋል፡፡ በተለያዩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነቶች ላይ ስምምነት ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ በኦፊሴላዊ ግንኙነቶች ዲፕሎማሲያዊ እንደሆኑ ቢታወቅም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ፖለቲካ ጋር በተገናኘ ጠንከር ያሉ ንግግሮችን ማሰማትና የፖለቲካ ግፊት በሚፈጥሩ መንገዶች ላይ መጓዝ ጀምረዋል፡፡
ከ15 ቀናት በፊት ሁለተኛው የግብፅ ወጣቶች ጉባዔ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብፅ የውኃ ድርሻ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ ጥያቄ ከወጣቶቹ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በገቡት የመርህ መገለጫ ስምምነት መሠረት በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በማከልም፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ግድብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በጥንቃቄ የሚጠኑ ናቸው፡፡ ግድቡን በተመለከተ የግብፃውያን ሥጋት ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ ለሺሕ ዓመታት ከግብፃውያን ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይህ የሞት ወይም የሕይወት ጉዳይ መሆኑን ማንኛውም በውኃው ፍሰት ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚጥር ወገን ሊያውቀው ይገባል፤›› ሲሉ ያልተለመደ ጠንካራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሥጋት የሆነችውን የደቡብ ሱዳን ቀውስ ለመፍታት የአካባቢው አገሮች ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ፣ የደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሔ ቀማሪ ሆነው እየገፉ ይገኛሉ እየተባለ ነው፡፡
የደቡብ ሱዳን መንገድ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያተረፈው የግጭት ተንታኝ ቡድን ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በቅርቡ የደቡብ ሱዳንን ቀውስ በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፣ ግብፅ በደቡብ ሱዳን በኩል ምን እንደምትሻ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
‹‹ግብፅ ለደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሔ ለመፈለግ የተነሳችበት ምክንያት ማጠንጠኛው፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የኃይል ማመንጫ ግድብ ነው፤›› በማለት በግልጽ አስፍሯል፡፡
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ በንፁህ የአደራዳሪነት መርህ ቀውሱን ለመፍታት ብሎም የድንበር ደኅንነት ለማስጠበቅ እየሠራች እንደምትገኝ ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በአሜሪካ የቀረበውን ምክረ ሐሳብ መደገፏን፣ የፕሬዚዳንት ኪር ተቀናቃኝ የሆኑትን አማፂያንና የቀድሞ ፕሬዚዳንተ ዶ/ር ሪክ ማቻርን አስጠልላለች በማለት ደቡብ ሱዳን ፊቷን ኢትዮጵያ ላይ እንዳዞረች ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በደቡብ ሱዳን እንዲሰማራ በተባበሩበት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተወሰነው የአካባቢውን ሰላም አስከባሪ ኃይል በመደገፍ ሠራዊት ለማዋጣት መጣሯም፣ የሳልቫ ኪር መንግሥትን እንዳሳዘነ የክራይሲስ ግሩፕ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን ላይ ጥቅም ያላቸው ዋናዋ ሱዳንና ኡጋንዳ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የሰላም ጥረትን በማደናቀፍ ክፍተት መፍጠራቸውን ያስረዳል፡፡
የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የኡጋንዳ አማፂያን በደቡብ ሱዳን እንዳይከትሙ፣ እንዲሁም የኡጋንዳ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳይጎዳ የሳልቫ ኪር መንግሥትን ይከላከላል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና መንግሥታቸውም በኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ተፅዕኖ ሥር የወደቁ ስለመሆናቸው ሪፖርቱ ያብራራል፡፡
ይሁን እንጂ ኡጋንዳ ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላትን ተሰሚነትንና ተፅዕኖ፣ በሌላ በኩል የሱዳኑን ፕሬዚዳንት አል በሽር በደቡብ ሱዳን ላይ የያዙትን የፖለቲካ አቋም በመጋፋት፣ ተፅዕኖቸውን ከጥግ ማድረስ አዳጋች እንደሆነባቸው በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡
በዚህ የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ሪፖርት የሚስማሙ የሰላምና የፀጥታ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት የደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሔ ቀማሪ ለመሆን የወጡት ይህንኑ ክፍተት በመጠቀም በኡጋንዳ በኩል በመቅረባቸው ነው፡፡
የደቡብ ሱዳን ግጭት ዳግም ካገረሸ ካለፈው ሐምሌ ወር በኋላ ብቻ ሦስት ጊዜ በርዕሰ ብሔር ደረጃ መገናኘታቸውንና የውይይታቸው ማጠንጠኛም የደቡብ ሱዳን ጉዳይ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
ግብፅ በዚህ መንገድ የደቡብ ሱዳን ጥቅምና ፍላጎት በማስከበር ስም የዓባይ ወንዝ ተጋሪ የሆነችውን ኡጋንዳን ከኢትዮጵያ ነጥላ ወደ ራሷ ማምጣት ትፈልጋለች የሚሉት ባለሙያው፣ ይህ ባይሳካ እንኳን በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጠረውን የፖለቲካ ጫና እንደምትፈልገው ያብራራሉ፡፡
ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው የግል የደኅንነት ተቋም ስትራትፎር፣ ‹‹ግብፅ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማስቆም ምን ልታደርግ ትችላለች?›› በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት የተለያዩ መላምቶችን አስቀምጧል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚለው ግብፅ በተደጋጋሚ እንደምትለው ወታደራዊ ጥቃት ኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም አትችልም፡፡ የዚህ ምክንያት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ርቀትን በዋነኝነት ጠቅሷል፡፡ ግብፅ ከፍተኛ ወታደራዊ አቅም ቢኖራትም እስከ ዛሬ በአየር ላይ ነዳጅ መሙላት አቅም ያልፈጠረች በመሆኑ፣ ይህን ለማሳካት ወታደራዊ የጦር ሠፈር ማግኘት የምትችልበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባታል ይላል፡፡
ይህንን ለማድረግ ግን በአካባቢው ያሉ አገሮች በሙሉ በኢትዮጵያ በኩል የቆሙ በመሆናቸው አስቸጋሪ እንደሚሆን ያብራራል፡፡ በመሆኑም የመጨረሻ ያላት አማራጭ የግድቡ ግንባታን ለማደናቀፍ አሻጥር መፈጸም (Sabotage) መሆኑን ይገልጻል፡፡
ሪፖርቱ ይህንን ይበል እንጂ፣ አሁን የተፈጠረው የደቡብ ሱዳን ቀውስ ለግብፅ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ይመስላል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በግብፅ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸውና ትብብር ላይ መምከራቸው በይፋ ተገልጿል፡፡
የተለያዩ ሚዲያዎችና የደቡብ ሱዳን አማፂያን ግን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅ ጋር ማሴራቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደምትሻ ገልጾ፣ የሰሞኑ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝትም በዚሁ ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ እንደሆነ በመግለጽ አጣጥሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርም በሰሞኑ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተው የተናፈሰው ወሬ ሐሰት ነው በማለት አስተባብለዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በመሠረተ ቢስ ወሬ አይደናቀፍም በማለት፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደኅንነት ተንታኝ ግብፅ በደቡብ ሱዳን በኩል የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የማደናቀፍ ዕርምጃ መውሰድ ትሻለች የሚለውን መላምት አይስማሙበትም፡፡ ‹‹ቢያንስ የሁለቱ አገሮች (ግብፅና ኢትዮጵያ) ግንኙነት ወደዚህ ደረጃ የደረሰ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን ግብፅ በዚህ እንቅስቃሴዋ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና መፍጠር እንደምትችል፣ ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያገኘችውን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት መቀልበስ እንደምትሻ የአሁኑ እንቅስቃሴ ትልቁ ዓላማም ይኼው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በፓርላማ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ አካባቢያዊ ዲፕሎማሲን በሚመለከት የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ራስ ምታት እንደሆነባቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ እጃቸውን እያስገቡ ያሉ አገሮች እንቅስቃሴ በተለያየ ፍላጎት የተቃኘ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከቀናት በፊት በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ፣ ለዚህ ጉዳይ የጎንዮሽ የባለድርሻዎች ውይይት መጥራታቸውን ተናግረው የነበረ ቢሆንም ውይይቱን ማካሄድ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ reporter