Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፓርቲዎቹ በድርድሩ እና ክርክሩ እነማን ይሳተፉ በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያዩ

0 410

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

22ቱ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ በሚደረገው ድርድር እነማን ይሳተፉ በሚለው ጉዳይ ላይ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቤት ስራ የሰጠ ውሳኔ አሳለፉ።ኢህአዴግን ጨምሮ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ውይይት አድርገዋል።በውይይቱ ላይ ብዙሃኑ ፓርቲዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ በህጋዊነት የተመዘገቡት እና በምርጫ ቦርድ እውቅና የተሰጣቸው ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች በድርድሩ እና ክርክሩ ላይ ይሳተፉ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።ኢህአዴግ በበኩሉ ከእነዚህ በተጨማሪ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው የክልል ፓርቲዎች (የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች) እንዲሳተፉ ሃሳብ አቅርቧል።የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ በበኩሉ፥ ድርድሩ በኢህአዴግ እና መድረክ ብቻ እንደሚካሄድ ጠቅሶ መድረክ ዋና ተደራዳሪ ሆኖ እንደሚቀርብ ገልጿል።ከዚህ ባለፈም ፓርቲዎቹ እንደ አቋማቸው በቡድን ሆነው ከኢህአዴግ ጋር መደራደር እንደሚችሉም አንስቷል።ለዚህም በሸንጎ ወይም በጉባኤ የሚካሄድ ድርድር ጊዜ ከማራዘም የበለጠ ውጤት አለማስገኘቱን በምክንያትነት ጠቅሷል።የፓርቲዎቹ ተወካዮችም በቀረቡት ሃሳቦች ላይ አስተያተቸውን የሰጡ ሲሆን፥ በኢህአዴግና መድረክ የቀረቡ ሃሳቦች ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።በተለይም መድረክ ራሱን የሌሎች ወኪል አድርጎ ማቅረቡና፥ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ራሱን ትልቅ አድርጎ ማስቀመጡ ተገቢ አይደለም ነው ያሉት።ሃሳቡም አሁን እየታየ ያለውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል የሚያጠፋ ነው ብለዋል ፓርቲዎቹ።በኢህአዴግ ሃሳብ ላይ ባቀረቡት ተቃውሞም፥ ሃሳቡ የክልል ፓርቲዎች ሆነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላገኙትን ያገለለ በመሆኑ አድሏዊ ነው ሲሉም ነው ሃሳባቸውን የገለጹት።በተጨማሪም 22 ፓርቲዎች ሲጠሩ በፓርላማው ያላቸው መቀመጫ እንደመስፈርት ባለመቆጠሩ ሃሳቡ አግባብ አይደለም ብለዋል።ኢህአዴግም በፓርቲው በኩል የቀረበው ሃሳብ መውጣት እንደሚችል በመጥቀስ፥ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።ለ21ዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል እውቅና እንደሚሰጥ በመግለጽም፥ በድርድሩ እኩል የመሳተፍ መብት አላቸው ብሏል።ፓርቲዎቹ በአንድነት መደራደር ከፈለጉ የራሳቸውን አደረጃጀት ይዘው መምጣትና፥ በቡድን ከፈለጉም በራሳቸው አቋም መደራደር የሚያስችል ቡድን ፈጥረው መምጣት እንደሚችሉም አንስቷል።በተናጠል መደራደር የሚፈልግ ፓርቲ ካለም የጋራ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ፍላጎት ካለው ፓርቲ ጋር ኢህአዴግ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።በዛሬው ውይይት ላይ በድርድሩ ስንት ሰው ይወከል የሚለው ጉዳይ ፓርቲዎቹ የሚመጡበት አደረጃጀት ሳይታወቅ ስለማይወሰን ሃሳብ አልተሰጠበትም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy