NEWS

ፓርቲዎች ለመወያየት ተገናኝተው ሳይስማሙ ተለያዩ

By Admin

March 13, 2017

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ከቀረቡት ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 12ቱ ለብቻቸው ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ከስምምነት ሳይደርሱ ተለያዩ።

ከኢህአዴግ ውጭ በድርድሩ ሂደት ዙሪያ ለመወያየት ቀነ ቀጠሮ ከያዙት 21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መድረክን ጨምሮ ዘጠኙ ፓርቲዎች ባልታወቀ ምክንያት በቀጠሯቸው መሰረት አለመገኘታቸው ነው የተገለጸው።

ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር አስፈላጊና መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመደራደር የሚያስችል ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀት በጋራ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እስካሁን በተደረጉ ውይይቶች በመደራደሪያ ረቂቅ ሰነዱ ዓላማ ላይ ከስምምነት ቢደርሱም በሰነዱ ስያሜ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መስማማት ተስኗቸው ቆይተዋል።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር መደራደር የሚችሉት ፓርቲዎቹ በተናጠል የየራሳቸውን የመደራደሪያ አጀንዳ በማቅረብ፣ 21ዱ ፓርቲዎች በጋራ ተስማምተው የጋራ አጀንዳ በመቅረፅ እንዲሁም “የራሴ ለየት ያለ አጀንዳ አለኝ” የሚል የፖለቲካ ፓርቲ በግል በሚያቀርበው የመደራደሪያ ሃሳብ በሚሉ ሶስት መንገዶች ነው።በመሆኑም 21 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር “በቅንጅት ወይስ በተናጠል” በሚለው ላይ ሁሉም ፓርቲዎች ባሉበት መስማማት ባለመቻላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻቸውን ተወያይተው ስምምነት ላይ ለመድረስ ዛሬ በቀጠሮ ተገናኝተዋል።

የተገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ሳይሟሉ ተስማምቶ ውሳኔ ላይ መድረስ ስለማይችሉ አብዛኞዎቹ በተናጠል ጥቂቶቹ አንድነት ፈጥሮ በመደራደር፤ የመላው ኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦህዴፓ) ደግሞ ከሁለቱም ሳይመርጥ የየራሳቸውን አቋም አቅርበው ሳይስማሙ ተለያየተዋል። ኢህአዴግን ጨምሮ 22ቱ ፓርቲዎች በቀጣይ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም በሚገናኙበት ወቅት ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተነጋግረው መስማማት ከቻሉ አንድነት ፈጥረው መስማማት ካልቻሉ በተናጠል ለመደራደር ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ