Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

102 ተቋማት ከ77 ሚሊየን ብር በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውዝፍ ክፍያ አልፈጸሙም

0 735

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

102 ተቋማት ከ77 ሚሊየን ብር በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውዝፍ ክፍያ ቢኖርባቸውም እስካሁን ክፍያ ሊፈጽሙ አልቻሉም።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለደንበኞች ማቅረብ፣ የአግልግሎት ክፍያን መሰብሰብና ክፍያውን በማይፈጽም ተቋም ላይ አገልግሎት ማቋረጥና በህግ ማስከፈል ይጠቀሳል።

ይሁንና ከዚህ ስልጣኑ መካከል ክፍያን መሰብሰብና ክፍያውን በማይፈጽም ተቋም ላይ በውሉ መሰረት አገልግሎቱን ማቋረጥ የሚለው በተገቢው መልኩ እየተተገበረ አለመሆኑን ከአገልግሎት ተቋሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ክፍያን ያለመፈጸም ችግር በተቋማት ላይ የተስተዋለ ሲሆን፥ በዚህ ሂደት እስከ ሁለት አመት ለሚሆን ጊዜና እስከ 17 ሚሊየን ብር የአገልግሎት ክፍያን ያልከፈሉ ተቋማት ተለይተዋል።

ከፍተኛ ከሆነው 17 ሚሊየን ብርና ከዛ በታች ውዝፍ እዳ ያለባቸው ተቋማት በድምሩ 102 ሲሆኑ፥ ከዚህ ውስጥ 90 ያህሉ የመንግስት ተቋማት ናቸው።

በአማካይ ለስድስት ወራት ያህል ምንም አይነት የአገልግሎት ክፍያ ያልፈጸሙት ተቋማት ውዝፍ እዳቸው ተጠራቅሞ አሁን ላይ 77 ሚሊየን 965 ሺህ 298 ብር ደርሷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሄር ታፈረ፥ ችግሩ በተለይም የስኳርና የብረታ ብረት ድርጅቶችን ጨምሮ በአብዛኛው በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

ተቋሙ በያዝነው አመት ብቻ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ በመበጀት አገልግሎቱን እየሰጠ ሲሆን፥ ከዚህ ጎን ለጎን የሚሰበሰበው የደንበኝነት ክፍያ አሁን ባለው ሁኔታ በአማካይ በአመት እስከ 5 ቢሊየን ብር ይደርሳል።

ያልተሰበሰበው ውዝፍ እዳም ለተቋሙ ለሃይል ግዢም ሆነ ለአገልግሎት ተጨማሪ ግብዓትን መፍጠር የሚያስችል ነበር፤ ይህ ባለመሆኑ ግን የፋይናንስ አስተዳደሩ ላይ የራሱን ተጽእኖ መፍጠሩን አቶ ገብረእግዚአብሄር ይናገራሉ።

እንደ አቶ ገብረእግዚአብሄር ገለጻ፥ ተቋማቱ ከሚሰጡት አገልግሎት አኳያ እርምጃ ከመውሰድ በቅድሚያ በደብዳቤ እና በአካል ከተቋማቱ ጋር ተነጋግረዋል፤ በዚህ ሂደት የመጣ ለውጥ ባይኖርም።

ውዝፉ ከልክ በላይ ነው ያለው የአገልግሎት ተቋሙ የደረሰበትን ችግር ከመግለጽ አልፎ፥ የተቋማቱን ማንነት ሊነግረን አልፈቀደም፤ የተቋማቱን ዝርዝርም በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን ብሏል።

አሁን ላይም ችግሩን ለመቅረፍ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን፥ የየሪጅኑን ክትትልና ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ እርምጃ የተወሰደባቸውንና ሊወሰድባቸው የሚገቡትን ጨምሮ የተሰጡ የማስጠንቀቂያ ብዛቶችንና መሰል መረጃዎችን እያደራጀ ይገኛል።

ከዛ የሚመጣውን ውጤት አሁን ካለው መረጃ ጋር በማደራጀትም ዝርዝር ማብራሪያና ስም ዝርዝር ይፋ ይደረጋልም ነው የተባለው።

ከዛ ጎን ለጎን ግን ተቋማቱ ላይ ውል የማቋረጥና በህግ ክፍያውን የማስፈጸም ስራ እንደሚሰራም አቶ ገብረእግዚአብሄር ገልጸዋል። FBC

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy