Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ጠንካራ ዲፕሎማሲ

0 477

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ጠንካራ ዲፕሎማሲ (ታዬ ከበደ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው ካደረጉት ገለፃ መካከል አገራችን የምትከተለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ መስመር አንዱ ነው። አገራችን የምትከተለውን የዲፕሎማሲ መስመር አስመልክተውም፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና የአገራችንን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር መንግስት ሳይታክት እየሰራ መሆነነ ገልፀዋል። በተለይም መንግስት ዋናውን ትኩረት በጎረቤቶች ላይ አድርጎ መስራቱ ከሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ሀገራችን ያላት ግንኙነት ጠንካራና  በጥሩ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን አስረድተዋል።

በተለይም በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሀገሪቱ ወደ መልሶ ግንባታ እንድትገባና ህዝቡ መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ አዲስ ከተመረጠው መንግሥት ጋር እጅግ ተቀራርቦ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን የከፋ ድርቅ ለመቋቋም ሀገራችን ካላት ውስን ሃብት ወንድም ከሆነው ከዚያች አገር ህዝብ ጋር ተካፍለን እንድንጠቀም በማሰብ ህዝቡን ለመታደግ ኢትዮጵያ እየሰራች ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን ውስጥ እየከፋ የመጣውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በቅርቡ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የታወጀው ‘ብሔራዊ ንግግር’ ሁሉንም አካላት ያካተተ እንዲሆን የማበረታታትና ከሰላምና ፀጥታው ባሻገር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ እንዳይሄድ የማድረግ ስራዎችን ሀገራችን እያከናወነች ነው።

በንግድና ኢንቨስትመንት ለመተሳሰርም ከዚህ ቀደም በሀገራችን በኩል እስከ እስከ ደቡብ ሱዳን ድንበር ድረስ የሰራነው መንገድ ወደ ሁለት የክልል ከተሞቻቸው እንዲራዘም የማድረግ ስራን የኢፌዴሪ መንግስት እንዲያከናውን በጁባ አስተዳድር በተጠየቀው መሰረት፤ አገራችን መንገዱ ሁለቱ አገራት ካላቸው ወዳጅነት ማጠናከሪያ እንዲሆን በማሰብ የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን የወዳጅነት መንገድ በሚል ይሁንታዋን ሰጥታ ስራውን ገቢራዊ እያደረገች ነው። ይህ ብቻም አይደለም። ኢትዮጰያ ከጎረቤቶቿ አልፋ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከሩዋንዳና ከኡጋንዳ፣ ከታንዛንያና ከቡሩንዲ ጋር ያላት ግንኙነትም ጠንካራ ነው።

ይህን በጎ የሆነ የሀገራችንን የሁለትዩሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠልም እየሰራች ነው። ለዚህም አገራችን በምትመራው በኢጋድ በኩል እንዲሁም የአህጉራችን ፓን አፍሪካዊ ድርጅት ከሆነው የአፍሪካ ህብረት ጋር የምታደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ እያጎለበተች ትገኛለች። ከዚህ ባሻገርም በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የናይል ኢንሺየቲቭ ማዕቀፍ እንዲጎለብት አገራችን የጀመረችው ስራ ሂደቱን በማነቃነቅ ዙሪያ ኢትዮጵያ መጫወት የሚገባትን ሚና እንድትወጣ እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከአህጉራችን አልፎ ከመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በጋልፍ ካውንስል አገሮች ጋር የተጀመረውን መልካምና ጠንካራ ግንኙነት ከሀገራችን ዘላቂ ጥቅም አኳያ እየተቃኘ ቀጥሏል። እንዲሁም ከምስራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጋር አገራችን ያላት ስትራቴጅካዊ ግንኙነት በተደጋጋሚ የጉብኝቶች በማጎልበት የልምድ ልውውጥ የተገኘበት ነው። ከዚህ አኳያ ከቻይና፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከሲንጋፖርና ከቬትናም ጋር እየተደረገ ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ይጠቀሳል።

በቅርቡ በምዕራቡ ዓለም የተከሰቱትን የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲሁም የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ውሣኔን ተከትሎ የሀገራችን ስትራቴጅካዊ ግንኙነት ከሀገራቱ ጋር ይበልጥ የሚጠናከርበትን ቅኝት በተከተለ መንገድ ሀገራችን እየተጓዘች ነው። በዚህም ውጤት ማምጣት ተችሏል።

እነዚህ የአገራችን መንግስት በዘላቂ ጥቅምና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጥረት ከምንም የተገኘ አይደለም። ሀገራችን የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ኢንቨስትመንትን መሳቡ አይቀርም።

ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱና በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ፖሊሲው በርካታ ባለሃብቶችን በመሳቡ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህን በመመርኮዝም የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የኢንቨስትመንት አዋጁን በተያ ጊዜያት በመከለስ የበለጠ ተወዳዳሪ፣ ሳቢና ግልጽ በማድረግ አሻሽሎታል። ይህም የውጭ ኢንቨስትመንቱ ሳቢና ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ለማድረግ ያለመ ተግባር ነው፡፡ በዚህም መንግስት ያቀደውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ አይታበይም፡፡    

የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሠላምና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን በመገንዘብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ተወላጆች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህብረሰብ ዘንድ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

እርግጥ የኢትዮጵያን በጎ ጎን ማስተዋወቅ የጥቂት ሙያተኞች ወይም የፖለቲካ ሹመኞች ስራ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የተሳካ አፈጻጸም ሊኖር የሚችለው መላው ህዝብ እንደ ሁኔታው የሀገሩ አምባሳደር ሆኖ ሲሳተፍ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ በመንግስት በኩል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው መንገዶች መንግስት እያከናወነ ያለው ጠንካራን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመደገፍና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

እርግጥ የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሠላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

የፖሊሲውና የስትራቴጂው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ነው። በዚህ ስራም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 25 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሠላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረትም በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ የቀጣናው አዋኪ ከሆነው ከሻዕቢያ በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩትና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያረጋገጡት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዲፕሎማሲ መሰረቱም ይኸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መስመር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡  

                                      

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy