CURRENT

ተስፋ መቁረጥን የቆራረጡ ተስፈኞች

By Admin

March 31, 2017

በርካቶች በአካል ጉዳተኝነታቸው ምክንያት መገለል ይደርስባቸዋል።ባልተገባ አመለካከት ሳቢያም የስራ ዕድልን የተነፈጉና በአትችሉም ሰበብ ማህበራዊ ህይወታቸው የተቃወሰ ጥቂቶች አይደሉም።ከነዚህ አካል ጉዳተኛ ወገኖች መሀል ግን እንደሚችሉ ያሳዩና በስራና በትምህርት ልቀው ማንነታቸውን ያስመሰከሩ ጠንካሮች አያሌ ናቸው።የአዲስ ዘመኗ መልካም ስራ አፈወርቅም ተስፋ ሳይቆርጡ ህይወታቸውን ከቀየሩና ለሌሎች ጭምር አርአያ ከሆኑ ሴት አካል ጉዳተኞች ጋር ቆይታ አድርጋ ማንነታቸውን እንዲህ ታስቃኘናለች።

 በትዳር ተጣምረው ዓመታትን የገፉት ጥንዶች ቤታቸው በልጆች መድመቁ ሲያስደስታቸው ኖሯል። ከወለዷቸው አስራሁለት ልጆች መሀል ለአስራ አንዱ የተለየ ፍቅርና ስስት አላቸው። ልጆቻቸው የትዳራቸው ማገርና የስማቸው መጠሪያ ሆነዋል። በዚህም ሁሌም ይኮሩባቸዋል። ጥንዶቹ በልጆቻቸው መገኘት የጎጇቸው ሲሳይ እንደሞላ ያምናሉ። ነገ አድገውና ተምረው ለፍሬ እንደሚበቁ ሲያስቡ ደስታቸው በእጥፍ ይጨምራል። እናም ለመጣ ለሄደው ሁሉ የእነሱ ልጆች መሆናቸውን ሲናገሩ ልባቸው ኩራትና ክብር ይሞላል።

ጥንዶቹ በትዳራቸው ቆይታ ካፈሯቸው ልጆች መሀል ግን በአስረኛዋ ልጃቸው ተደስተው አያውቁም። በእነሱ እምነት ይህቺ ህጻን ደስታቸውን የምታፈዝ ስማቸውን የምታጎድፍ ሆናለች። እንደሌሎቹ የማይመኩባትና ተስፋ የማይጥሉባት ዕድለ ቢስም ነች። ለዛሬ ጠግባ ማደሯን እንጂ ለነገው ህይወቷ የማያስቡላት ምስኪን ናት። ከመወለዷ ሶስት ወር ጀምሮ እንዳሻት አልታዘዝ ያላት ቀኝ እግሯ በእርምጃዋ ላይ የተወው መለያ የማንንታቸው ሀፍረት ሆኖ ሲያሸማቅቃቸው ኖሯል። በእነሱ ዕምነት ይህ ክፉ አሻራ ለእሷ ብቻ የተሰጠ ክፉ ዕድል ሆኗልና ነገዋ ሊያስጨንቃቸው አይገባም።

ህጻኗ አስቴር ከፍ ብላ መጫወት ስትጀምር ዋጋ እንደሌላት ያሰቡት ወላጆቿ እንደ እህትና ወንድሞቿ ተምራ ከቁምነገር እንድማትደርስ ሲናገሩ በእርግጠኝነት ነበር። እኩዮቿ ደብተር ይዘው ቀለም ቆጥረው ሲመለሱ ይህ ዕድል ለእሷ አልተፈቀደም ነበር። «አትችልም» መባሏን ዕውነት አምና ከቤት እንድትውል ስትገደድም “ለምን?” ሲል የተከራከረ አልነበረም። የልጃቸውን የአካል ጉዳት ወጌሻ ከመውሰድ የዘለለ መፍትሄ ያልሰጡት ወላጆች ከዕድሜዋ ማደግም ጋር ለሚስተዋለው አሉታዊ ለውጥም ከይሁንታ ወጭ መፍትሄ አልነበራቸውም።

በየጊዜው የአስተዳደግ አድልዎ እያየች ያደገችው አስቴር ከፍ እያለች ስትሄድ ይከፋት ጀመር። ከእህትና ወንድሞቿ የሚሰጣት ያነሰ ትኩረት የበታችነቷን ስሜቷን ያጎላው ያዘ። በተለይም እንደነሱ ያለመማሯ ሆደ ባሻነቷን አባሰው። በዚህ መልኩ ዓመታትን የገፋችው ህጻን ድንገት አዲስ አበባ የሚኖሩ ዘመዷ ጋር የመሄድን አጋጣሚ አገኘች። ይህ መሆኑ ለውጥን ሲሻ ለኖረ አዕምሮ ታላቅ እፎይታ ነበር።

አስቴር የትውልድ ሀገሯን አምቦን ትታ አዲስ አበባ ስትገባ ዕድሜዋ 12 ሆኖ ነበር። ዕድሜዋ ቀለምን ለይተው ግማሽ የትምህርት እርቀትን የሚጓዙበት ነው። ለእሷ ደግሞ ገና ፊደላትን የምትቆጥርበት የሀሁ ጅማሬ። ያም ሆኖ ግን ዕውቀትን ተርባ ለቆየችው ታዳጊ ታላቅ የምስራች ነበር። እንደ እኩዮቿ ደብተርና መጽሀፍን ለመያዝ፣ ትምህርት ቤት ውሎ ለመመለስ የተፈቀደላት ውድ ጊዜ ሆኗልና። ኑሮዋ መልካም ሲሆንላትና ዕድሜዋ ሲጠና ከትምህርቷ ጎን ለጎን ያገኘችውን እየሰራች መኖርን ለመደች። ይህን ለማድረግ አቅምና ፍላጎቱን ባታጣም አልፎ አልፎ በስራ አጋጣሚ የምታገኛቸው ሰዎች ያልተገባ አመለካከት ግን እንቅፋት ይሆንባት ጀመር። እሷ አካል ጉዳተኛ ብትሆንም እንደማንኛውም ሰው ሰርቶ ማደር እንደምትችል ታውቃለች። ይህ እምነቷ ስራን ሳትንቅና ሳትመርጥ እንድታከብረው አስችሏታል። ብዙዎች ግን በዚህ መንገድ እንዳትጓዝ ዕድሉን ሊሰጧት አልፈቅዱም። አንዳንዶች ስራውንና ማንነቷን ብቻ አገናዝበው ፊታቸውን አዙረውባታል። ጭራሽ ሊያናግሯትና የምትለውን መስማት ያልወደዱም ጥቂቶች አልነበሩም። አስቴር «አትችልም» በሚል ፊት የተነሳችበትና በር የተዘጋባትን ጊዜ አንድ ሁለት ብላ ቆጥራለች። ከጉዳቷ ይበልጥ የብዙዎች ክፉ ንግግርና ያልተደበቀ ንቀት ውስጧን ሲያደማት ኖሯል። ዛሬ ላይ ሆና ያለፈችባቸውን አስቸጋሪ መንገዶች ስታስብ አይኖችዋ በዕንባ ይሞላሉ።

በብዙ መከራና ክፉ አጋጣሚዎች ስትፈተን የቆየችው አስቴር አገሩን ስትለምድና በርካቶችን ስታውቅ ከዘመድ ቤት መኖሩ ከበዳት። እራሷን መቻል እንዳለባት ወስናም ቤት ተከራይታ ወጣች። ይህ ወቅት ነበር “የህይወት አጋሬ ነው” ካለችው ወጣት ጋር ያስተዋወቃት። ጓደኛዋ አሳቢና ተንከባካቢ የሚባል ነው። ብቸኝነቷን ለመቅረፍና ባዶነቷን ለመሙላት፣ ዕንባዋን ለማበስና ታሪኳን ለመቀየር ወደኋላ ያላለ ቀና ሰው። የትዳር ጅማሬውን የአብሮ መኖርን ምንነትና የጎጆን መልካምነትን ያሳያት የፍቅር መምህሯ ሆነ።

አራት ዓመታትን በፍቅር በዘለቀው ግንኙነት መሀል ወጣቱ የቅርብ ጓደኞቹንም ሆነ ቤተሰቦቹን ሊያስተዋውቃት አልፈቀደም። ይህ የመሆኑ ጉዳይ እሷን ቢያሳስባትም አንድ ቀን ሊያደርገው እንደሚችል አስባና የእሱን ፍቅር ብቻ ተቀብላ አብራው መኖርን ቀጠለች። አንድ ቀን ግን የጓደኛዋን እርቆ መሄድና ዳግም ያለመመለስ እውነት በድንገት ተረዳች። ድምጹን አጥፍቶ ፊቱን የማዞሩ ሚስጥርም የእሷ አካል ጉዳተኝነት ስለመሆኑ ዘግይታ አወቀች። ይህ አጋጣሚ ብዙ ፈተናን ላለፈችው አስቴር የሚገርም ባይሆንም በዚህ መልኩ ፍቅራቸውን ለመቋጨት ዝግጁ ያልነበረው ልቧ ግን ለጊዜውም ቢሆን መጎዳቱ አልቀረም።

ይህን ሁሉ ችግር ካሳለፈችም በኋላ ዛሬም ወጣቷ እራሷን አጠንክራ ለለውጥ ተዘጋጅታለች። ትላንት ሌት ቀን መልፋት የለመዱ ብርቱ እጆቿ ዛሬም በስራ መትጋታቸውን ቀጥለዋል። ከአካል ጉዳት ጋር ተያይዞ ምቹ የሚባሉ ሁኔታዎችና ያልተገቡ አመለካከቶች ዛሬም ድረስ የተቀረፉ ባይሆንም እሷን ከመሰሉ አካልጉዳተኛ ሴቶች ጋር በማህበር መደራጀቷ ሰርቶ የማደር ህልሟን ፈቶላታልና ደስተኛ ሆናለች።

ከዛሬ ሃያ ስምንት ዓመታት በፊት ለአቶ አሰግደውና ለወይዘሮ ሙሉመቤት ኪዳኔ፤ ሰባተኛ ልጅ የሆነችው ህጻን የመወለዷ የምስራች ተሰማ። ለቤተሰቡ የመጨረሻና ተወዳጅ የሆነችው ልጅ የዓይን ማረፊያ ሆናለችና እናቷ አይናለም ሲሉ ስም አወጡላት። አይናለም ዕድሜዋ እየጨመረ ሲሄድ በአካሏ ላይ የሚጠበቀው ለውጥ የመዘግየቱ እውነታ መላውን ቤተሰብ ያሳስብ ያዘ። ከእኩዮቿ ጋር እንዳሻት ያለመጫወቷና ዝምተኝነትን ማብዛቷ እናትን ቢያስጨንቃቸው ሀኪም ዘንድ ቀርበው መፍትሄና መላውን ጠየቁ ።

በወቅቱ ከህክምናው ያገኙት ምላሽ አጥጋቢነቱ ያልታያቸው ሴት ልጃቸውን በቤታቸው አስቀምጠው የሚሆነውን ከመጠበቅ ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። የዛኔ የአይናለምን አይነት ህመም በአካባቢያቸው ልጆች ላይ አይተው አያውቁምና ቆይቶ ይተዋታል በሚል ግምት ጊዜያትን ቆጠሩ። እያደር ግን የአይናለም እድገትና የሚጠበቀው ለውጥ ተስፋ አስቆራጭ ሆነ። ይህን የተረዱት ሙሉእመቤትም ልጃቸውን እያዘሉ ጸበል ሲያመላልሱ ቆዩ።

የአይናለም ዕድሜ ሲጨምር ቄስ ትምህርት ቤት እንድትገባ ተወሰነ። ከጓደኞችዋ ያነሰ የቀለም አቀባበል የነበራት ህጻን ግን ውሎ ከመግባት የዘለለ የለየችው አንድም ፊደል አልነበረም። ይሄኔ እናት በሀሳብ ባዘኑ። “ለምን ይህ ሆነ?” በሚል ጭንቀትም ዕንቅልፋቸውን አጡ። አሁንም በህክምናው ተስፋ አልቆረጡምና ሀኪሞች ዘንድ ቀርበው ምላሽን ናፈቁ። የአሁኑ የምርመራው ውጤት የአይናለም ችግር የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እንደሆነ አረጋገጡ። ይህን ከሰሙ በኋላ የወይዘሮ ሙሉእመቤት ዓይን ከልጃቸው አልነቀል አለ። ለእሷ ያላቸውን ጊዜና ትኩረት ጨምረውም አብረዋት መዋል ጀመሩ።

አይናለም እያደገችና ወጣትነቷ እየጨመረ ሲሄድ የእናትና ልጅ ትስስር ይበልጥ ጨመረ። በመንገዷ ሁሉ ሊገጥማት ከሚችለው ፈተና ለመታደግም እሳቸው ጊዜና ሀላፊነትን ወሰዱ። ውለው የሚገቡበት የመንግስት ስራ ቢኖራቸውም ወጥተው እስኪመለሱ አያምኗትም። እንደ እናት ለአንዲት ሴት ልጅ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማስገንዘብና በማሟላት ከማንም የቀረቡ ሆኑ። ልጃቸው ማለት ለእሳቸው መታወቂያቸው ናት። እሷን አይቶ እሳቸውን ማግኘት ቀላል የሚባል ነውና።

ወይዘሮ ሙሉእመቤት ከማንኛውም ቤተሰብ የበለጠ ፍላጎቷን ጠብቀው ባህርይና ልማዷን አቻችለው የመኖራቸውን ትዕግስት ለአንድም ቀን ተማረውበት አያውቁም። በአይናለም ብዙ አይተዋልና ለማንኛውም ጉዳይ ቢሆን ሁሌም ዝግጁ ናቸው። ወይዘሮዋን ዘወትር አንድ የእናትነት እውነት ያሳስባቸዋል። እሳቸው ከእሷ ቀድመው ቢያልፉ ቀጣዩ ህይወቷና ታላቁ ሀላፊነት ለማን አደራ እንደሚባል።

ወይዘሪት አፄባዩሽ አበበ የልጅነት ዘመኗን ከቤተሰቦቿ ጋር ስታሳልፍ ወደፊት ምን መሆን እንደሚገባት ታወጣና ታወርድ ነበር። ዘወትር አዕምሮዋ ለሚያቀብላት የሩቅ አላማና ግብም ዕቅዷ ስኬት እንደሚኖረው ስታስብ በእርግጠኝነት ነው። ይህን ታላቅ ውጥን ከዳር ለማድረስ ስትንደረደር በቆየችበት የወጣትነት ዘመን ግን ህይወቷ ፈተና ገጠመው። በድንገትም የአይኖችዋን ብርሀን ማጣቷን አወቀች። ይህ መሆኑ ትላንት አይናማ ለነበረችውና ታላቅ ዕቅድን ለሰነቀችው አፄ እጅግ ከባድ የሚባል ነበር።

አፄባዩሽ ግን የትላንቱን ማንነቷን አስባ ስለነገው ጨለማነት ለማሰላሰል ቦታ አልነበራትም። የልጅነቷን ህልምና የረጅም ጊዜ ዕቅዷን ለማሳካት ውስጧን በብርሃን ሞልታ ተነሳች። ተስፋ መቁረጥን አስወግዳ መንገዷን በዕውቀት ጎዳና ላይ አፋጠነች። አፄ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነጽሁፍ ስትቀበል ጉዞዋ በዚህ ብቻ እንደማይገታ እርግጠኛ ሆና ነበር።

ብርታትና አልሸነፍ ባይነት መለያዋ የሆነው ሴት አሁንም ቀጣዩን ዓላማዋን ለማሳካት ዕንቅልፍ አልነበራትም። በድንገት የአይኖችዋን ብርሀን መነጠቋ በፈተና መንገድ ቢያራምዳትም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ግን እጅ አላሰጣትም። እናም ቀጠለች። ዕቅድና ግቧ ትምህርትና ዕውቀት ብቻ ሆነ። ሁለተኛ ዲግሪዋን በማህበራዊ ሳይንስ መስክ ስታጠናቅቅም በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚገባት ከራስዋ ጋር ተነጋግራ ነበር።

አፄ የአካል ጉዳተኝነትን ስሜት ታውቀዋለች። ከሁሉም ደግሞ ከጉዳቱ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ማህበራዊ ተጽዕኖዎች ቀላል ያለመሆናቸውን በራሷና በመሰሎችዋ አረጋግጣለችና ቁስሉ ይበልጥ ይሰማታል። ይህ ተፅዕኖ በሴቶች ላይ ሲሆን ደግሞ ችግሩ ይበልጥ ይሰፋል።

ይህን እውነት የተረዳው የአፄ አዕምሮ አሁንም ማቀዱንና መልካም ማሰቡን አላቆመም። እሷን ጨምሮ ከጊዜ በኋላ ከማየት ወደ አለማየት ያለፉ ወገኖችዋን ስሜት ለመጋራት በተቋቋመው ማዕከል የነበራት ተሳትፎና ድርሻ የላቀ ነበር። ዛሬ አፄ ባዩሽ «አዲስ ህይወት ለአይነስውራን» የሚል ስያሜ የተሰጠውን ተቋም በዳይሬክተርነት ትመራለች። ማዕከሉ በተለያዩ ሙያዎች ያሉ አይነስውራንን ዕውቀትና ማንነትን ያሳየና የእሷንም ስኬታማነት ያስመሰከረ ስለመሆኑ በተግባር ተረጋግጦለታል። ልክ እንደ አፄ ባዩሽ ሁሉ በአስቴር ፣በወይዘሮ ሙሉመቤትና በሌሎችም ብርቱ ማንነት ውስጥ ተስፋ መቁረጥ የለም። ሁሉም አስቸጋሪውን መንገድ በጥንካሬ ታግለው ድል ነስተውታልና።