Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲው መጎልበት ይስሩ!

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲው መጎልበት ይስሩ!     /ታዬ ከበደ/

ባለፉት ስርዓቶች በሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ባለመገንባቱ ምክንያት ሕዝቦች በገዛ ሀገራችው በኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተረገጡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተገፎ የስቃይ ቀንበርን ሲሸከሙ ኖረዋል፡፡ ከጭቆና የአገዛዝ ስርዓቶች ሳይላቀቁ  በመቅረታቸው ሳቢያም፤ ስለ ሰላም፣ ስለ ልማት እና ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ እንዳይሰሙ፣ እንዳያዩና እንዳይናገሩ ተደርገው ለሰቆቃ ተዳርገዋል፡፡

ታዲያ ለዚህ ችግር ምላሽ ለመስጠት ከየብሔሩ የተወጣጡ ውድ የሕዝብ ልጆች ህይወታቸውን፣ አካላቸውንና ንብረታቸውን ቤዛ አድርገዋል። በዚህም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እኩልነት፣ የኃይማኖትና የእምነት ነፃነት እንዲሁም የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ብሎም ሌሎች ወሳኝ የሆኑ የቡድንና የግል መብቶች እንዲረጋገጡ ማድረግ ችለዋል።

እናም ሕዝቦቿ መብታቸውን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩባት፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያልታየበት፣ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ ያልታሰበባት ሀገር፤ ዛሬ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘርግታ ይህን የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ጉዞ ማየቷ ማንኛውንም ዜጋ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም፡፡

እንደሚታወቀው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው ውይይትና ክርክር ነው፡፡ የውይይትና ክርክር ጠቀሜታም ሕዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው ስለሚችሉ ፓርቲዊች እንዲያውቁ፣ በዚህም ወደፊት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሚካሄድ መርጫ ስለ ፓርቲዎቹ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ያላንዳች ተጽዕኖ ምርጫ እንዲያካሂዱ መደላድል ለመፍጠር ነው፡፡ በዴሞክራሲ መሰረትም ተቃዋሚውንም ይሁን ገዥውን ፓርቲ የሚደግፈው ህዝብ ድምፅ እንዲሰማም ለማድረግ ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን ከህዝብ የምርጫ ይሁንታ እንጂ በውይይትና ክርክር በአቋራጭ መንገድ የሚገኝ አይደለም፡፡

የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቢሆኑ በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በውይይትና ክርክር በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ግና እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ገና 26 ዓመታትን እንኳን ያልደፈነ ለጋ በመሆኑ፣ የተቋማዊ ፖርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድና የተፈለገውን ርቀት ያህል እንዲጓዝ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል ብሎ መደምደም የሚቻል አይመስለኝም፡፡

በእኔ እምነት ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ከላይ እንደጠቀስኩት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ፣ ስልጣንን ከመጋራት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ሊኖረውም አይገባም እላለሁ። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ልክ እንዳለፉት ጊዜያት መንግስታዊ ስልጣንን ህገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ በውጭ ኃይሎች ግፊት ለመያዝ ከመሻት ከመነጨ በሚመስል ሁኔታ፣ ዛሬም መንግስት ‘ዴሞክራሲውን ለማስፋት ቆርጨ ተነስቻለሁ’ ሲል ጉዳዩን የመድብለ ፓርቲውን ስርዓት ከማጎልበት አኳያ ከማየት ይልቅ፣ ከስልጣን መጋራት ጋር ሊያያይዙት ይሞክራሉ።  

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ ብቻ አይደለም—ህገ መንግስቱን ካለመገንዘብ ጭምር የመጣ እንጂ። የኢፌዴሪ ህገ መንግስቱ አንቀፅ 8፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ-መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ደንግጓል። ይህ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያሳየው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። ህዝቡ ሲፈልግ ይሾማል፤ ሳይፈልግ ደግሞ ይሽራል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል። ተቃዋሚዎቹ ግን ይህን የተዘጋ ዶሴ ከ25 ዓመት በኋላ አዋራውን አራግፈው ሊጠቀሙበት የፈለጉ ይመስላል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምህዳር ግን ይህን ዶሴ የሚያስተናግድበት ቦታ ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ምናልባትም ገዥው ፓርቲና መንግስት ‘ከስልጣናችን ቆርሰን እንስጥ’ ቢሉ እንኳን ስርዓቱ ይህን እንዲያደርጉ የሚፈቅድላቸው ስላልሆነ ነው።

እንደሚታወቀው በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ አንድ በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባር የህዝብን ውክልና መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። ህዝቡ የሚፈልገውን ለማስፈፀም እንጂ እርሱ የሚፈልገውን ነገር በህዝቡ ላይ ለመጫን አይደለም። ምናልባትም የራሱን ፍላጎት በህዝቡ ላይ ለመጫን ካሰበ፣ ህዝቡ በፓርላማ አማካኝነት የሰጠውን የመተማመኛ ድምፅ ሊነጥቀው ይችላል። እናም ከዴሞክራሲ አኳያ የገዥ ፓርቲ ማናቸውም እንቅስቃሴ ከውክልና ጋር የተያያዘ ብቻ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ህዝብ ከሰጠው ውክልና ውጭ ሆኖ ስልጣንን ለሌላ ፓርቲ ሊያጋራ አይችልም። መብትም የለውም። ህዝቡ በ2007 ምርጫ ወቅት የሰጠውን ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ውክልና ችግር ስለገጠመው ብቻ ሸርፎ ለሌላ ፓርቲ የሚሰጥበት ምንም ዓይነት ህጋዊ አመክንዩ ሊኖር አይችልም። አዎ! ህዝቡ በህገ መንግስቱ መሰረት በአምስት ዓመት አንዴ በተደረገው ምርጫ ‘የሚያስራና ለሀገራችን የሚስማማ ፖሊሲና ስትራቴጂ አለህ፣ ከድህነት ልታወጣኝ የምትችለው ስለሆንክ ስልጣኔን በውክልና ሰጥቼሃለው’ ብሎ በእምነት የሰጠውን ስልጣን፣ ከመሬት ተነስቶ ተቃዋሚዎችን ስልጣን የሚያጋራበት መብትና ምክንያት የለውም።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል።

ተቃዋሚዎችም ይህን ተስፋ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳይከታቸው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል። በተለይም ውይይትና ክርክርን ገና ከጅመሩ በመሸሽ የሚገኝ ምንም ዓይነት የዴሞክራሲ ትርፍ እንደሌለ መገንዘብ ይገባል። በይሆናል መንፈስ እየተመሩ ውይይትና ክርክርን ከመሸሽ ይልቅ፤ ያሉ ችግሮችን በመነጋገር መፍታት ይገባል። አሊያ ግን ለዚህች ሀገር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበትና ለዴሞክራሲው መስፋት ተፈላጊውን መፍትሔ ማምጣት የሚቻል አይመስለኝም።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy