Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አንኳር ጉዳዩች

0 1,111

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አንኳር ጉዳዩች  /ታዬ ከበደ

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት “አመለካከትንና ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብትን” በደነገገበት አንቀፅ 29 ላይ አንኳር ጉዳዩችን ይዟል። እነርሱም ማንኛውም ሰው የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ እንደሚችል፣ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዳለው፣ የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የስነ ጥበብ የፈጠራ ነፃነት መረጋገጡን ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት የሚገልፁ መብቶች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ እንደሚደረግ እንዲሁም በዚህ አንቀፅ ስር የተጠቀሱት መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ህጎች ብቻ መሆኑንና ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ የህግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል የሚሉት ገዳዩች በህገ መንግስቱ ህጋዊ ከለላ የተሰጣቸውና እየተተገበሩ ያሉ መብቶች ናቸው።

ከእነዚህ አንኳር ሃሳብን የመያዝና በነፃነት የመግለፅ መብቶች መረዳት የሚቻለው ቁም ነገር፤ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ መብቶች መብት ብቻ ሳይሆኑ፣ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው በሚወጡ አዋጆችና ህጎች ገቢራዊ የሚሆኑ መሆኑን ነው። ይህም አንድ መብት እስከተሰጠ ድረስ፤ በዚያኑ ልክ መብቱን ህጋዊ በሆነ መንገድ ለማስፈፀም ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል ያስረዳናል።

እርግጥም በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የሚሰጡ መብቶች ከግዴታዎች ጋር የተቆራኙ ናቸው። እናም መብትና ግዴታን ነጣጥሎ መመልከት አይቻልም—ሁለቱም አንድም ሁለትም ስለሆኑ። ያም ሆኖ ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት ገደቦችን ለማስቀመጥ ሲል፣ ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብቶችን የመገደብ አካሄድን አይከተልም። እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ካለማወቅ አሊያም ከተለያዩ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎች በመነሳት መብቱን በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታ ላይኖር እንደሚችል ስለሚገነዘብ፤ የዴሞክራሲ አንድ እሴት በሆነው መቻቻል አማካኝነት ሆደ ሰፊ በመሆን የሚፈጠሩ ችግሮችን የማስተማርና የማሳወቅ መንገዶችን ተከትሎ ለመፍታት ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ለነገሩ መንግስት ይህን የሚያደርገው ለማንም ብሎ አይመስለኝም—የሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲሰፋና እንዲጠልቅ ካለው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት እንጂ።

ታዲያ በዚህ ፅሑፌ ላይ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ ሰባት ህገ መንግስታዊ መብቶችንና ገደቦችን በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ይህም መብቶቹን ከነ ገደቦቻቸው ማወቅ በዋነኛነት የመብቱ ተጠቃሚ ለሆኑት መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ለአጠቃላይ ዜጎች ጠቃሚ ስለሆነ የተደራጀ ግንዛቤን ይፈጥራል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ ሃሳብን በነፃነት ከመያዝና ከመግለፅ ጋር ህገ መንግስታዊ ከለላና ዋስትና ካለው መብት ውስጥ፤ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ሃሳብ የመያዝ መብት አንዱ ነው። ይህ መብት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውሰጥ የሰው ልጅ ያሻውን ዓይነት አስተሳሰብ የመያዝ መብቱ የህግ ከለላና ዕውቅና ያለው መሆኑን ይገልፃል። ሃሳብን መያዝ፤ ሳይተገብሩ የራስ ሃሳብን መያዝና አቋም መውሰድን እንዲሁም አግባብ በሆኑ ህጋዊ ማዕቀፎች ውስጥ ሃሳብን በነፃነት መተግበር የሚያሳይ ፅንሰ ሃሳብ ነው።

ፅንሰ ሃሳቡ የሰው ልጅ ይጠቅመኛል ወይም ይበጀኛል የሚለውን አስተሳሰብ መያዝና መተግበር እንደሚችል የሚያስረዳ ነው። በዚህ ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ሃሳብን መያዝ እና መግለፅ የተሰኙ ሁለት ጉዳዩች አሉ። ምናልባትም እነዚህ ሁለቱም ጉዳዩች በተናጠል አሊያም በአንድነት ሊገለፁ ይችላሉ። በተናጠል ሲገለፁ አንድ ሰው የመሰለውን ሃሳብ ይዞ ምንም ዓይነት ተግባራዊ ውሳኔ ላይወስድ የሚችልበትን ነባራዊ ዕውነታን ያመላክታሉ። በአንድነት ሲገለፁ ደግሞ፤ አንድ ሰው የመሰለውን ሃሳብ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባርም ሃሳቡን በፈለገው መንገድ እንዲያራምድ የሚያስችለውን አውድ ይፈጥሩለታል። ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖርበትም። ይህም በሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሰው ልጅ አንድን ሃሳብ ስለያዘ አሊያም የያዘውን ሃሳብ በፈለገው የመገናኛ መንገድ ስለገለፀ ሊጠየቅ አይችልም፤ ይልቁንም ህጋዊ ከለላ አግኝቶ እንዳሻው ሊገልፀው ይችላል። ይህም ፌዴራላዊ ስርዓታችን ካለፉት ስርዓቶች ምን ያህል የተለየና ዜጎችን መብቶቻቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ህጋዊ ከለላ የሚሰጥ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብት ከፕሬስ ጋር ተያይዞም ይገለፃል። እዚህ ላይ “ፕሬስ” የሚለው ቃል ሁሉንም የመገናኛ ብዙሃን ዓይነቶችን ከመወከል ባህሪው አኳያ ልንመለከተው የሚገባ ይመስለኛል። እናም ህገ መንግስቱ ፕሬስ በተቋማዊ አሰራሩ ነፃ እንዲሆንና ሁሉንም ዓይነት ሀገራዊ አመለካከቶችን እንዲያስተናግድ ህጋዊ ከለላ ሰጥቶታል። ይህም ፕሬስ በባህሪው ያለበትን ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እንዲወጣ ያስችለዋል። ማንኛውም ዓይነት አስተሳሰብ ያለ አንዳች ገደብ እንዲንሸራሸርም ያስችለዋል። ሆኖም ፕሬስ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ እንደ እኛ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።

የሀገራችን ህዝቦች ተስፋቸው ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲ ጋር የቶራኘ ነው። ለዘመናት አንገታቸውን ሲያስደፋ የነበረውን ድህነትን ድል ለመንሳት ቆርጠው ተነስተዋል። ይህን መከወን እንደሚችሉም ባለፉት 26 ዓመታት ገደማ ተጨባጭ ውጤቶችን ማየት ችለዋል። ለነገሩ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች በጥቂት ዓመታት ውስጥ የአስተማማኝ ሰላም፣ የፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለቤቶች መሆን ችለዋል። ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርም፤ ብዙዎቹ የአህጉሪቱ ሀገራት ማሳካት ያልቻሏቸውን መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶችን ተራምደዋል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ ሃሳብን በነፃነት ከመያዝና ከመግለፅ አኳያ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ  በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን የሚመለከተው አንኳር ጉዳይ ነው። መገናኛ ብዙሃኑ የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት ማናቸውንም አስተሳሰቦች እኩልና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሃሳብን በነፃነት ለመያዝና ለመግለፅ የተደነገገውን ህገ መንገስታዊ መብት ዕውን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም ወገኖች በእኩልነት የማስተናገድ ህጋዊም ይሁን ሙያ ግዴታ አለባቸው። በእኔ እምነት መገናኛ ብዙሃኑ ያን ያህል የደረጀ ባይሆንም እስካሁን ድረስ ሁሉንም ወገኖች በማሳተፍና ድምፃቸው እንዲሰማ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ወደፊትም ይህን የዴሞክራሲ መንገድ ይበልጥ በማስፋት የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ። እርግጥ እነዚህ በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉ አንኳር ሃቆች ሀገራችን ምን ያህል ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ ነው። እናም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሲባል እነዚህን አንኳር ቁም ነገሮች ያካተተ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy