Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሁሉም ጊዜ አለው ለማስታወቂያም

0 1,620

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

« ለሁሉም ጊዜ አለው» ብሏል አሉ ጠቢቡ ሰሎሞን። እውነት ብሏል አያ! ሁሉም ነገር በጊዜና በወቅቱ፣ በወጉና በአግባቡ ሲሆን ምንኛ ደስ ይል መሰላችሁ። መቼም ብዙ ጊዜ «ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው» ይሉትን አባባል እየተረትን መኖራችን ያየነውን የሰማነውን ጉድለት ሁሉ እንዳላወቅን እየታዘብን ጭጭ እንድንል ሳያደርገን አልቀረም። ግን ደግሞ አንዳንዴ «እንዴትና ለምን? ማለትን መልመድ ያለብን ይመስለኛል። ተናጋሪና ሰሚ ከተገኘ ማለት ነው።

ይሄን የጊዜ ነገር ካነሳነው አይቀር የማስታወ ቂያዎቻችንን ጉዳይም ማስታወሱ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል። እኔማ አንዳንዴ የሚታዩና የሚነገሩ ማስታወቂያዎችን ግድ መስማትና ማየት ስላለብን ብቻ የምናደርገው መስሎ ነው የሚሰማኝ። ወዳጆቼ! እስከዛሬ እኮ ብዙ ማስታወቂያዎችን አይተናል፣ ሰምተናልም። ግን ምንያህሎቹን ይሆን አምነን የተቀበልናቸው?በየትኞቹስ መልዕክት ይሆን የተማርንባቸው? መቼም በብዘዎቹ እንደምንገረም ሁሉ፣ጥቂት በማይባሉት ደግሞ ብሽቅ እንደምንል መገመቱ አይቸግርም። ለምን ከተባለ ደግሞ አብዛኞቹ ጊዜንና ቦታን ከግምት ያላስገቡ መሆናቸው እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነውና። እነዚህን ማስታወቂያዎች ግን ወደድንም ጠላንም መስማትና ማየታችን ግድ ሊለን ይችላል።

መቼም የዛሬን አያድርገውና ከጥቂት ወራት በፊት ያሳለፍነውን የቅዝቃዜና ያልተለመደ የብርድ ጊዜን የምትዘነጉት አይመስለኝም። እንዴታ! እንደልብስ ደርበን እንደውሃ ቸልሰን የተንቀጠቀጥንበትን ያን አጋጣሚ ማን በቀላሉ ይረሳዋል? አጥንትን ዘልቆና ውስጥን አራቁቶ ግራ ሲያጋባን በነበረው የብርድ በትርስ ማን ያልተገረፈ ማንስ «እትትት…» ሲል ያልተንዘፈዘፈ ይኖራል? ብዙዎቻችን ጠዋትና ማታችንን ፈርተን ደጁንና ቤቱን መለየት እስኪያቅተን በቅዝቃዜ የራድንበትንና በሙቀት ናፍቆት የዋተትንበት ጊዜ እኔም ሆንኩ እናንተ በዋዛ አንረሳውም። ብቻ መልሶ አያምጣብን!!

ይህ እውነት በነበረበት በአንዱ ቀን ታዲያ እንደተለመደው እጆቼንና ፊቴን በወፍራም ልብሶች ጀቡኜ እየተንዘፈዘፍኩና ጥርሴን እያንገጫገጭኩ ከቤቴ ወጣሁ። ይህ መሆኑ ደግሞ የዛንዕለት ብቻ አልነበረምና በመንገዴም ገና አብሮኝ የሚዘልቀውን ውስጠ ገብ ቅዝቃዜ ማሰቤ አልቀረም። መቼም በዚህ ወቅት በላይ በላዩ እንደውሃ የሚፈሰውን ብርድ እንደልጅ ደልሎ የሞቀ ትንፋሽን በቀላሉ ማግኘት አይታሰብም። ከሚሄዱቡት ስፍራ በቶሎ ለመድረስ ደግሞ የታክሲው ውጣውረድና የመንገዱ ቀና ያለመሆንም ሌላው ዕንቅፋት ነው።መቼም በዛ በብርድ አለንጋ የተሸነቆጠ ሁሉ ያን ጊዜ ዛሬ ላይ ሆኖ በቀላሉ ይረሳዋል ብዬ አልገምትምና ጨዋታዬ ሁሉ ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆንብኝ እሰጋለሁ።

እናላችሁ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ስጠብቀው የቆየሁትን ታክሲ በግፊያ አገኘሁና ወደ ውስጥ ዘለቅሁ።እውነቱን ለመናገር በዛን ሰዓት ብቻዬን ከምሆን ይልቅ በትርፍ ተጭኖ ጎኔን የሚያሞቀኝ ሰው እስከመፈለግ ተመኝቼ ነበር።ደግነቱ ታክሲው በቶሎ ሞላና ጉዞ ጀመረ።ይህ በሆነ አፍታም ሲደመጥ ከነበረው ሬዲዮ በተከታታይ የተወሰኑ ማስታወቂያዎች ተለቀቁና ማድመጥ ጀመርን። መደዳውን ከተሰሙት ማስታወቂያዎች መሀል ግን የአንዱ መልዕክት ብሽቅ አደረገኝ።

ወዳጆቼ! ወቅቱ የከፋ የሚባል ብርድና ያልተለመደ ቅዝቃዜ ውስጥን የሚያርድበት ጊዜ ስለመሆኑ እንዳትዘነጉ።የዛኔ የተለቀቀው የአንድ ለስላሳ መጠጥ ማስታወቂያ ግን ምን ማለት ጀመረ መሰላችሁ?

«ኧረረ…! ኧረረ …! ሙቀት፣ ኧረረ … ! ፀሐይ፣ ሙቀቱ በዚሁ ከቀጠለ እኮ !ዶሮ እራሷ የተቀቀለ እንቁላል መጣል ሳትጀምር አትቀርም። ፀሐዩ በዚሁ ከቀጠለ በቆሎ ማሳ ላይ እያለ ፈንዲሻ ይሆናል» በሁለት ሰዎች ቅብብል የሚተላለፈው መልዕክት ይህን ካለ በኋላም በሳቅ በታጀበ ድምጽና በተለየ ስሜት ቀዝቃዛውን የለስላሳ መጠጥ ግጥም የማድረግን ተገቢነት በመጠቆም ይሰናበታል።

እስቲ ይታያችሁ አሁን ይህን ማስታወቂያ ጠዋትና ማታ በብርድ አንጀቱ ለሚንዘፈዘፍ አድማጭ ማሰማቱ ተገቢ ነበር? እንዲያ ፀሐይ በቅዝቃዜ በተረታችበትና ለብ ያለ ትንፋሽ እንኳን ብርቅ በሆነበት ጊዜ የሙቀቱን ማየል እየተረኩና በግድ እያሳመኑ፣ ዓይናችሁን ሸፍኑና እናታላችሁ ማለቱ አግባብ ነውን? እኔ ግን በወቅቱ ማስታወቂያውን በሰማሁ ቁጥር ከመብሸቅ አልፌ «ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰውን ያስተርከኝ ጀምሮ ነበር።

በእርግጥ ይህ ማስታወቂያ አሁንም በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች መተላለፉን ቀጥሏል።ሆኖም እያንዳንዱ መልዕክት ከወቅቱ የአየር ሁኔታ ጋር የሚስማማ በመሆኑ ብንሰማው የሚያስገርመን ሊሆን አይችልም። ሙቀቱም ሆነ ፀሐዩ እዛ ላይ እንደተጠቀሰው የማሳውን በቆሎ ፈንዲሻ ባያደርግና ዶሮዋን የተቀቀለ ዕንቁላል ባያስጥልም አየሩ በእርግጥም ተቀይሯልና ቀዝቃዛ ለስላሰን ቢገባበዙበት አያስከፋም።

አንድ ወቅት ለረጅም ጊዜ በቴሌቪዚን መስኮት ይተላለፉ ከነበሩ ማስታወቂያዎች መሀል በአንዲት ተወዳጅ አርቲስት ይቀርብ የነበረውን የፍራሽ ማስታወቂያ አልዘነጋውም።ይህ ማስታወቂያ የምርቱን ጥራትና የዋጋውን ተመጣጣኝነት ለማሳየት የተጠቀመበት ማሳያም መልካም እንደነበር ትዝ ይለኛል።ይሁን እንጂ ፍራሹን የምታስተዋውቀው ሴት ከምታስተላልፈው መልዕክት መጨረሻ ላይ ሁሌም የምትጠቀምበት «ደህና እደሩ» የሚለው ቃል ለብዙዎች የተመቸ አልነበረም። ለምን ከተባለ ደግሞ ይህ አባባል ማታ በመኝታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ማለዳውንና በምሳ ሰዓት ጭምር እንዲተላለፍ ሆኖ ተመቻችቷልና።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በበአላት ሰሞን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችንና የጊዜ ሁኔታንም አብሮ መጥቀስ ይቻላል። ተደጋግሞ እንደሚስተዋለው የተለያዩ በአላትን መድረስ አስመልክቶ ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁ አንዳንድ ድርጅቶች «መልካም በአል» በሚል የበጎ ምኞት ማጀቢያ መጠቀማቸው የተለመደ ነው። አስገራሚው ጉዳይ ግን ይህ መሆኑ አይደለም።ማስታወቂያው ወቅቱን ጠብቆ ከተላለፈ በኋላ ምንም አይነት የጊዜ ለውጥና ማሻሻያ ሳይደረግለት «መልካም በአል» የሚለውን ቃል እያስቀደመ ለተከታታይ ወራት መተላለፉን ይቀጥላል።

ይህ ሲሆን ለሚሰማውና ለሚመለከተው ሁሉ የበአሉ መምጣትና መሄድ የሚያደናግር ቢሆንም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ግን የሚያስጨንቃቸው አይመስልም። አስነጋሪዎቹ ገንዘብ ስላወጡና አስተላላፊዎቹም ስለተቀበሉ ብቻ ባልተገባ ጊዜ ማስታወቂያው እስኪሰለች መለቀቁ የእነሱ ጉዳይ መስሎ አይሰማቸውም። ይሁን እንጂ በቅድሚያ መልዕክቱን ለሚያስ ተላልፉለትና «ደንበኛ ንጉስ ነው» ለሚሉት ተጠቃሚ አክብሮት ሊኖራቸው በተገባ ነበር።

ከምንም በላይ ግን እነዚህ ሚዲያውን በስፋት የተቆጣጠሩ አንዳንድ ማስታወቂያዎች እንዳሻቸው የመሆናቸውን ጉዳይ አስተውሎ ልጓሙን በአግባቡ የሚይዝ አካል ሊኖር ይገባል። የመልዕክቱን መተላለፍ ብቻ ሳይሆን የሥራውን በተገቢ አቅጣጫ መጓዝን የሚለይም ብቁ የሚባል ባለሙያ ሊኖር ያስፈልጋል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ከሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች መሀል የጊዜንና የመልዕክትን ይዘት ብቻ አንስተን በጥቂቱ መዘዝን እንጂ ተነግረው የማያልቁ እንከኖች መኖራቸውን አብዛኞቻችን የምናውቀው ነው።

ሁልጊዜ መወቃቀሱ ብቻ መፍትሄ ነው ባይባልም የአንዱን ስህተት ሌላው የመደጋገሙ ልማድ ግን በበጎነት የሚኮረጅ አይደለም። ባለማስታወቂያ ድርጀቶችም ሆናችሁ የጉዳዩ ባለቤቶች ለሌላው ከማድረሳችሁ በፊት በቅድሚያ እናንተ ልታምኑበትና በአግባቡም ልትመረምሩት ይገባል። ከራስ ያልመነጨ ሀቅ ለሌላው እውነት ሆኖ ሊያሳምን አይችልምና። አበቃሁ!

 መልካምስራ አፈወርቅ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy