Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለ74 አዲስ የሃይማኖትና ዕምነት ተቋማት ሕጋዊ ፍቃድ ተሰጠ

0 694

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ74 አዲስ የሃይማኖትና ዕምነት ተቋማት ሕጋዊ ፍቃድ መስጠቱን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት በ2009 ዓ.ም የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ ወራት አቅጣጫ ላይ የተዘጋጀ የጋራ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል፡፡ ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ለ74 አዳዲስ የሃይማኖትና እምነት ተቋማት ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ በሕዝቦች መካከል ያለውን የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ለማጎልበት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ተከናውነዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ጌታዋ ደስታው እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከኢትዮጵያ የሃይማኖር ጉባኤ ጋር  ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በዚህም የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ለ72 አዳዲስ የሃይማኖትና የእምነት ተቋማት ሕጋዊ ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ74 ተሰጥቷል፡፡ ለ190 ነባር የሃይማኖት ተቋማት የፈቃድ እድሳት ለማድረግ አቅዶም ለ30ዎቹ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

አቶ ጌታዋ እንደተናገሩት፤ ለ74 ተቋማት ሕጋዊ ፍቃድ ሲሰጥ ከተቀመጠው ስታንዳርድ ባጠረ ጊዜና በተሻለ ጥራት በመሰራቱ ውጤታማ አፈጻጸም ታይቶበታል፡፡ በአንጻሩ የፈቃድ እድሳቱ አገልግሎት አፈጻጸም ከ15 ነጥብ 79 በመቶ አልዘለለም፡፡ ይህ ተቋማቱ የፍቃድ ወረቀቱን ከወሰዱ በኋላ የማሳደስ ዝግጁነት ማነስ ውጤት ሲሆን፤ በሂደትና በአሠራር መመሪያው የሚፈታ ይሆናል፡፡

ለሃይማኖትና እምነት ተቋማቱ የሕጋዊ ሰውነት ፈቃድ ከመስጠትና ፈቃድ ከማደስ አገልግሎት ባሻገር በሕዝቦች መካከል ያለውን የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታዋ፤ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመሆን ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰላም አብሮ በመኖርና በመቻቻል እስቴች፣ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥና መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች አፈታት፣ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌዎች፣ ሴኩላሪዝምና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንዲሁም የማህበረሰብ ተኮር ፀረ አክራሪነትና ትግል ዙሪያ ሰነዶች ተዘጋጅተው ከ3 ሚሊዮን 795ሺ በላይ ለሚሆን ሕዝብ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በአገር ሰላምና ልማት ላይ በጋራ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሁለቱ አካላት ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛል፡፡ ለአብነትም አዳዲስ የተመዘገቡ ተቋማት ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የተከናወነ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ጉባኤው ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር አብሮ እየሰራ ነው፡፡ ይህ አሠራር አዳዲሶችን ከመመዝገብ ባሻገር ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል በመሆኑ ትብብሩ ሊጠናከር ይገባዋል፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አገርና ሕዝብ የሚያስፈልገው ዘላቂና አስተማማኝ ዋስትና ያለው ሰላም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከሃይማኖት ተቋማት ጋር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ ከመሆናቸውም በላይ ሁለቱ አካላት የበለጠ እንዲቀራረቡና አብረው እንዲሰሩ አስችሏል፡፡ በመሆኑም ሁለቱም አካላት በአገሪቱ ያሉ ሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴት ታሪካቸውን ለማጠናከር ኃላፊነታቸውን ያለማቋረጥ ሊወጡ ይገባል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy