Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም አስተዳደር ከሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ አኳያ ሲፈተሽ

0 601

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልካም አስተዳደር ከሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ አኳያ ሲፈተሽ /  ታዬ ከበደ/

           ሀገራችን በነደፈችው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እውን የሆነው  ፈጣን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በአገር ውስጥም ከአገር ውጭ ሰፊ ዕውቅና እና ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዕቅድ የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ከመፍጠር ባለፈ ምርትና መርታማነት እንዲያድጉ ያደረገ ነው፡፡ በዕድገቱም አርሶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት ማደግ እንደሚቻል አረጋግጠዋል፤ ለላቀ ዕድገት እንዲተጉም ከፍተኛ መነቃቃትን እየፈጠረም ነው፡፡  

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጠንካራ የማስፈፀም አቅም ያላቸው መንግስታዊ መዋቅር የመፍጠር፣ ግልፅነትን የማስፈንና ሙስናን ከምንጩ የማድረቅ፣ የህዝብ ተሳትፎን የማረጋገጥ እና የባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የማካተትና የመተግበር አቅጣጫዎች ተይዘው በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማስፈን የኪራይ ሰብሳብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን ለመቀነስ በየደረጃው የሚደረጉ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የህብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠናከርበትና ከመንግስት ተቋማት ጋር ቋሚ ግንኙነት የሚፈጥርበት አሰራርም ተዘርግቷል፡፡

በተለይም የሀገራችን ህዳሴ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ድርጊት ከምንጩ ለማድረቅ ሲባል መንግስት የራሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር በህግ ፊት በማቅረብ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በዚህም አስተማሪ በሆነ መንገድ ትምህርት ለመስጠት ሞክሯል።

ምንም እንኳን የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ባይሆንም፣ ድርጊቱን በሂደት የመቅረፍ ስራዎች ተከናውነዋል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይም በዘርፉ ዙሪያ የሚከናወነው ተግባርም በቀዳሚው የዕቅድ ዘመን የተካሄደውን ሁሉን አቀፍ ክንዋኔዎች የሚያጠናክርና አዳዲስ አሰራሮችን የሚከተል ነው።

ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገራችን የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ በሚደረገው ጥረት ወሣኙን ምዕራፍ የያዘ ነው። የዜጐችን እኩል የልማት ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመገንባት የላቀ አስተዋፅኦ ያለው ዕቅድ ነው፡፡

ስለሆነም የዕቅዱ ዋና መነሻ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ረድፍ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የማሰለፍ ሀገራዊ ራዕይን የነገበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም በቀጣዩ የአምስት ዓመት ዕቅድ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በጥቅሉ ሲታዩ፣ ወደዚሁ ሀገራዊ ራዕይ እንዲያደርሱን ሆነው የተቀረፁ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ ሀገራዊ የሴክተር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችንም በመነሻነት የያዘ ነው። ሁላችንም እንደምንገነዘበው በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ እንዲሁም በየደረጃው የሕዝቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ ብሎም የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ለመገንባት በሚገባ የተዘረዘሩ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው በመተግበር ላይ ናቸው፡፡

ታዲያ ከላይ የተዘረዘሩትን ዋነኛ ስራዎች ማከናወን ከተቻለ የፖለቲካ ኢኮኖሚው ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ከያዘበት ወደ ልማታዊነት የበላይነት ወደ ያዘበት መሸጋገሩ አይቀሬ ነው። በመሆኑም በአንድ ወገን ልማታዊነትን የሚያጐለብቱ ድጋፎችን በጥራት በማቅረብ፣ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምንጭ ሆነው የተለዩትን ጉዳዮች በልዩ ትኩረት በማድረቅ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ልማታዊነት የበለጠ እንዲጐመራና የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ማድረግ ይቻላል። ይህም መልካም አስተዳደርን ዕውን ከማድረግና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እጅግ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል።

ይህ ማለት ግን እስከዛሬ ድረስ አንዳችም ዓይነት የመልካም አስተዳደር ስራዎች ገቢራዊ አልሆኑም ማለት አይደለም። መንግስትና ህዝቡ ችግሩን በሂደት ለመፍታት ሀገር አቀፍ የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በማቋቋምና ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳዳርን ለማስፈን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ህብረተሰቡን በተደራጀ መልኩ የማንቀሳቀስ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ እስሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ቢሆኑም አሁንም ጠንካራ ሥራ መከናወን እንዳለበት አይካድም።

ልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መገንባትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የዛሬ 14 ዓመት ገደማ በተካሄደው የተሀድሶ መስመር ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ታዲያ አሁንም በገጠር ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ያለው እንዲሆንና የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል።

በአንፃሩም በከተሞች የበላይነት ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቡ ዛሬም ስር የሰደደ መሆኑን ነው። እናም ልማታዊነትን ይበልጥ በማጐልበትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከምንጩ በማድረቅ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ልማታዊ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡

ይህን የዕቅዱን ትልም ዕውን ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩና የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው ከህዝቡ ጋር በተደራጀ መንገድ በመቀናጀት መስራት ይገባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ‘ይህ ስራ የእገሌ ነው’ ሳይባል ሁሉም የበኩሉን ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል። እርግጥ ሀገራችን አረጋግጠዋለሁ ብላ ለተነሳችው የህዳሴ ጉዞ ትልልቆቹ አደጋዎች ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። እናም አደጋዎቹን ለመዋጋትና ትግሉን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እሳቤ የበላይነት ለመደምደም በርካታ ስራዎችን ማከናወን የግድ በመሆኑ በዕቅዱ ተይዟል።

በተለይም የመንግሥትን ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ይበልጥ የማስፈፀምና አገልግሎቶችን ለዜጐች በብቃት የማድረስ ዋና ተልዕኮ የተሸከሙት ልማታዊ የፖለቲካ አመራሩና የፐብሊክ ሰርቪስ የመፍጠር እንዲሁም በሁሉም የአስተዳዳር እርከኖች በየደረጃው የሚገኘውን የሰው ኃይል በተከታታይ አጠናከሮ ማብቃት በቁልፍነት የሚከናወን ተግባር ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት እያካሄደ ካለው ጥልቅ ተሃድሶ ጋር የሚመጋገብ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም በዕቅድ ዘመኑ ማንኛውም ተቋም በአሰራሩና በአደረጃጀቱ የመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥን ባልተሸራረፈ መልኩ በመከተልና የአገልግሎት አሰጣጡም ተገልጋዮችን የሚያረካ፣ ቀልጣፋና ተልዕኮውን በተሟላ ውጤታማነት መፈጸም እንዲችል አስፈላጊው ክትትልም ሆነ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ የውጤት ተኮር ስርዓት ትግበራው የተጠናከረ የመንግስት የአፈጻጸም አመራር ማዕቀፍ እንዲሆንም ይደረጋል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪሱ ተግባራት በዚህ ብቻ የተገደቡ አይደሉም። ፈጻሚው አካል በለውጥ ሰራዊት አግባብ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል የተጠናከረ የለውጥ ሰራዊት እንዲገነባ ይደረጋል፤ የአቅም ግንባታ ስራው እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ይህ ሲሆንም ከፐብሊክ ሰርቫንቱ አኳያ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተቀረፉና በአመዛኙ መልስ እያገኙ ይሄዳሉ።

ተደጋግሞ እንደተገለፀው በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ጉዳይ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ የህዝብ እርካታና አመኔታ ደረጃ አሁን ካለበት 60 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ግብ ተይዟል፡፡

ለመልካም አስተዳደር መስፈን ዋና መሳሪያ የሆነውን የግልፅነትና ተጠያቂነት ሥርዓት በሁሉም መንግስት ተቋማት ለመዘርጋት በሚቀጥለው የዕቅድ ዘመን በፌዴራልና በክልል የመንግስት ተቋማት የዜጎች ቻርተርን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር በተቋማት የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር የበለጠ እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡  በሁለተኛው የልማት ዕቅድ በትግበራ ላይ ያሉት ሁሉም የሪፎርም ፕሮግራሞች በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩና ለውጡ ስር እንዲሰድና ተቋማዊ ባህል እንዲሆን ብርቱ ጥረት ይደረጋል፡፡ ለዚህ ጥረት ደግሞ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እናም በጥልቅ ተሃድሶው ውስጥ በንቃት በመሳተፍ መልካም አስተዳደር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተያዘለት ግብ መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy