Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መረጋጋትን ከማዘናጋት ለመለየት ሲባል

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

መረጋጋትን ከማዘናጋት ለመለየት ሲባል
(ሰለሞን ሽፈራው)
ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የምትመራበትን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት “በአንድ ወይም ደግሞ በሌላ መንገድ ለማስገድ ቆርጠው ስለመነሳታቸው” የሚናገሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸው የሚካድ ጉዳይ አይሆንም፡፡ እናም እነዚሁ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ መወገድ አለበት ብለው የሚያምኑ የትምክህት፤ እንዲሁም የጠባብ ብሔርተኝነት ጽንፈኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብን በማቀንቀን የሚታወቁ ቡድኖች፤ የኢፌዴሪን መንግሥት ለመደርመስ ያለመ የአመፅ ተግባር ለመቀስቀስ ሲሉ፤ በተደራጀ መልኩ የሚፈፅሙት ፈርጀ ብዙ ደባ መገለጫ የሆኑ ሁከት እና ብጥብጥ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡
በተለይም ደግሞ የጎረቤት ኤርትራ ግፈኛ አገዛዝ ፤ከዚያች አገር ሕዝብ ጉረሮ ላይ እየቀማ ቀለብ የሚሰፍርላቸው፤ እንደነ ኦ.ነ.ግ እና ግንቦት ሰባት ዓይነቶቹ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ነውጠኛ ቡድኖች፤ እቺን ሀገር ወደለየለት የትርምስ አደጋ የሚያስገባ የአመፃ ተግባር ስትራቴጂ ነድፈው፤ ይሔንኑ ዕቅዳቸውን ለማሳካት ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት አፍራሽ እንቅስቃሴ እጅግ አሳሳቢ ገፅታ እየተላበሰ እንደመጣ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ይህን የምንልበት ዋነኛ ምክንያትም፤ ሁለቱ ጽንፈኛ ቡድኖች ሥርዓቱን በኃይል ርምጃ ለማስወገድ ያለመ ግልፅ እና ግልጽ ልሆነ (ህቡዕ) እንቅስቃሴ በማድረግ ዕኩይ ተግባር የመፈፀም እንቅስቃሴ ላይ እንደተጠመዱ የሚነገርላቸው የጥፋት ቡድኖች፤ ከባህር ማዶው አክራሪ ዲያስፖራ ጭፍን እና ድፍን ያለ የጥላቻ ፖለቲካ የሚመነጭ ስሜታዊነት በተከተለ ተቃውሞ እየተነሳሱ የሀገር ውስጡን ሰላም እና መረጋጋት ከመሠረቱ ለማናጋት የሚቃጣቸው ወገኖች ቁጥር መጨመሩ ነው፡፡
ምንም እንኳን ሀገራችንን ከመላው የብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦቿ ብዝሃነት በሚመነጩ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖት እና የሥነ-ልቦና ልዩነቶች ምክንያት የማፈራረስ አጀንዳ ነድፈው የሚንቀሳቀሱት የትምክህት እና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ እሳቤ አቀንቃኝ ኃይሎች፤ በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመቀልበስ ያለመ ተቃውሞ ሲያራምዱ ያልተስተዋሉበት አጋጣሚ እንዳልነበር ቢታወቅም፤ ሁለቱን ተቃራኒ ፅንፎች ወክለው ሥርዓቱን አደጋ ለመጣል ሲኳትኑ የቆዩት አክራሪ ቡድኖች ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የተጠናከሩበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ ግን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት ሊቆጠር የሚቻለውም፤ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለሀገራችን የብሔር፣ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ያጎናፀፋቸውን ሕገ መንግሥታዊ የቡድን እና የግለሰብ መብቶች ያለአንዳች መሸራረፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ እንብዛም የሚያመረቃ ሥራ ሳንሰራ መቆየታችን እና እንዲሁም ደግሞ ፅንፈኛዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍተቶቹን ሁሉ ሊጠቀሙባቸው ከመሞከር አለመቦዘናቸው እንደሆነ ኢህአዴግ ራሱም በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው አምኖ የተቀበለው ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ሀገሪቷን የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት ገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ጭምር ራሱን በጥልቅ እንዲፈትሽ የተገደደበት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ባፈጠጠ እና ባገጠጠ መልኩ ጎልቶ የሚንፀባረቅ አሳሳቢ ነባራዊ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የዘመነ ፌስ ቡክ ዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የወቅቱን ፈርጀ ብዙ የመረጃ ማሠራጫ አውታሮች ሁሉ፤ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ሀገር ቤት የሚያዛምቱት መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ፤ ከጭፍን የጥላቻ ስሜት የሚመነጭ ጽንፈኛ አቋምን የሙጥኝ የሚሉ ወጣት ዜጎቻችን እንዲበራከቱ ያደረገ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለማሳደሩም ነው ታዛቢዎች የሚስማሙበት ጉዳይ፡፡ ይልቁንም ደግሞ፤ የአስመራው ግፈኛ አገዛዝ ከፈረደበት የኤርትራ ሕዝብ ጉረሮ ላይ እየቀማ ቀለብ የሚሰፍርላቸው፤ ኦ.ነ.ግ.ን እና ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉት የለየላቸው ሽብር ፈጣሪ ቡድኖች፤ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ ስትራቴጂ ነድፈው ከሚንቀሳቀሱበት ፈርጀ ብዙ የጥፋት ተልዕኮ የመፈፀም እና የማስፈፀም ዕኩይ ተግባር ጋር በተያያዘ መልኩ ተደጋግሞ የሚስተዋል የጎዳና ላይ ነውጥ፤ አሊያም ደግሞ ሁከት እና ብጥብጥ፤ ሀገራችን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጭምር የላቀ ከበሬታ እንዲቸራት ያደረገውን አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት ክፉኛ ሊያናጋው የሚችል አደገኛ አዝማሚያ አስከትሎብን በመገኘቱ ምክንያት፤ የኢፌዲሪ መንግሥት የአስቸኳይ ጌዜ አዋጅ ለመደንገግ መገደዱ አይዘነጋም፡፡
እናም ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈፃሚ መሆን በመቻሉ ምክንያት የተቀለበሰውን እጅግ አሳሳቢ የሀገራዊ ደህንነት ሥጋት ስናስታውስ፤ አሁንም ድረስ ከውስጣችን ያልጠፋ የእንዴት ሊሆን ቻለ ግራ መጋባት ስሜት እንቅልፍ ነስቶን መሰንበቱን ነው በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ የምሻው፡፡ እንዲያውም ያን ሀገር አውዳሚ የአንድ ሰሞን ሁከት እና ብጥብጥ ከማቀነባበር እስከ መተግበር እጃቸው እንደነበረበት የሚገመቱ የቀለም አብዮት ናፋቂ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞችማ፤ ጉዳዩን “ዳግማዊ ኦሮማይ” ሲሉ የገለፁበት አግባብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
እነዚሁ የመዲናችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ልሂቃን በዚያው የሁከት እና ብጥብጥ ሰሞን “ዳግማዊ ኦሮማይ” በሚል ርዕስ የተፃፈ እና ሥርዓቱ እንዳበቃለት የሚያትት “ትንተናቸውን” እንዳስነበቡን ሁሉ “በፈንጂ ላይ የቆመው ሰው አጭር ታሪክ” የተሰኘ “ማስቦኪያ” ርዕስ የሰጡትን ሌላ “ልብ ወለድ” ቢጤ ጽሑፍ እዚያው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አቅርበው እንደነበርም ትዝ ይለኛል፡፡ እንደነርሱ ሥነ-ጽሑፋዊ ዘይቤ ፈንጂ ላይ እንደቆመሰው የተቆጠረው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ ወይም ደግሞ የሚመራው የዚች አገር መንግሥት መሆኑ ነው፡፡ ይህን የሚጠራጠር አንባቢ ካለ በተለይም ከጳጉሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሣምንታዊ ውስጥ ታትሞ የወጣውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ፈልጎ እንዲመለከት እየጠቆምኩት እኔ ግን የመጣጥፌ ዋነኛ ትኩረት ወደሆነው ነጥብ ስመለስ…
ስለዚህ ላለፉት ስድስት ወራት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ሰላም ወዳዱን አብዝሃ ኅብረተሰብ ከብርቱ የደህነት ሥጋት እና እንዲሁም ደግሞ በሀገር አውዳሚው የሁከት እና የብጥብጥ ተግባር አራማጆቹ ቡድኖች ምክንያት ሊደርስበት ይችል ከነበረው ተጨማሪ የሀብት እና የንብረት ኪሳራ የተደገ የመሆኑን ያህል፤ የ“ኦሮማይ ትንቢታቸውን” ያከሸፈባቸው ጥቂት ወገኖችም እንዳሉ ልብ ይባል እላለሁ፡፡ ለነገሩ ፅንፈኝነት የተጠናወተውን የትምክህት እና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በማንቀንቀን የሚታወቁትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጎራዎች የሚወክሉት ኃይሎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለመውጣቱ የሰማንበት ዜና ከተነገረበት ቀን ጀምሮ ሐዘን የመቀመጥ ያህል በሚቆጠር የድንጋጤ ስሜት ተውጠው እየያቸውን ሲያስነኩት መስተዋላቸው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
በተለይም ደግሞ ኑሯቸውን በበለፀጉት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ውስጥ ያደረጉ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ፖለቲከኞች፤ እዚህ አገር ቤት ተግባራዊ ስለተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መስማታቸውን ተከትሎ ለያዥ ለገናዥ እስኪያቆቱ ድረስ “ቡራ ከረዩ” ሲሉ መስተዋላቸውን ነው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ የመጡን ወገኖች የሚናገሩት፡፡ ለአብነት ያህልም አንድ በቅርቡ ከባህር ማዶ የተመለሰ ወዳጃችን “ብለው….! ትምክትተኞቹ ኃይሎች ኢሳት ላይ፤ የኦ.ነ.ግ.ን ጠባብ ብሔርተኛ አቋም የሚያራምዱት ቡድኖች ደግሞ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የተሰኘው የሳተላይት ቴሌቭዢን ላይ በየቀኑ የሚያወሩት ነገር በሙሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማውገዝ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥን ከመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልታሰረ ሰው ይገኛል የሚል ግምት አልነበረኝም” ሲል ነው ትዝብቱን ያጫወተን፡፡ ተጠቃሹ ሚዲያ ተብዬዎች፤ ሻዕቢያ ቀለብ ለሚሰፍርላቸው፤ ለነኦ.ነ.ግ እና ለነግንቦት ሰባት የለየለት ግብረ ሽበራ ፕሮፖጋንዳዊ ሽፋን ለመስጠት ሲባል ብቻ የተቋቋሙ የቡድኖቹ ልሳናት እንደመሆናቸው መጠን ግን፤ ጉዳዩ እንብዛም አላስገረመንም፡፡ እንዲያውም በወቅቱ አብረውን ከነበሩት ሰዎች መካከል አንደኛው “እነርሱ ሌላ ምን እንዲሉ ይጠበቅ ኖሯል ወዳጄ? ኢህአዴግ ከ17 ዓመታት እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግል በኋላ የተቆጣጠራትን መዲናችንን አዲስ አበባን ሳይቀር በጥቂት ቀናት የቀለም አብዮት እንደሚቀሙት አምነው ነበር እኮ!” ሲል በቀልድ መልክ የተናገረው እውነት ምን ያህል እንዳሳቀኝ አይረሳኝም፡፡
በእርግጥም ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እቺን ሀገር የነሶሪያ እና የነየመን አሳዛኝ ዕጣ እንዲገጥማት የሚያደርግ የጥፋት ድግስ ደግሰውልን የነበሩት አመፅ ናፋቂ ኃይሎች ለዓመታት በዘለቀ የሴራ ፖለቲካቸው የነደፉትን የትርምስ ስትራቴጂ ያመከነ ተግባር ፈፀወሟል፡፡ ይህን ሥልጣን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ እንዲገኝ ያደረጉት አስገዳጅ ችግሮቻችን አሁን ላይ በማያሻማ መልኩ ስለመቀልበሳቸው አረጋግጠናል ማለቴ አይደለም፡፡
በግልፅ አነጋገር፤ አደገኛውን አዝማሚያ ዳግም ሊስስት በማይችልበት ደረጃ ማስቀረት ካለብን፤ አሁንም የደፈረሱ ነገሮችን በደንብ የማጥራት፤ የተጣመሙ ጉዳዮችንም በቅጡ የማቃናት ሀገር አቀፋዊ የቤት ሥራ ልንሠራ እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ እንግዲያውስ ለዚህ መጣጥፌ “መረጋጋትን ከማዘናጋት ለመለየት ሲባል” የሚል ርዕስ የሰጡትም ያለምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቅስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲቆይ የተደረገበትን የኮማንድ ፖስቱ ጥያቄ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ከልብ የሚደገፍ ሆኖ እንዳገኘሁት ለማመልከት እንጂ፡፡ ስለዚህ፤ ቀሪዎቹ አራት ወራትም ኮማንድ ፖስቱ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ወደ ቅድመ 2008ቱ አስተማማኝ ቁመናው የመመለስ አመርቂ ተግባር የሚፈፅምባቸው እንዲሆኑ እየተመኘሁ እነሆ የዛሬውን ጽሑፌን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

  • መዓሰላማት!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy