Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መሰረታዊ ሸቀጦችን በአዲስ መልክ ለማቅረብ የተቀረጸው አሰራር በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል

0 629

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መሰረታዊ ሸቀጦችን በአዲስ መልክ ለማቅረብ የተቀረጸው አሰራር በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራልበአዲስ አበባ ከተማ እየተፈጠረ ያስቸገረውን የስኳርና የዘይት አቅርቦት ችግር ይፈታል የተባለው አዲሱ የነጋዴዎችና የሸማቾች ትስስር በሚቀጥለው ሳምንት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን የአስተዳደሩ የንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው አዲሱ አሰራር ከዚህ ቀደም የነበረውን የሸማቾች ችግር ይፈታል ቢልም አንድ አንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት አዲሱ የሸማቾችና የችርቻሮ ነጋዴዎች ትስስር ችግሩን ይፈታዋል ብለው እንደማያምኑ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

የቢሮው የንግድ ዘርፍ ክትትልና ቁጥጥር የስራ ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን በየነ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በከተማዋ በአቅርቦት ውስንነትና ነጋዴዎች በሚፈጥሩት ሰው ሰራሸ እጥረት ምክንያት ሸማቾች ስኳርና ዘይት በሚፈልጉት ጊዜና መጠን እያገኙ አይደለም። በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅርፍ ቢሮው የሸማቾችን ወርሀዊ ፍላጎትን መጠን በመለየት በአዲስ መልክ በአካባቢያቸው ካሉ ሱቆች ጋር የማስተሳሰር ስራ ተሰርቷል።

አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አቶ ካሳሁን ገልፀው፤ በክፍለ ከተማ ፣ በወረዳና በቀጣና ደረጃ መሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦችን ማግኘት ያለባቸው ሸማቾችን በእማወራ፣ አባወራና ተከራይ ግለሰቦች በሚል የመለየት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

«ከዚሁ ጎን ለጎን በቢሮ ደረጃ መሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦችን የምናስተሳስርበት ካርድ አሳትመናል” ያሉት ቡድን መሪው፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በአስሩም ክፍለ ከተሞች በተመረጡ አስር ሞዴል ወረዳዎች በሙከራ (በፓይለት ፕሮግራም) ደረጃ ስራ ይጀምራል» ሲሉ አስታውቀዋል።

በተመረጡ ወረዳዎች የተጀመረው የንግድ ትስስር ውጤታማነት ታይቶ በቀጣይ በሁሉም ቀበሌና ወረዳዎች ለማስጀመር ዝግጅት መደረጉንም አቶ ካሳሁን ጠቁመው፤ በአዲስ አበባ በከተማ በአዲሱ አሰራር መሰረት 920 ሺ ዜጎች ይመዘገባሉ ተብሎ ቢታቀደም ከዚህ በላይ ቁጥር ያለው የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎቱን ለማግኘት መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ እንዳሉትም የፓይለት ፕሮግራም የተመረጠበት ዋናው ምክንያት ከተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚነሱ የአሰራር ክፍተቶችን ደረጃ በደረጃ መፍትሔ ለመስጠትና ያለውን የአሰራር ክፍተት በትክከል ለመቆጣጠር ነው። በጥናቱ መሰረት ግን አዲሱ አሰራር ከአሁን በፊት ከነበረው አሰራር የተሻለና መሰረታዊ ችግሮችን የሚፈታ ነው፡፡

አንድ አንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት አዲሱ የሸማቾችና የችርቻሮ ነጋዴዎች ትስስር ችግሩን ይፈታዋል ብለው እንደማያምኑ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ ወንድወሰን በየነ እንደተናገረው፤ አሁን መሰረታዊ ሸቀጦችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ቢሆንም ስግብግብ ነጋዴዎች መኖራቸው ስለማይቀር ችግሩ ይቃለላል ማለት አይቻልም። ስለሆነም መንግስት በእነዚህ ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሉባባ ሀሰን በበኩላቸው፤ አዲሱ አሰራር ከመተግበር ይልቅ በመጀመሪያ መንግስት አቅርቦቱን ከህዝብ ፍላጎት ጋር ማጣጣም አለበት ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ስኳርና ዘይት በሚደብቁና ለግላቸው ጥቅም በሚያውሉ ነጋዴዎች ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ አለበት ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተውናል።

አራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነውና ሸቀጣሸቀጥ በመሸጥ የሚተዳደረው ወጣት ካሜል አብዱልሸኩር በበኩሉ አዲሱ አሰራር ቢጀመር የማህበረሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ሊያሟላ እንደሚችል ገልፆ አሁን ያለው አሰራር የማህበረሰቡን ፍላጎት የማያሟላ ከመሆኑም በላይ የአቅርቦት እጥረት መኖሩንም ተናግሯል።

ለአዲስ አበባ በወር 120 ሺ ኩንታል ስኳር ይቀርብ የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ አሰራር መሰረት 180 ሺ ኩንታል እንደሚያስፈልግ መረጋገጡን፤ በተመሳሳይም እስካሁን በነበረው አሰራርም የሚቀርበው 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፤ በአዲሱ አሰራር ወደ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ከፍ ማለቱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

አብርሃም አባዲ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy