Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መድረክ ከፓርቲዎች ውይይት ራሴን ያገለልኩት ውጤት ስለማያመጣ ነው አለ

0 342

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአደራዳሪ ጉዳይ አሁንም መስማማት አልተቻለም

ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ላይ በስድስት ዙሮች ከተሳተፈ በኋላ፣ በሰባተኛው ራሱን ያገለለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ምክንያቱ ውይይቱ ውጤት ስለማያመጣ ነው አለ፡፡ መድረክ ይህንን የገለጸው ዓርብ መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ከጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለድርድር፣ ክርክርና ለውይይት ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶችንና ደንቦችን ለመቅረፅ ሰባት ዙር ውይይት ያደረጉት ፓርቲዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውይይቱ በተናጠል ወይም በተወካይ አልያም አንድ ለአንድ ይደረግና ማን ያደራድር በሚሉ ሁለት ጉዳዮች ላይ መስማማት ተስኗቸዋል፡፡

መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ግንኙነታቸው በእኩልነት መርህ እንዲካሄድ ተስማምተዋል፡፡ መድረክ ያለውን ልምድና በአገር አቀፍ ምርጫ ያቀረባቸውን ዕጩዎች ብዛት በመጥቀስ የዋና ተደራዳሪነት ሚና እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ ይህ የማያስማማ ከሆነ ደግሞ ኢሕአዴግ ከመድረክ ጋር በተናጠል፣ ጎን ለጎን ደግሞ ሌሎች ፓርቲዎች ፍላጎታቸው ከሆነ ከእነሱ ጋር በጋራ እንዲወያይ መደረግ እንዳለበት ገልጿል፡፡ የኢሕአዴግ ተወካዮች ለተመሳሳይ አጀንዳ የተለያየ ውይይት ለማድረግ ኢሕአዴግ ፍላጎት እንደሌለው በመግለጽ፣ አጀንዳዎች እስኪለዩ ድረስ መድረክ መታገስ እንደሚገባው አሳስበው ነበር፡፡

በዕለቱ አደራዳሪ ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ሲሉ፣ ኢሕአዴግ ግን ድርድሩን ተሳታፊ ፓርቲዎች በፈረቃ ሊያደርጉት እንደሚገባ ተከራክሮ ነበር፡፡

መድረክና ኢሕአዴግ በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አቋም ከሌሎች አመራሮች ጋር መክረው መልሳቸውን ለመጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ይዘው እንዲመጡ ቀጠሮም ተይዞ ነበር፡፡ በዚሁ ሰባተኛ ዙር ውይይት የመድረክ መቀመጫዎች ባዶ ነበሩ፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎችም መድረክ ለመቅረቱ የሰጠው ማብራሪያ ካለ ጠይቀው ነበር፡፡

አደራዳሪው ማን ይሁን በሚለው ላይ ኢሕአዴግ አቋም ቀይሮ ከሆነ ለመረዳት ለቀረበው ጥያቄ የተገኘው ምላሽ አስቀድሞ የቀረበው ከሌሎች ፓርቲዎች ነበር፡፡ በዚህም የተወሰኑ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ያቀረበው በፈረቃ የማደራደር ሚና ችግር እንደሌለበት መገንዘባቸውን በመግለጽ የአቋም ለውጥ አሳይተዋል፡፡

በዚሁ የአደራዳሪ ጉዳይ ላይ ስምምነት ባለመገኘቱ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ያሉ ፓርቲዎች ድጋሚ ጉዳዩን አጢነውበት ምላሻቸውን ለሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡

የፓርቲዎቹ ውይይት በዚህ ሁኔታ ላይ ባለበት ወቅት መድረክ በጽሕፈት ቤቱ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ከውይይቱ ራሱን ያገለለበትን ምክንያት አብራርቷል፡፡ ‹‹ድርድሩ ተጨባጭ ውጤት ሊያስገኝ በሚችልበት ሁኔታ የሁለትዮሽ እንዲሆንና በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲመራ ያቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፤›› ሲል በጋዜጣዊ መግለጫው ገልጿል፡፡

መድረክ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዑካን የየፓርቲያቸውን አጀንዳዎችና አቋሞች ይዘው ተራ በተራ በሚጨቃጨቁበት ስብሰባ ወይም ጉባዔ ውጤት ይገኛል ብሎ እንደማያምን አስረድቷል፡፡ በዚህ ትክክለኛ የድርድር ባህሪ በሌለውና ውጤታማ ሊሆን በማይችል የ22 ፓርቲዎች ውይይት ሒደት ውስጥ መቀጠል ተገቢ ሆኖ ስላላገኘው ራሱን እንዳገለለም አስታውቋል፡፡

‹‹የሁለትዮሽ የድርድር አማራጭ ለኢሕአዴግ አቅርበን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፤›› ያሉት የመድረክ አመራሮች ኢሕአዴግ ፈቃደኝነቱን በአስቸኳይ እንዲገልጽ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡

መድረክ በዚሁ መግለጫው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአራት ወራት መራዘሙን ተቃውሟል፡፡ ለመራዘሙ የሕዝቡ ፈቃደኝነት በጥናት ስለመታየቱ የቀረበው ገለጻም ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡

መግለጫውን በጋራ የሰጡት የመድረክ አመራሮች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ አቶ ከላዬ ዘገዬና አቶ ጥሩነህ ገምታ የተለያዩ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ቀርበዋል፡፡ መድረክ ሕዝቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደማይፈልግ በምን እንዳወቀ ለቀረበው ጥያቄ ፕሮፌሰር በየነ ሲመልሱ፣ ‹‹ከሕዝቡ ጋር እኮ ነው የምንኖረው፣›› ብለዋል፡፡

መድረክ በተደጋጋሚ እንደሚያነሳውና በጋዜጣዊ መግለጫውም እንዳነሳው ‘ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች’ ሲል ስለእነማን እንደሆነ ተጠይቀውም፣ ‹‹ከኢሕአዴግ ጋር የጥቅም ግንኙነት የሌላቸው እንደ መድረክ ያሉ ፓርቲዎችን ማለታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ወሳኝ ጥያቄዎች ሲቀርብለት ራሱ ከመመለስ ይልቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርስ እንዲነካከሱ በማድረግ አድበስብሰሶ የማለፍ ልምድ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ዓይነት አካሄድ መድረክን በ2001 ዓ.ም. ተካሂዶ ከነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር ደንብ ድርድር እንዳገለለም አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪም የአሁኑ የድርድር ምኅዳር በመተማመን እንዲካሄድ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ኢሕአዴግ እንዲወስድ መድረክ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገበት ገልጸው፣ እነዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትና የመድረክና የሌሎች ፓርቲዎች አመራሮች ከእስር መፈታት እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ በመድረክ እምነት ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት የተገደደው አገሪቱ ባለችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ለኢሕአዴግ ሲያሳውቁ የኢሕአዴግ ተወካዮች እንዳጣጣሉት አውስተዋል፡፡ reporte

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy