Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምጣኔ ሃብት ሲያድግ ስደት ለምን?

0 622

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ780ሺ በላይ ከጎረቤት አገራት የመጡ ስደተኞችን በማስጠለል ድጋፍ እያደረገች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በዓመት ከአንድ ሺ የአገሪቷ ዜጎች መካከል ዘጠኙ ወደ ሌሎች አገራት ይሰደዳሉ።

ትኩረቱን በሰዎች ፍልሰት ላይ ያደረገው (አይ..ኤም) መረጃ የሚያመለክተው፤ በህጋዊና በህገወጥ መንገድ ከሚሰደዱ ዜጎች መካከል ለሥራ እና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እንዲሁም በአርብቶ አደሮች በኩል ደግሞ፤ ለእንስሳት ውሃ እና መኖ ፍለጋ ድንበር ከሚያቋርጡባቸው ምክንያቶች ዋነኞቹ ናቸው። በእርግጥ በኢትዮጵያ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁንና ዕድገቱን በማይገልጽ መልኩ ወጣቶች ሲሰደዱ ይስተዋላል። ለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? በሚለው ጥያቄ ላይ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ያካፍላሉ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ወልዳይ አመሃ፤ «የኢኮኖሚ ዕድገት ስላለ ብቻ የወጣቶች ስደት ይቆማል ማለት አይቻልም» ይላሉ። የሰዎች ፍላጎት የተለያየ ሲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸውም የተሻለና ምቹ ቦታዎችን መፈለግ እንደማይቀር ነው የሚያስረዱት። የዓለም ባንክ በአስር ዓመት ውስጥ ባጠናው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተቀጣሪዎች መካከል ገቢያቸው በጥሩ ሁኔታ ያደገው የቤት ሠራተኞች መሆናቸውን እንደሚጠቁም ይናገራሉ። ይሁንና በብዛት ወደ ዓረብ አገራት የሚሰደዱት እነዚሁ የቤት ሠራተኞች መሆናቸውን ነው የሚገልፁት። ይህም ከሚያገኙት የበለጠ ገቢ በመመኘት ስደትን ተመራጭ ማድረጋቸውን ይጠቁማሉ።

እንደ ዶክተር ወልዳይ ገለፃ፤ በሌላ በኩል ስደትን ለመቀነስ አብዛኛውን የአገሪቷን ኢኮኖሚ በዋነኛነት በሰው ኃይል ልማት በተለይም በአምራች ኃይል ላይ ሊያተኩር ይገባል። ይህም ሲባል የአገሪቷ ዕድገት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር መጣመር አለበት። ይህ ባለመጠናከሩ በርካታ ወጣቶች እንዲሰደዱ ምክንያት ይፈጥራል። በመሆኑም አምራች የሰው ኃይል በሥራ ላይ ማሰማራቱ ከዕድገቱ ጎን ለጎን ሊተኮርበት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የመደበው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ስደትን የመቀነስ አቅም ይፈጥራል። ወጣቶች እና ሴቶች በማምረቻ ተቋማት ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይሰጣል። በመሆኑም ይህ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይመክራሉ።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ እስራኤል ወልደኪዳን በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ወጣቶች ለስደት የሚገፋፋቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራሉ። «በተለይ በህግ ማዕቀፉ ውስጥ የወጣቶች ጉዳይ በላዕላይ ደረጃ አለመቀመጡ ችግሩን አባብሶታል። በተጨማሪም በአገሪቱ በገጠር እና ከተማ አካባቢ ላሉ ወጣቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ እኩል ትኩረት አልተሰጣቸውም። በገጠር አካባቢም ከእርሻ በተለየ በሌሎች ሥራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ አለመደረጉ እና በጥቃቅንና አነስተኛ የሚደራጁ አካላት በገጠር አለመበራከታቸው፤ አልፎ አልፎም ለሥራ የመደራጀት ልማድ አለመኖሩ ክፍተት እንዲኖር አድርጓል» ባይናቸው።

«የወጣቶችን ችግር ለማቃለል ተግባርና ቃል አልተዋሃዱም» ይላሉ። ከህግ አኳያም በርካታ የህግ ማዕቀፎች በወረቀት ላይ ሰፍረው ይቀመጡ እንጂ ተግባሩ ግን በሚጠበቀው ልክ መሬት የነካ እንዳልነበር ነው የሚናገሩት። በመሆኑም የችግሮቹ መደራረብ ወጣቶችን ለስደት እየገፋፋ መሆኑን ይጠቁማሉ። ባለድርሻ አካላት ተብለው ከመለየታቸው ይልቅ የወጣቶች ጉዳይ ሁሉም የአገሪቱ ህዝብ የመፍትሄው አካል እንዲሆን አድርጎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ነው የሚገልፁት።

አቶ ማቲያስ አሰፋ በወጣቶችና ስፖርት የወጣቶች ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር ሲሆኑ በአቶ እስራኤል «ለገጠር እና ከተማ ወጣቶች እኩል ትኩረት አልተሰጠም» በሚለው ሃሳብ አይስማሙም። «ይልቁንስ መንግሥት በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ወጣቶች ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸውን በማገናዘቡ በገጠርም ሆነ በከተማ ለሚገኙ ወጣች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የተሰጠው ትኩረት እኩል ነው» ይላሉ። ችግሩ ግን አሳሳቢ የሆነው የአስፈፃሚ አካላት ሥራውን ተግባር ተኮር ባለማድረጋቸው ነው የሚል ወቀሳ ያነሳሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከሆነ፣ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት በሁለት አሃዝ ማደጉ ብቻ ወጣቶች ከስደት መታደግ አይችልም ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያውን የዶክተር ወልዳይ ሐሳብ ይጋራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ታዳጊዎች ወደ ወጣት የዕድሜ ክልል ይገባሉ። ከዚህም ባሻገር በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ከመሆናቸው የተነሳ በዚያው ልክ የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉን እንደችግር ይጠቅሳሉ። «እስከ አሁን ድረስ እያደገ ባለው ምጣኔ ሃብትና የወጣቶች ፍላጎት እንዲጣጣም የተሰራው በቂ አልነበረም። ለዚህም የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቅረፍ እና ወጣቶችን በፍላጎታቸው እና በችሎታቸው እንዲሰማሩ ውጤታማ ተግባር ይጠበቃል» በማለት ያብራራሉ።

እንደ አቶ ማቲያስ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ስደትን ለመቀነስ የሚያስችል የወጣቶች ፓኬጅ ተቀርጿል። ይህን ተግባራዊ የማያደርጉ አካላትም ተጠያቂነት የሚያስከትል አሠራር ተዘጋጅቷል። በመሆኑም በቀጣይ እቅዱ ወደ ውጤታማ ተግባር የሚለወጥ ከሆነ ለወጣቶች ብሩህ ጊዜ እንደሚሆን ይተነብያሉ። ችግሩን ለማቃለልም የሃይማኖት አባቶች፣ ከማህበረሰቡ ተሰሚነት ያላቸው አካላትን በማሳተፍ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ከአሁኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል። ወጣቶችም በአገር ውስጥ ሠርተው ሃብት እንዲያፈሩ የአቅም ግንባታ መስጠትና ማገዝ ለነገው አገር ተረካቢ ወጣት በአገር ውስጥ ምቹ መደላድል ይፈጥራል። የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።

ባለሙያዎቹ በጋራ እንደሚስማሙት፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰጠው ትኩረት የተጠናከረ እና ውጤታማ ባለመሆኑ ስደት እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዕድገት አኳያ መልካም አጋጣሚዎች በመፈጠር ላይ ናቸው። መንግሥትም እነዚህን ችግሮች ማጤንና ስደትን ለማስቆም የጀመራቸውን ጥረት በልበ ሙሉነት መስራትና ጥረቶቹን ማጠናከር እንዳለበት ያመላክታል።

ጌትነት ተስፋማርያም እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy